43.27 F
Washington DC
March 1, 2021
Satenaw Ethiopian News/Breaking News
Amharic News

‹‹በግፍ አይዘምቱም ከተዘመተባቸው አይረቱም›› | የአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት

‹‹በግፍ አይዘምቱም ከተዘመተባቸው አይረቱም››

ባሕር ዳር፡ የካቲት 07/2013 ዓ.ም (አብመድ) ‹‹ማስተማሪያም አታድርገኝ ማስተማሪያም አትንሳኝ›› የሚለው ድንቅ የኢትዮጵያዊያን አባባል ለኢትጵያ ጠላቶች አልተገለጠላቸውም፡፡ የኢትዮጵያ ጠላቶች ከተሸናፊዎቹ አይማሩም፤ እሳት እንደሚያቃጥል እያዩ ወደ እሳት ይወርዳሉ፣ በእሳት ተቃጥለው ሳይመለሱ ይቀራሉ፡፡

ኢትዮጵያ ለማሸነፍ ብቻ የተፈጠረች ነጻነት ያለው ሕዝብ ያለባት ነጻ ሀገር መሆኗን እያወቁ አሸናፊነቷን ማመን ይቸግራቸዋል፡፡ ለማሸነፍ ሌላ እድል ይሞክራሉ፣ የኢትዮጵያን ታሪክ ከፍ አድርገው እነርሱ ከታሪክ ይወርዳሉ፣ ኢትዮጵያን የነካ ሁሉ መዝገቡ ጥቁር ይሆናል፣ ኢትዮጵያ ደግሞ መዝገቧ የወርቅ ይሆናል፡፡

ሊቃውንት ‹‹ኢትዮጵያዊያን በግፍ አይዘምቱም ከተዘመተባቸው አይረቱም›› ይላሉ፡፡ ኢትዮጵያን የነኳት ይወድቃሉ፣ በክፉ የተመኟት ያልቃሉ፣ በክፉ ያሰቧት አስቀድመው ይሸበራሉ፤ ይናወጻሉ፤ ከማዕልት እስከ ሌሊት ከሌሊት እስከ ማዕልት ሳይቋረጥ የሚፀለይባት ሀገር ናት ኢትዮጵያ፡፡ ይህ ፀጋ ለማንም ሀገር አልተሰጠም ከኢትዮጵያ ውጭ፤ የመነኮሳቱ ፀሎት፣ የቅዱሳኑ ምህላ፣ የሼሑ ዱዓ ኢትዮጵያን ከምንም ነገር ጠብቋት ይኖራል፡፡ ዓለም ላይ በአሸናፊነት የሚሄድ ኢትዮጵያዊ ብቻ ነው፡፡ ነጻ ሀገር ነጻ ሕዝብ ነውና፡፡ ኢትዮጵያዊነት እሳት ነው፡፡ ቢጠጉት የሚያቃጥል፣ ቢይዙት የሚቀቀል፡፡

ኢትዮጵያ ለምድር የተበረከተች ልዩ ስጦታ ናት፡፡ በምድር የሚተካላት ያለ አይመስልም፡፡ ስጋ ከደም ተለይቶ እንደማይኖር ሁሉ ኢትዮጵያዊያንም ከኢትዮጵያዊነት ተለይተው መኖር አይችሉም፡፡ ኢትጵያዊነት እስትንፋስ፣ ኢትዮጵያዊነት መልካም ልሳን፣ ኢትዮጵያዊነት ቅዱስ መንፈስ፣ ኢትዮጵያዊነት ግርማ ሞገስ፣ ኢትዮጵያዊነት የማይደፈር የማይገሰስ፣ ኢትዮጵያዊነት በምርምር የማይደረስ ረቂቅ ነው፡፡

ኢትዮጵያዊያን ፈጣሪ ይሰማቸዋል፡፡ ይጠብቃቸዋል፣ ያቅባቸዋል፣ ጠላቶቿን ፈጥኖ ያስገዛለቸዋል፣ ሀገራቸውን ዳሯን እሳት መሀሏን ገነት ያደርግላቸዋል፡፡ ኢትዮጵያ የአፍሪካ የነጻነት ሰንደቅ፣ የአማኒያን ሀገር፣ ከሁሉም የቀደመች፣ ሚስጥሯ ያልተደረሰባት፣ የባዕድ ንጉሥ ግዛት የማታውቅ፣ ራስ ገዝ፣ ነጻ ምድር ነጻ ሕዝቦች ያሉባት ናት፡፡

