79.57 F
Washington DC
June 14, 2021
Satenaw Ethiopian News/Breaking News
Amharic News

“አሁናዊው የኢትዮጵያ ሁኔታ ከመንግሥት ፍጥነትን፣ ከፓርቲዎች ብስለትን እና ከሕዝብ ትዕግስትን የሚጠይቅ ነው” ዶክተር በዕውቀቱ ድረስ
“አሁናዊው የኢትዮጵያ ሁኔታ ከመንግሥት ፍጥነትን፣ ከፓርቲዎች ብስለትን እና ከሕዝብ ትዕግስትን የሚጠይቅ ነው” ዶክተር
በዕውቀቱ ድረስ
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 08/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ቀድሞ በሀገር ጉብኝት፣ በመልክዓ ምድራዊ ጥናት፣ በሃይማኖት ስብከት፣ በንግድ
ልውውጥ እና በበጎ አድራጎት፤ በኋለኛው ዘመን ደግሞ በቅኝ ግዛት እና በዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ቀጣናውን ሲያንዣብቡበት
የኖሩት ምዕራባውያን የኢትዮጵያውያንን ሥነ ልቦና ከሀገሬው በላይ በደንብ ለመረዳት ጥረዋል፡፡ በቅንነት ከተገነባው
የኢትዮጵያውያን የሀገር ፍቅር እሳቤ ውስጥ ብልጣ ብልጦቹ ምዕራባውያን ደካማ ጎን ያሏቸውን ክፍተቶች ሲለቅሙ ኖረዋል፡፡
ኢትዮጵያውያን በሀገራቸው ሉዓላዊነት ለደቂቃ መደራደርን የማይፈልጉ፣ ከራሳቸው ሕይዎት በላይ የሀገራቸው ክብር ግድ
የሚላቸው እና ሀገራዊ ችግሮችን ፊት ለፊት የሚጋፈጡ መሆናቸውን ዓለም በሚገባ ያውቃል፡፡
በሀገራቸው ክብር የመጣን ጠላት በጦር አውደ ውጊያዎች ሲፋለሙ ነጭ ለብሰው፣ ፀሐይ ሞቋቸው እና ሀገር አውቋቸው እንጂ
ተደብቆ ትግልን አይመርጡም ነበር፡፡ ኢትዮጵያውያን ጠላቶቻቸውን በሌሊት ሄደው ቢገጥሙ እና ተደብቀው ቢያጠቁ እንኳን
ከድል ማግስት እምነት ያጎደሉ ያህል ይሰማቸዋል እንጂ ጀብድ የፈፀሙ አድርገው አይቀበሉም ነበር፡፡ የኢትዮጵያውያንን የግንባር
ስጋነት የሚያውቁት ምዕራባውያን እና ቅጥረኞቻቸው ብዙ ጊዜ ኢትዮጵያን የወጉት በደካማ ጎኗ ከጀርባ ሆነው ነበር፡፡ ድብቅ
ሴራዎቻቸው እና ስውር እጆቻቸው በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ዘመን የማይፍቃቸው ጠባሳዎችን ትተው አልፈዋል፡፡
በአራቱም አቅጣጫ የቀበሩትና በየዘመናቱ የፈነዱትን የሴራ ፈንጅዎች ጊዜያዊ ጉዳት ሲያክሙ የኖሩት መሪዎቿም በተፈጥሮ
ሃብቶቻቸው የሚጠቀሙበት እና ፀጋዎቻቸውን አስተውለው የሚያለሙበት ጊዜና ጉልበት አጥተው በኃይል ወደ ስልጣን ወጥተው
በኃይል ከስልጣን ተገፍተው ሲወርዱ ታይቷል፡፡
አንዳንድ የቀጣናው ጎረቤት ሀገራት እና ምዕራባውያን የኢትዮጵያን ጎልቶ መውጣት ከማይፈልጉበት ምክንያት አንዱ ደግሞ
የዓባይ ውኃ ነው፡፡ በዓባይ ወንዝ የውኃ አበርክቶ ከ85 በመቶ በላይ ድርሻ ያላት ሀገር ኢትዮጵያ ብትሆንም ውኃውን በመጠቀም
