56.68 F
Washington DC
April 21, 2021
Satenaw Ethiopian News/Breaking News
Amharic News

ታክስ ማጭበርበር የግብር አሰባሰብ ሂደቱ ላይ ጫና እየፈጠረ መሆኑን የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ አስታወቀ፡፡

ታክስ ማጭበርበር የግብር አሰባሰብ ሂደቱ ላይ ጫና እየፈጠረ መሆኑን የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ አስታወቀ፡፡

ባሕር ዳር፡ የካቲት 27/2013 ዓ.ም (አብመድ) በአማራ ክልል ከ20 ሺህ በላይ ግብር ከፋዮች የታክስና የግብር እዳ አለባቸው። በዚህ ምክንያት ክልሉ ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ አጥቷል፤ ከዚህ ውስጥ 143 ሚሊዮን ብር ብቻ ማስመለስ ተችሏል። የአማራ ክልል ምክር ቤት የበጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ተጠሪ መሥሪያ ቤቶች የ2013 በጀት ዓመት የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም በባሕር ዳር ገምግሟል።

የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ ምክትል ኀላፊ ክብረት ማሕሙድ ባቀረቡት ሪፖርት በበጀት ዓመቱ 20 ነጥብ 56 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ በስድስት ወራቱ 10 ነጥብ 02 ቢሊዮን እንደተሰበሰበ ተናግረዋል። አፈጻጸሙ 92 ነጥብ 4 በመቶ ነው።

አቶ ክብረት ጥሩ አፈጻጸም እንዲመዘገብ ያስቻሉ ምክንያቶች ያሉአቸውን በሪፖርታቸው ጠቅሰዋል፡፡ ከ300 ሺህ በላይ ግብር ከፋዮች ያለቅጣት በሰዓቱ ግብር ከፍለዋል፤ የደንበኞችን መረጃ አያያዝ ለማዘመን እንቅስቃሴ ተደርጓል፤ የዲስፕሊን ግድፈት በነበረባቸው የተቋሙ ሠራተኞች ላይ ርምጃ ተወስዷል፤ የአጋርና ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ጥሩ እንደነበርም አንስተዋል።

በግማሽ ዓመቱ ወደ 43 ሺህ 252 ግብር ከፋዮች በአዲስ ወደ ሕጋዊ መረቡ እንዲገቡ ለማድረግ የተሠራው ሥራ አበረታች መሆኑም በቋሚ ኮሚቴው ተገምግሟል።

በሌላ በኩል የግብይት ደረሰኝ አለመጠቀም፣ የታክስ ሕግ አለማስከበር፣ ታክስና ግብር ማጭበርበር፣ በግብር ከፋዮች ዘንድ የሚስተዋል የአመለካከት ችግር እና የሕግ ማስከበር ዘመቻው በገቢ አሰባሰብ ሂደቱ የነበሩ ችግሮች ተብለው ተነስተዋል፡፡ በተለይ የማጭበርበር እንቅስቃሴው ክልሉን ከፍተኛ ዋጋ እያስከፈለ መሆኑን ነው ምክትል ቢሮ ኀላፊው የተናገሩት። በአንድ ግለሰብ ቤት በተደረገ ፍተሻ አራት ሀሰተኛ የሽያጭ መመዝገቢያ መሳሪያ፣ ከ300 በላይ የተለያዩ ተቋማት የግዥ ደረሰኞች እንዲሁም ከ80 በላይ የተለያዩ ተቋማት ሀሰተኛ ማኅተሞች መገኘታቸውን ጠቅሰዋል። በሌሎች ግለሰቦችም ተመሳሳይ ድርጊት መገኘቱን ነው ያመላከቱት። ይህም የክልሉን ገቢ በማሳጣት ከፍተኛ ተጽዕኖ እያደረሰ ነው ብለዋል።

በተመሳሳይ የተርን ኦቨርና የተጨማሪ እሴት ታክስ አሠባሰብ መሠረታዊ ክፍተት ያለባቸው መሆኑ እና የማኅበረሰቡ በደረሰኝ የመገበያየት ልምድ አናሳ መሆን በሂደቱ የታዩ ክፍተቶች ናቸው ተብለዋል።

ቋሚ ኮሚቴው በቀጣይ ትኩረት ያስፈልጋቸዋል ካላቸው ነጥቦች መካከል የሒሳብ መመዝገቢያ ማሽን፣ የተርን ኦቨር ታክስ፣ የተጨማሪ እሴት ታክስ፣ የንግድ ገቢ ግብር፣ የእርሻ ሥራ ገቢ፣ የመሬት መጠቀሚያና ውዝፍ ገቢ ግብርን በውጤታማነት መሰብሰብ ተነስተዋል።

የስመ ንብረት ዝውውር መመሪያው ከከተማ ልማት ቤቶችና ኮንስትራክሽን ቢሮ ጋር መግባባት ስላልተፈጠረበት ከፍተኛ ውዝግብ እንዲፈጠር ማድረጉንም የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወይዘሮ ወርቄ አሰፋ አንስተዋል። የተሻለ አማራጭን በመፈለግ የአሠራር ማስተካከያ ማድረግ እንደሚገባም ተናግረዋል።

የገቢዎች ቢሮ ተወካዮች በሰጡት ማብራሪያ ውዝፍ የሊዝ እዳ ገቢ እንዳይሆን የመረጃ ስወራ ከፍተኛ ፈተና እንደሆነበት አስታውቋል።

የቢሮው ምክትል ኀላፊ ፍቅረማርያም ደጀኔ በሰጡት ምላሽ የታዩ መልካም ተሞክሮዎችን ይበልጥ በማስፋት ክፍተቶችን ለማረም በትኩረት ይሠራል። በገቢ ተቋሙ በኩል ያሉ የክትትል ውስንነቶችን ለመፍታትም የአመለካከት ለውጥ እንዲመጣ ስልጠና ይሰጣል ነው ያሉት።

ዘጋቢ:- ደጀኔ በቀለ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡

Source link

Related posts

በሲሚንቶ ግብይት የወጣውን የዋጋ ተመን ተግባራዊ ባላደረጉ ነጋዴዎች ላይ ሕጋዊ እርምጃ መውሰድ መጀመሩን የአማራ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ አስታወቀ፡፡

admin

መንግሥትና ተግባሩ (ግዴታው) – አገሬ አዲስ | Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider

admin

የደቡብ እና ሲዳማ ክልሎች ምርጫው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ እየሰሩ መሆኑን ገለጹ

admin