73.2 F
Washington DC
June 14, 2021
Satenaw Ethiopian News/Breaking News
Amharic News

በ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ አካል ጉዳተኞች በንቃት እንዲሳተፉ እየሠሩ መሆኑን የፖለቲካ ፓርቲዎች ተናገሩ፡፡

በ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ አካል ጉዳተኞች በንቃት እንዲሳተፉ እየሠሩ መሆኑን የፖለቲካ ፓርቲዎች ተናገሩ፡፡

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 24/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ከአንድ ቢሊዮን በላይ ወይም 15 በመቶ የሚሆነው የዓለማችን ሕዝብ አካል ጉዳተኛ እንደሆነ የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ያመላክታል፡፡ በተለይ ባላደጉት ሀገራት አካል ጉዳተኝነት በቁጥር ከፍ ያለ እና አካል ጉዳተኞች የሚያጋጥሟቸው የሕይወት ፈተናዎች የበዙ ናቸው፡፡ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተሳትፎአቸው እና አበርክቶአቸው ስለሚገደብ በማኅበረሰቡ ጥገኛ የመሆን እድላቸው የሰፋ ነው፡፡

እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ ሀገራት የአካል ጉዳተኞችን ተሳትፎ በተለያየ ዘርፍ ለማሳደግ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን ከግምት ውስጥ ያስገባ ማስፈጸሚያ ሠነድ ያዘጋጃሉ፡፡

በ6ኛው ሀገራዊ ምርጫም ለአካል ጉዳተኞች ምን ያህል ትኩረት እንደተሰጠም አራት የፖለቲካ ፓርቲዎችን ጠይቀናል፡፡

ከብልጽግና ፓርቲ አሚኮ ያነጋገራቸው አቶ ደረጀ አበጀ በበኩላቸው አካል ጉዳተኞች በማንኛውም መስክ እኩል ተሳታፊና ተጠቃሚ የሚሆኑበት መንገድ መመቻቸት አለበት ብለዋል፡፡

ፓርቲያቸው ብልጽግና አካል ጉዳተኞች መብታቸውን እንዲጠቀሙ ካሁን ቀደም ከነበረው በተሻለ መንገድ ሠርቷል፤ በስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ የአካል ጉዳተኞች ተሳትፎ እንዲያድግ ከዘርፉ ማኅበራት ጋር ሲሠሩ እንደነበር ገልጸዋል፡፡ በወረዳ እና በክልል ምክር ቤቶች በማሳተፍ ችግሮቻቸውን እንዲያቀርቡ እየሠሩ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡ አቶ ደረጀ እንዳሉት በርካታ አካል ጉዳተኞች ችሎታቸውን መሠረት በማድረግ በአስፈጻሚነት እየሠሩ ነው፡፡

ከአማራ ዲሞክራሲያዊ ኃይል ንቅናቄ (አዲኃን) አቶ ጌታሁን ዋለ እንዳሉት ፓርቲያቸው አካል ጉዳተኞች እንደ ማንኛውም ሰው በፖለቲካው እኩል ተሳታፊ መሆን አለባቸው ብሎ ያምናል፡፡ አቶ ጌታሁን ካሁን በፊት በነበሩ የምርጫ ጊዜያት አካል ጉዳተኞችን በመራጭነት፣ ተመራጭነት እና በአባልነት በማሳተፍ በኩል ክፍተት መኖሩን ጠቅሰዋል፡፡

ይህን ችግር ለመቅረፍ ፓርቲያቸው አዲኃን አካል ጉዳተኞችን በእጩነትም ሆነ በአባልነት በማሳተፍ ለፓርቲው እድገት ይሠራል ነው ያሉት፡፡ አካል ጉዳተኞች እንደማንኛውም ዜጋ በማንኛውም መንገድ እኩል ተሳታፊ መሆን አለባቸው ብሎ ያምናል፤ በማንኛውም መስክ ቢሳተፉ ብቁ አይደሉም የሚለው የተሳሳተ አመለካከት ሊቀረፍ ይገባል ብለዋል፡፡

አቶ ጌታሁን “አካል ጉዳተኞችን በማንኛውም መንገድ እኩል ለማሳተፍ መንገዱን ማመቻቸት ከእኛ ይጠበቃል፤ ይህንንም ትኩረት ሠጥተን እየሠራን ነው” ብለዋል፡፡

በ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ አካል ጉዳተኞች በመራጭነት እንዲሳተፉ በማድረግ ረገድም መሥራታቸውን ተናግረዋል፡፡

ከኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ሀሳብ የሰጡን አቶ ፀጋዬ ፈጠነ እንዳሉት ፓርቲያቸው አካል ጉዳተኝነት የሚያስከትለውን ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ችግሮች መቅረፍ ተገቢ ነው ብሎ ያምናል፡፡ አካል ጉዳተኞች በመንግሥትም ሆነ በማኅበረሰቡ የሚደርስባቸውን መገለል በማስቀረት ለሀገር ልማት አበርክቶአቸውን ለማሳደግ ይሠራል ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ በሚሊዮን የሚቆጠሩ አካል ጉዳተኞች ይኖራሉ ያሉት አቶ ፀጋዬ የእነዚህን አካል ጉዳተኞች ችግር የተረዳ ማኅበረሰብና አመራር መፍጠር ተገቢ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ፓርቲያቸው ኢዜማም እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ ይሠራል ነው ያሉት፡፡

አቶ ፀጋዬ እንዳሉት ፓርቲው የመግባቢያ ሠነድ ሲያዘጋጅ አካል ጉዳተኞችን አሳትፏል፤ በአባልነትና በዕጩነት ለማሳተፍ ባይሳካለትም ለተወዳዳሪነት በቀረበባቸው የምርጫ ጣቢያዎች ላይ አካል ጉዳተኞች እንዲሳተፉ ከማኅበራት ጋር ሠርቷል፡፡

ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) አሚኮ ያነጋገራቸው አቶ ገበያው ይታየው ደግሞ አብን አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ አድርጎ እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

አብን የአካል ጉዳተኞችን ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተሳትፎ ለማሳደግ እና ተጠቃሚ ለማድረግ ያላሰለሰ ጥረት ያደርጋል ብለዋል፡፡ አካል ጉዳተኞች በተለያየ ዘርፍ ያለባቸውን ችግር እና የሚገጥማቸውን ፈተና ለመቅረፍ ንቅናቄው እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ለእጩነት ከተመዘገቡ 691 የንቅናቄው አባላት 17 በመቶ ያህሉ አካል ጉዳተኞች መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡ በመራጭነት እና በታዛቢነት እንዲሳተፉ የግንዛቤ ሥራ እየሠሩ እንደሆነም አስታውቀዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 23/2013 ዓ.ም (አሚኮ)

Source link

Related posts

የመራጮች የምዝገባ ሒደት ባልተጀመረባቸው የምርጫ ክልሎች ከሚያዝያ 29 እስከ ግንቦት 13 ቀን ድረስ በልዩ ሁኔታ እንዲከናወን ተወሰነ

admin

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ ግድምና ጅሌ ጥሙጋ ወረዳ ተከስቶ የነበረው ችግር መፈታቱ ተገለጸ

admin

ጀኔራል ብርሃኑ ጁላ በኢትዮጵያ ከእንግሊዝ አምባሳደር ጋር ተወያዩ

admin