የነበራት ሚና ግን “ምንም” የሚባል ነበር፡፡
በጥንታዊው እና ረጂሙ የኢትዮጵያ የሥነ መንግሥት ምስረታ ታሪክ ውስጥ ወደ መሪነት ዙፋን ብቅ ያሉ ነገሥታት እና መሪዎች
በዓባይ ወንዝ የመጠቀም የፀና ፍላጎት ነበራቸው ያሉን በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ጥናት
ትምህርት ክፍል ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት በዕውቀቱ ድረስ (ዶክተር) ናቸው፡፡ በውስጣዊ ችግር፣ በምጣኔ ሃብታዊ አቅም እጦት
እና በውጭ ኃይሎች ሴራ ምክንያት ዓባይን አልምቶ የመጠቀም እቅዶቻቸው ገቢር አልሆነም እንጂ ይላሉ፡፡
እንደ ዶክተር በዕውቀቱ ገለፃ ኢትዮጵያ ታላቁን ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከ10 ዓመታት በፊት በዓባይ ወንዝ ላይ ስትጀምር የገንዘብ
አቅሙን በራሷ ለመወጣት ከመወሰኗ በተጨማሪ ሳንካ ፈጣሪዎቹ የጎረቤት ሀገራት በራሳቸው የውስጥ ችግር መታመስ መልካም
አጋጣሚ የፈጠረ ነበር ይላሉ፡፡ ፕሮጀክቱን በተያዘለት የጊዜ መርሐ ግብር መሰረት መፈፀም አለመቻሏም ለአሁናዊው መጠነ ሰፊ
ጫና እንደዳረጋት በመጠቆም፡፡ ግድቡ በተያዘለተ ጊዜ ተጠናቆ ቢሆን ኖሮ ከሚያስገኘው ምጣኔ ሃብታዊ ትሩፋት በዘለለ
ከውስጣዊ ችግሮቻችን በተጨማሪ ዓለም ዓቀፋዊ እና ቀጣናዊ ጣልቃ ገብነቶች አይበረቱም ነበር ነው ያሉት፡፡
የሕዳሴው ግድብ መጠናቀቅ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለጂኦ ፖለቲካዊ ቀጣናው የተለየ ትርጉም እንዳለው የፖለቲካ ሳይንስ
ምሁሩ አብራርተዋል፡፡ በቅርቡ የሚካሄደው ሁለተኛ ዙር የውኃ ሙሌት ኢትዮጵያን ወደ አዲስ ዲፕሎማሲያዊ ትሩፋት ያሸጋግራታል
ብለዋል፡፡ ዶክተር በዕውቀቱ ከሁለተኛው ዙር የውኃ ሙሌት በኋላ የተፋሰሱ ሀገራት በግድቡ ላይ ያላቸውን ተፅዕኖ የሚያቆሙት
ለኢትዮጵያ ብለው ሳይሆን ለራሳቸው ደኅንነት በማሰብ ጭምር ነው ብለዋል፡፡
ከግድቡ መጠናቀቅ በኋላ በሀገር ውስጥ የኢትዮጵያ ኃይል የማመንጨት አቅም ይሻሻላል፤ ይህም ለሥራ ዕድል ፈጠራ የተለየ
ትርጉም ያመጣል ነው ዶክተር በዕውቀቱ፡፡ ከሀገር ውጭም ቀጣናውን በኃይል አቅርቦት ማስተሳሰር ይጀምራል ብለዋል፡፡ ሌሎቹ
የዓባይ ተፋሰስ ሀገራት የተፈጥሮ ሃብትን ተጠቅሞ መለወጥን ትምሕርት ይወስዳሉ፤ ይህም ለጋራ ትብብር እና እድገት ከማገዙም
በላይ የኢትዮጵያ ዓለም አቀፋዊ ተሰሚነት በዚሁ ልክ ያድጋል ባይ ናቸው፡፡
ዶክተር በዕውቀቱ እንደሚሉት ሁለተኛው ዙር የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ውኃ ሙሌት ከፍትሐዊ ተጠቃሚነት በዘለለ