ኢትዮጵያ በዓለም ገፅ ከጠፉ የጥቁር ግዛቶች የተረፈች ብቸኛ የተስፋ ችቦ ናትም ይሏታል፡፡ የአፍሪካዊያን አባቶችና አያቶች በአፍሪካ አቋቁመውት ለነበረው ሥርዓተ መንግሥት ሐውልት ነችም ብልዋታል ኢትዮጵያን፡፡

ኢትዮጵያን ለመውረር፣ ሕዝቦቿን ለማስገበር፣ ታሪኳን ለመመዝበር፣ ነጻነቷን ለመገርሰስ፣ ፀጋዋን ለመውረስ ኃያሌ ጠላቶች ተመዋል፤ ጦርነት ተደርጓል፤ አንዱም ያሰበውን አላሳካም፤ የኢትዮጵያ ጠባቂዎች ጀግና ወታደሮች ብቻ አይደሉም፤ ኢትዮጵያዊያን አብዝተው የሚያምኑት ጣላቶቿ በውል የማይረዱት ረቂቅ ጠባቂ አላት፡፡ ረቂቁን ጠባቂ የሚያሸንፈው የለም፤ የኢትዮጵያ ጠላቶች የሚታዩትን ጀግና ሠራዊትም ማሸነፍ አይቻላቸውም፡፡

ከክርስቶስ ልደት በፊት በ336 ዓ.ዓ በግሪክ ነግሦ የነበረው ታላቁ እስክንድር (አሌክሳንደር) ግዛቱን ያሰፋ ነበር፡፡ ብዙ ሀገራት በጦር፣ ብዙዎች ደግሞ ዝናውን እየሰሙ አስቀድመው ይገብሩለት ነበር፡፡ ጳውሎስ ኞኞ “ኩዌንቱስ ኩርቱውስ” የተባለውን ደራሲ ዋቢ አድርገው እንደጻፉት ‹‹ወጣቱ ንጉሥ ለጦርነት ሲነሳ የምወረው ግብፅን ብቻ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያንም ጭምር ነው›› አለ፡፡ ታላቁ እስክንድር በወኔ እንደተነሳ ግብፅን እና ሌሎች ሀገራትን አስገበረ፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ግን መግባት አልተቻለውም፡፡ እስክንድር ስለ ኢትዮጵያዊያን ጀግንነትና አይደፈሬነት አስቀድሞ ሰምቶ ነበርና ከኢትዮጵያዊያን ጋር ለመግጠም ፈራ፡፡ ስለኢትዮጵያዊያን የሚነገረው ጀግንነትም አውነት ስላልመሰለው ራሱ እስክንድር ኢትዮጵያ ውስጥ ገብቶ ለመሰለል ተነሳ፡፡

‹‹እስክንድር ከምርጥ የጦር አለቆቹ ጋር ሆኖ ሁሉም ተራ ሰው መስለው ለመሰለል ወደ ኢትዮጵያ ገቡ፡፡ ኢትዮጵያዊቷ ንግሥት ህንደኬም አሌክሳንደር ተራ ሰው መስሎ ወደ ኢትዮጵያ ለመሰሰለል መግባቱን ሰማች፡፡ ንግሥቲቱ እነኛን እንግዳ ተራ ሰዎች ወደ ቤተመንግሥቷ አስጠርታ እንዲህ አለች ‹ዓለምን አንቀጥቅጠህ የገዛህ ታላቁ እስክንድር ሆይ ዛሬ በሴት እጅ ተይዘሃል› ንጉሡ በመታወቁ ደንግጦ ጥበቧን አደነቀ፡፡ የኢትዮጵያን ሠራዊት ብዛትና ሰላዮቿን አደንቆ‹ ንግሥት ሆይ የተነገረኝ ሁሉ እውነት ነው፡፡ ይህ በጦር የማይፈታ ሕዝብ ነውና እኔና አንቺ ተጋብተን ዓለምን እንግዛት›› አላት፡፡

