59.29 F
Washington DC
April 21, 2021
Satenaw Ethiopian News/Breaking News
Amharic News

በፈለገ ሕይወት ጠቅላላ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የአግልግሎት አሰጣጥ ጥራትን ለማሻሻል የሚያስችል የማነሳሻ (አይ ኬር ኢኒሼቲቭ) መርሐ ግብር ይፋ ተደረገ፡፡

በፈለገ ሕይወት ጠቅላላ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የአግልግሎት አሰጣጥ ጥራትን ለማሻሻል የሚያስችል የማነሳሻ (አይ ኬር ኢኒሼቲቭ) መርሐ ግብር ይፋ ተደረገ፡፡

ባሕር ዳር: የካቲት 29/2013 ዓ.ም (አብመድ)

“እኔም ይመለከተኛል” በሚል መሪ ሃሳብ ይፋ የተደረገው መርሐ ግብር ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን በመሥራት በሆስፒታሉ የሚሰጠውን አገልግሎት ጥራት ለማሻሻል ታሳቢ ያደረገ ነው ተብሏል፡፡ መርሐ ግብሩን ተግባራዊ ለማድረግ 2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር እንደሚጨርስ ታውቋል፡፡ ይህም በፈለገ ሕይወት ጠቅላላ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል፣ በክልሉ ጤና ቢሮ እና በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ይሸፈናል ተብሏል፡፡

መርሐ ግብሩን ያስጀመሩት የአማራ ክልል ምክትል ርዕስ መስተዳድር ፋንታ ማንደፍሮ (ዶክተር) ፈለገ ሕይወት ጠቅላላ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የአማራ ክልልና የአጎራባች ሕዝቦችን ለዘመናት ያገለገለ፣ የብዙ ሰዎችን ሕይወት ያተረፈ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ከዚህ በላይ የሰው ኃይልና ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ቢሟላ ብዙ ሥራ መሥራት የሚችል አንጋፋ ተቋም ነው ብለዋል፡፡

ሆስፒታሉን ለማዘመን ሕንፃዎች፣ መሳሪያዎች ትልቅ ሚና እንዳላቸው ሁሉ “እኔ ይመለከተኛል፣ እኔም የሰው ሕይወት ያሳስበኛል፣ ያስጨንቀኛል” የሚል ባለሙያ መፍጠር በጤና ዘርፍ እጅግ ወሳኝ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

ዛሬ ይፋ የተደረገው መርሐ ግብርም የጤናው ጉዳይ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል የሚመለከተው በመሆኑ የጋራ ሥራን የሚያነሳሳ እንደሆነ ነው የተናገሩት፡፡

ከዚህ በፊት በፈለገ ሕይወት ጠቅላላ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የነበረው የንጽሕና አጠባበቅ ችግር እየተሻሻለ መምጣቱን የጠቀሱት ምክትል ርዕስ መስተዳደሩ ሁሉንም አካላት መተባበር ሲችሉ ችግሩን ማስተካከል እንደሚቻል ማሳያ ነው ብለዋል፡፡ በፈለገ ሕይወት ጠቅላላ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታልና በሁሉም ሆስፒታሎች የሚሰሩ የሥራ ኀላፊዎችና ጤና ጥበቃ ቢሮው የጤናው ሴክተር እንዲሻሻል እየሠሩ ያሉትን ሥራ አድንቀዋል፡፡

ምክትል ርዕስ መስተዳድሩ የጤና ባለሙያዎች የሚቆሙ ሕይወቶች እንዲቀጥሉ በማድረግ እየሠሩት ለሚገኙት ሥራ ትልቅ ምስጋና ይገባቸዋልም ብለዋል፡፡

የኢፌዴሪ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ዓለምፀሐይ ጳውሎስ እንደገለጹት ሆስፒታሎች በተሻለ ጥራት አገልግሎት እንዲሰጡ የሚያስችሉ የማነሳሻ መርሐ ግብሮች እየተካሄዱ ነው፡፡

“እኔም ይመለከተኛል” በሚል መሪ ሃሳብ የተዘጋጁ የማነሳሻ መርሐ ግብሮች በሀገር አቀፍ ደረጃ በ24 ሆስፒታሎች ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡

መርሐ ግብሩ የአገልግሎት አሰጣጥና የመምራት ክህሎት እንዲሁም የገቢ አሰባሰብ ሥርዓትን የሚያዘምን እንደሆነ ሚኒስትር ዴኤታዋ ገልጸዋል፡፡ የሁሉም ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ አሁን ካለበት አሠራር በመውጣት ኅብረተሰቡን ማርካት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

የአማራ ክልል ጤና ጥበቃ ቢሮ ኀላፊ መልካሙ አብቴ (ዶክተር) መርሐ ግብሩ በሆስፒታሉ የሚታየውን ችግር በመለየት ማን፣ እስከ መቼ ለችግሮች መፍትሔ መስጠት እንዳለበት አቅጣጫ የሚያስቀምጥ እና ተግባሩ በበጀት የሚደገፍ ነው ብለዋል፡፡ በተለይም በሆስፒታሎች የህክምና ጥራትን ለማስጠበቅ፣ባለሙያውን ውጤታማ ለማድረግ፣ የአስተዳደሩንና የቦርድ አባላትን የበለጠ መፍትሔ እንዲያፈላልጉ የሚያግዝ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡

መርሐ ግብሩ ይፋ ከሆነባቸው በደብረ ብርሃን፣ ደሴና ጎንደር ሆስፒታሎች የተሻለ አፈጻጸም እየታየ እንደሚገኝም ኀላፊው ተናግረዋል፡፡ ጤና ጥበቃ ቢሮም የመርሐ ግብሩን አፈጻጸም በልዩ ሁኔታ እንደሚከታተለውና እንደሚደግፈው አስታውቀዋል፡፡

ዘጋቢ፡- አዳሙ ሽባባው

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡

Source link

Related posts

ባልደራስና የአብን የትብብር ስምምነት ተፈራረሙ

admin

አለም ዙሪያ ለምትገኙ፣ በየሀገሩ ለተደራጃችሁ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ፡-

admin

“ኢትዮጵያዊነት የማይደበዝዝ ይልቁንም በይበልጥ የሚደምቅና የሚፈካ የጋራ ማንነታችን ሊሆን ይገባል” ርእሰ መሥተዳድር አገኘሁ ተሻገር

admin