በቀጣናው የተሰሚነት አቅምንም ይጨምራል፡፡ ግድቡ አሁን ባለበት የግንባታ ደረጃ እስካለ ድረስ ውኃ መያዙ ወደዱትም
ጠሉትም አይቀርም፡፡ ነገር ግን ይላሉ የፖለቲካ ሳይንስ መምሕሩ ኢትዮጵያ ከምትፈልገው ግብ እስክትደርስ የግድቡን ህልውና
መጠበቅ፣ በቂ ቅድመ ዝግጅት ማድረግ፣ ውስጣዊ ልዩነቶችን ማከም እና የደኅንነት ተቋማትን ማጠናከር ይገባታል፡፡
የተፋሰሱ ሀገራት በተለይም ግብጽ በዓባይ ውኃ ላይ ለዘመናት ያላት አቋም ግልፅ ነው፡፡ ሱዳንም ምንም እንኳን የሕዳሴው
ግድብ ግንባታ በሕልውናዋ ላይ አደጋ እንደሌለው በራሷ የዘርፉ ምሁራን ሳይቀር በተደጋጋሚ ቢገለፅም የውስጥ ፖለቲካዊ
ችግሮቿን ለጊዜው ለማከም ወጥ አቋም ማሳየት እንደተሳናት ታይቷል ብለዋል ዶክተር በዕውቀቱ፡፡
የሦስቱ ሀገራት ድርድር ከአፍሪካ ኅብረት ጥላ ስር እንዳይወጣ ኢትዮጵያ ግልፅ እና ጠንካራ አቋም ማራመዷን አጠናክራ
መቀጠል አለባት ነው ያሉት፡፡ ከ13 ዓመታት በፊት ከአፍሪካ አንድነት ድርጅት ወደ አፍሪካ ኅብረት የተሸጋገረው ድርጅቱ ዋና
ዓላማው “አፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄ ይሻሉ” የሚል መርህ በመያዙ መሆኑን አስታውሰዋል፡፡ ዶክተር በዕውቀቱ
የሦስቱን ሀገራት ችግር ከፍሪካ ኅብረት ጥላ ስር እንዳይወጣ በማድረግ ኢትዮጵያ ዲፕሎማሲያዊ የበላይነትን ልትወስድ ይገባል
ብለዋል፡፡
ይህንን ቀጣናዊ ችግር ለመቅረፍ ብዙ ውጣ ውረድ እንዳለው ነው ምሁሩ የገለጹት፡፡ “አሁናዊው የኢትዮጵያ ሁኔታ ከመንግሥት
ፍጥነትን፣ ከፓርቲዎች ብስለትን እና ከሕዝብ ትዕግስትን የሚጠይቅ ነው” ብለዋል ዶክተር በዕውቀቱ፡፡ መምሕሩ እንዳሉት
መንግሥት ቅድሚያ ለሚሰጣቸው ጉዳዮች ቅድሚያ በመስጠት እና የዜጎችን ደኅንነት በማስጠበቁ ረገድ በጊዜ የለኝም መንፈስ
ሊሠራ ይገባል፡፡
ተፎካካሪ ፓርቲዎችም ቅድሚያ “ለማዕዱ” በመስጠት በጋራ እና በትብብር መንፈስ በብስለት መሥራት እና ሕዝቡም ነገሮችን
በትዕግስት እና በንቃት መከታተል እንዳለባቸው መክረዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m


Previous articleየብርቱካን ፍራፍሬ በሽታ መድኃኒት መገኘቱ ተገለጸ፡፡


Source link

Related posts

“ኢየሩሳሌምን መሠላት፣ ገነትን በምድር ሠራት”

admin

አቶ እርስቱ ይርዳ ከ190 ሚሊየን ብር በላይ ለሚገነባው የሳውላ የንጹህ መጠጥ ውሃ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ አኖሩ

admin

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአውሮፓ ህብረት ምርጫውን የሚታዘቡ ባለሙያዎችን እንደሚልክ አስታወቀ

admin