አዎ እውነት ነው ኢትዮጵያዊ በጦር አይፈታም፣ በጠላት አይረታም፣ ትጥቁን አይፈታም፣ የነኳት ይወድቃሉ፣ ይጨነቃሉ፣ ይጠበባሉ እንጂ ከቶውንም አያሸንፏትም፡፡

የሮማው አውግስጦስ ቄሳርም ኢትዮጵያን ያስገብር ዘንድ አሰበ፡፡ በአውሮፓ፣ በኢሲያና በሌሎች አህጉራት ያሉትን ሀገራት አስገበረ፡፡ በሥልጣኑ ስርም አደረጋቸው፡፡ ከክርስቶስ ልደት በፊት በ29 ዓ.ዓ አይሎስ ጋሎስ በሚባል የጦር አዛዥ የሚመራ በሺህ የሚቆጠር ሠራዊት ወደ ኢትዮጵያ ላከ፡፡ ጦሩ እግረኛና ፈረሰኛ ነበር፡፡ በዚያ ዘመን የአክሱም መንግሥት ገናና ነው፡፡ የኢትዮጵያ የባሕር ኃይል እንደማይደፈር አይሎስ ጋሎስ አስቀድሞ ተገነዘበ፡፡ ጦሩንም በግብጽና በዛሬው ሱዳን አሻግሮ በአክሱም ያለውን የኢትዮጵያን መንግሥት ለመውጋት ገሠገሠ፡፡ ይሄን የሠሙት ኢትዮጵያዊያን ጦራቸውን ሰብቀው የአውግስጦስ ቄሳርን ጦር ከወሰናቸው ማዶ አቆሙት፡፡ ጦርነት ተካሄደ፡፡ እኒያን ግንባራቸው እንደ እሳት የሚፋጅ፣ ክንዳቸው እጥፍ የማይል ኢትዮጵያዊያንን ወደኋላ የሚመልሳቸው ጠፋ፡፡ ውጊያው ጦፈ፤ ከሮም የመጣው ጦር እየመነመነ ሄደ፡፡ በየጥሻው የአራዊት ራት እየሆነ አለቀ፡፡ ሮምና ንጉሡ፣ ሹማምንቱ ሁሉ ተጨነቁ፡፡ ‹‹ሳይደርሱባቸው እየደረሱ ይመለሳሉ እየቀመሱ›› እንዳለ ሳይደርሱበት የደረሰው የሮም ጦር እርቅ ይሆን ዘንድ ለመነ፡፡ ይቅርታ አደረጉለት፡፡ የተረፈው ጦርም ወደ ሀገሩ ተመለሰ፡፡ የሮም ነገሥታት ሽንፈታቸው አንገበገባቸው፡፡ ገናናው መንግሥታቸውና የሚፈራው ሠራዊታቸው በጀግኖች ኢትዮጵያዊያን አፈረ፡፡

ታሪካቸውን ያድሱ ዘንድ ተነሱ፡፡ ዓመተ ዓለም አልቆ ዓመተ ምህረት መጣ፡፡ የዓለም አካሄድ ሁሉ ተቀየረ፡፡ ዘመን አንድ ብሎ ይቆጠር ጀመር፡፡ በ54 ዓ.ም በሮም የነገሠው ኔሮ ኢትዮጵያን ለማስገበር ፎክሮ ተነሳ፡፡ የኔሮ አማካሪዎችም ኢትዮጵያዊያን ሀገራቸውን የማያስደፍሩ ጀግኖች መሆናቸውን ነገሩት፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ጦር መላክ የባሰ ውርደት እንደሚሆን አስጠነቀቁት፡፡ ከአባቶቹ ሽንፈት ያልተረደው ንጉሥ አሻፈረኝ አለ፡፡

ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያዊያንን የሚሰልል ቡድን ላከ፡፡ ጳውሎስ ኞኞ የሮማውን ፀሓፉ ሴኔካን ዋቢ አድርገው እንደጻፉት ‹‹ኔሮ የአባቶቹን ምኞት ለመፈፀም የዓባይን ምንጭ የሚፈልጉ ናቸው ብሎ ለኢትዮጵያው ንጉሥ ደብዳቤ ፅፎ ሰላዮቹን ወደ ኢትዮጵያ ላከን፡፡ የተላክነው ሰላዮች ኢትዮጵያ ውስጥ ከርመን ስንመለስ ሕዝቡ ጦረኛ መሆኑንና በአሁኑ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ ጦር መላክ እንደማያዋጣ ነገርነው፡፡ ሀገሪቱ ግን እጅግ በጣም ለም ናት አልነው›› ሲል ከትቧል፡፡

