70.74 F
Washington DC
May 14, 2021
Satenaw Ethiopian News/Breaking News
Amharic News

በፌዴራል መንግሥት የሚገነቡ መሠረተ ልማቶች በአግባቡ እንዲከናወኑ ክልሉ በትኩረት እንደሚሠራ ርእሰ መሥተዳድር አገኘሁ ተሻገር አስታወቁ፡፡

በፌዴራል መንግሥት የሚገነቡ መሠረተ ልማቶች በአግባቡ እንዲከናወኑ ክልሉ በትኩረት እንደሚሠራ ርእሰ መሥተዳድር አገኘሁ ተሻገር አስታወቁ፡፡

ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 03/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር አገኘሁ ተሻገርና ሌሎች የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር በፌዴራል መንግሥት በጀት እየተገነቡ የሚገኙ መሠረተ ልማቶችን የግንባታ ሂደት ምልከታ አድርገዋል። ምልከታዉ የባሕር ዳር ዘጌ አስፋልት ኮንክሪት መንገድ እና በባሕር ዳር ከተማ እየተገነባ የሚገኘውን አዲሱ የዓባይ ወንዝ ድልድይን አካቷል።

የባሕር ዳር ዘጌ አስፋልት ኮንክሪት መንገድ ግንባታ የተጀመረው ‘በማርካን ትሬዲንግ’ ተቋራጭነት በ2010 ዓ.ም ነበር። 21 ነጥብ 8 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ይህ መንገድ 4 መቶ 50 ሚሊዮን ብር ተመድቦለታል። ይሁን እንጂ ፕሮጀክቱ የወሰን ማስከበር፣ የሲሚንቶና የነዳጅ መወደድ ችግሮች ስላጋጠመው የተፈለገዉን ያክል ሊሠራ እንዳልቻለ የፕሮጀክቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ ማንደፍሮ በሪሁን አስረድተዋል።

ፕሮጀክቱን ለማጠናቀቅ ተቋራጩ አቅሙ የቻለዉን ሁሉ እያደረገ እንደሚገኝም አቶ ማንደፍሮ ተናግረዋል።

የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አገኘሁ ተሻገር የባሕር ዳር ዘጌ አስፋልት ኮንክሪት መንገድ ግንባታ ሲጠናቀቅ ለአካባቢዉ ሁለንተናዊ እድገት ጠንካራ ጠቀሜታ ይኖረዋል ብለዋል። እየተጓተተ ያለው ይህ ፕሮጀክት በወቅቱ እንዲጠናቀቅ ክልሉ ትኩረት ሰጥቶ ድጋፍ እንደሚያደርግ ርእሰ መሥተዳድሩ ገልጸዋል።

ይሁን እንጂ ፕሮጀክቱ ከሦስተኛ ወገን ነፃ ሆኖ በተሰጠው አካባቢ እንኳ የተፈለገዉን ያክል እንዳልሠራና በቀሪ ጊዜ ጠንክሮ ሊሠራ እንደሚገባ አቅጣጫ አስቀምጠዋል።

የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ምልከታ ያደረጉበት ሌላው አዲሱ የዓባይ ድልድይ የግንባታ ሂደት ነው። ድልድዩ አሁን ላይ 44 በመቶ መጠናቀቅ እንደሚጠበቅበት ነገር ግን ግንባታው 27 በመቶ ላይ መሆኑን በስታዲያ የምህንድስና ሥራዎች ተቆጣጣሪ ድርጅት የድልድዩ ምክትል ዋና ተጠሪ መሀንዲስ የሆኑት ኢንጂነር ፍቅረሥላሴ ወርቁ አስረድተዋል፡፡

ድልድዩ 380 ሜትር እንደሚረዝም፣ የጎን ስፋቱ ደግሞ 49 ሜትር ሲሆን በግራና በቀኝ በአንድ ግዜ ስድስት ተሽከርካሪዎችን ማስተናገድ ይችላል፡፡ በተጨማሪም ባለሁለት አቅጣጫ የብስክሌት ተጠቃሚዎች መስመር እና አምስት ሜትር የእግረኛ መንገድን ያካተተ እንደሆነም ኢንጂነሩ አስረድተዋል፡፡ የድልድዩ ዲዛይን ለ100 ዓመታት አገልግሎት እንዲሰጥ የታሰበ ስለሆነ ጥራት ያላቸዉንና ደረጃቸው ከፍ ያሉ የግንባታ ቁሳቁስ በሥራ ላይ እየዋሉ እነደሆነ ነው ኢንጂነሩ ያስረዱት፡፡

ድልድዩ 6 ሺህ ቶን ክብደት የመሸከም አቅም አለው፤ ኢንጂነር ፍቅረሥላሴ ግንባታው በተያዘለት ወቅት እንዲጠናቀቅ ቀንና ማታ እየሠሩ እንደሆነ አስረድተዋል።

ርእሰ መሥተዳድር አገኘሁ ተሻገር በድልድዩ ግንባታ በዘርፉ ልምድ ያካበቱ የውጪና የሀገር ውስጥ ባለሙታዎች እየተሳተፉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የፕሮጀክቱ ግንባታ ሲጠናቀቅ በሁሉም በኩል ባሕር ዳርን ከፍ እንደሚያደርጋት ገልጸዋል፡፡

በክልሉ ባለፉት በርካታ ዓመታት ያልተገነቡ መሠረተ ልማቶች በአሁኑ ወቅት እየተገነቡ መሆኑንም አንስተዋል። ርእሰ መሥተዳድሩ በተለይ በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች እየተገነቡ የሚገኙ የመንገድ ፕሮጀክቶች ከሦስተኛ ወገን ነፃ ለማድረግ ኅብረተሰቡ ትብብር እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

“በክልሉ የሚገነቡ መሠረተ ልማቶችን ከሁሉም ዘርፍ የተውጣጣ የክልሉ ካቢኔ ቅዳሜና እሑድ ምልከታ ያደርጋል፤ ለሚስተዋሉ ችግሮች ሁሉ መፍትሄ ይሰጣል” ብለዋል አቶ አገኘሁ፡፡

የሥራ ተቋራጮችም ምቹ ሁኔታዎች ሲፈጠሩላቸው ሙሉ አቅማቸውን አሟጠው መሥራት እንደሚጠበቅባቸው ርእሰ መሥተዳድሩ አሳስበዋል።

ዘጋቢ፡- ቡሩክ ተሾመ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡

Source link

Related posts

የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በትግራይ እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በተለያዩ ችግሮች ለተፈናቀሉ ወገኖች 15 ሚሊየን ብር ድጋፍ አደረገ

admin

የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ያሰለጠኗቸውን ተማሪዎች አስመረቁ

admin

በኢትዮጵያ የኮሮናቫይረስ ስርጭት ያለበትን ደረጃ ለማወቅ በሀገር አቀፍ ደረጃ ጥናት ሊካሄድ ነው።

admin