ኔሮ ግን የሰላዮችን ሀሳብ አልተቀበለም፡፡ አባቶቹ ያልቻሉትን ኢትዮጵያን የማስገበር ምኞት እሱ እንደሚችል ተማመነ፡፡ ካምቤይስ በሚባል የጦር መሪ የሚመራ ጦር ወደ ኢትዮጵያ ላከ፡፡ ጀግንነታቸውን ቀምሶ አየው፡፡ ጦሩ እንዳልነበር ሆነ፡፡ ወሬ ነጋሪ ታጣ፡፡ ተደመሰሰ፡፡

ሌላ ዘመን አልፎ ሌላ ዘመን መጣ፡፡ በተደጋጋሚ ሞክሮ ያትረሳካላት ጣልያን ሌላ ዕድል መሞከር ፈለገች፡፡ ዳግማዊ ምኒልክ በአስፈሪው ዙፋን ተቀምጠውበታል፡፡ ፍቅርና ትህትና የሚቀድማቸው ንጉሡ ሀገራቸው ከሌሎች ሀገራት ጋር በፍቅር ትኖር ዘንድ አጥብቀው ይሻሉ፡፡ ጣልያንም ከኢትዮጵያ ጋር የይስሙላ ፍቅር ጀምራለች፡፡ እምዬ እና እቴጌ ፍቅሩ የእውነት መስሏቸዋል፡፡ ጣልያን ግን አካሄዷ ሌላ መንገድ ነበረው፡፡ የውጫሌው ውል መዘዝ አመጣ፡፡ የጣልያን ድብቅ መንገድ እንደታወቀ ታሻሽል ዘንድ ተጠየቀች፡፡ በመልዕክተኞቿ ፍቅር፣ በወታደሮቿ ጦር የምትልከው ጣልያን አልመለስም አለች፡፡ አስፈሪው ቀን መጣ፡፡ ጣልያን ወታደሯን ወደ አስፈሪዋ ምድር ላከች፡፡ በሌሎች ሀገራት በድል የተንበሸበሸው የጣልያን ወታደር በኢትዮጵያ ላይም እንደሚደግመው ተገምቷል፡፡ ጊዜው እየደረሰ መጣ፡፡ የኢትዮጵያ አርበኞች እንደ አንድ ልብ መካሪ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ተሰባስበው፣ በኢትዮጵያዊነት ተሳስረው እየተጠባበቁ ነው፡፡ ጊዜው ደረሰ፡፡

ያን ጊዜ አፈወርቅ ገብረ ኢየሱስ ዳግማዊ አጤ ምኒልክ በሚለው መጽሐፋቸው ‹‹ነገሩ እያደረ በኢጣልያ ከበደበት በጥቂት ጦር እንገላገላን ያ ሀበሻ ጦር አይቆምልንም ሲል የነበረው ድሮ ጨነቀው፡፡ ጠበበው፡፡ ውኃ ተባሕር ወዲያ በመርከብ ተጭኖ መጥቶ እንዳረቂ በብርጭቆ ተለክቶ ተናኝቶ የበቅሎ፣ የፈረስ ገለባና ገፈራ ተፈረንጅ አገር መጥቶ ጫማው ልብሱ ትንባሆው ሳይቀር ተባሕር ማዶ መጥቶ ተሀበሻ ጋር ለመዋጋት እጅግ የጨነቀ ነገር ሆነበት›› በማለት ከትበዋል፡፡

የሆነው ሆነና ጦርነቱ አልቀረም የፈራው አስቀድሞ የተረበሸው የጣልያን ወታደር ጦርነቱን ለማድረግ ቀረበ፡፡ ‹‹ጀኔራል ባራቴሪ ተበላዩ የተሸመው ጄኔራል ጀኔራል ባልደሴራ ሳይደርስ ተሻምቶ መዋጋት ፈለገ፡፡ ለዚያ ወዲያማ በከንቱ ነው፣ የኢትዮጵያ አምላክ መቸም የኢጣልያን ሁሉ ነገር እንደ ጥቅመ ሠናዖር ኅንጻ እንደ ባቤል( ባቢሎን) ቋንቋ አደረገው›› ሲሉም ጽፈዋል አፈወርቅ ገብረ ኢየሱስ፡፡

‹‹ጄነራል ባራቴሪ አቅሙን ሳያውቅ ጦሩን ሳይቆጥር ያን ሁሉ ሰው አላበሰው፡፡ ገፍቶ ከአንበሳ አፍ ጣለው›› ዓለም የጠበቀችው ሳይሆን ያልጠበቀችው ሆነ፡፡ የጣልያን ጦር ተሸነፈ፡፡ ምድር ተገረመች፡፡ ኃያላኑ ደነገጡ፡፡ ሮም ጨለመች፡፡ ኢትዮጵያ አበራች፡፡ ከፍም አለች፡፡ የጥቁርን ዘር በሙሉ በብርሃን አንዲራመድ አደረገች፡፡

ሞት ያላስተማራቸው፣ መሸነፍ ያልሰለቻቸው ጣልያኖች ለ40 ዓመታት ሌላ ዝግጅት አድርገው በዘመነ ግርማዊ ቀዳማዊ ኀይለ ሥላሴ ዘመን ተመለሱ፡፡ የማያቋርጥ ውጊያ ተደረገ፡፡ ዓምስት ዓመታት በእሳት ላንቃ ተገረፈች፡፡ በማይታጠፍ ጦር ተወጋች፡፡ በኢትዮጵያ የሆነው ሁሉ አልቻል አላት፡፡ የቀደመውን ሽንፈት ተቀብላ ተመለሰች፡፡

ኢትዮጵያዊያን ‹‹አትንኩን›› ይላሉ ከነኳቸው ክንዳቸውን ያነሳሉ፣ በግርማቸው ይጥላሉ፣ በጦራቸው ይገድላሉ፣ በኃይላቸው ድንበር ያስከብራሉ፣ ጠላት ያሳፍራሉ፡፡ በ1298 ዓ.ም የባሕር ላይ ጉዞ እንደጀመረ የሚነገርለት ተጓዡ ማርኮ ፓውሎ ‹‹ልታውቁት የሚገባ ነገር አለ፤ በአበሻ ምድር ምርጥ የሆኑ ወታደሮች አሉ፤ አብዘኛዎቹ ወታደሮችም ፈረሰኖች ናቸው፤ ፈረስም በብዛት አላቸው፤ በዚህም ምክንያት ተዋጊዎችና ኃይለኞች ናቸው፤ በህንድ ሀገር ስላሉትና ከምናደንቃቸው እውቅ የህንድ ወታደሮችም የሚበልጡ ናቸው›› ብሏል፡፡

ኢትዮጵያ በግፍ አትዘምትም፣ ለግፍ ለዘመተ አትታጠፍም፡፡ የአሁኖቹ የግፍ ዘማቾችም እንደቀደሞቹ ይሆናሉ፡፡ ኢትዮጵያን እሳት ለመለብለብ በዳር የቀረቡት እሳቱ አስቀድሞ እነርሱውን ይበላቸዋል፡፡ ለምን ካሉ ኃይሏ ብርቱ ነውና፡፡ ግን ደግሞ የጠነከረ አንድነት፣ የማይናወፅ ኢትዮጵያዊነት ያስፈልገናል፡፡ በሰርጋችን ቀን ወደጅ በሀዘናችን ቀን ጠላት የሚሆኑን አንድ ሆነን እናሳፍራቸው፡፡ አንድነት ለኢትዮጵያዊያን የተሰጠ የቆዬ ማንነት ነውና፤ ጳውሎስ ኞኞ ኢትዮጵያና የኢጣሊያ ጦርነትን እና አፈወርቅ ገብረ ኢየሱስ ዳግማሚ አጤ ምኒልክን በምንጭነት ተጠቅሜያለሁ፡፡

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡

Source link

Related posts

በዘላቂ የኑሮ ዋስትና ማረጋገጥ ፕሮግራም 230 ሺህ ቤተሰቦች ተጠቃሚ ሆነዋል

admin

በቻይና በትምህርት ላይ ከሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ጋር በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት ተካሄደ

admin

በክልሉ 13 ዞኖች የወባ በሽታ በስፋት እንደሚገኝ የኦሮሚያ ጤና ቢሮ አስታወቀ

admin