በገቢዎች ሚኒስቴር የኮምቦልቻ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የሰጣቸው ስልጠና በታክስ አስተዳደሩ እየተፈጠሩ ያሉትን የወንጀል ድርጊቶች ለመከላከል እንደሚረዳቸው ሕግ አስከባሪዎች ተናገሩ።
ባሕር ዳር ፡ የካቲት 07/2013 ዓ.ም (አብመድ)
በገቢዎች ሚኒስቴር የኮምቦልቻ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ከባለድርሻ አካላት ጋር በገቢ ግብር አዋጅ፣ በታክስ አስተዳደር አዋጅ፣ በታክስ ዙሪያ በሚፈጸሙ ወንጀሎች እንዲሁም በጉሙሩክ አዋጅና በሚፈጸሙ የኮንትሮባንድና የንግድ ማጭበርበር ዙሪያ ስልጠና አካሂዷል፡፡
ስልጠናው በምሥራቅ አማራ ለሚገኙና ከተመረጡ አካባዎች ለመጡ የፖሊስ፣ የአቃቢ ሕግ እና የዳኞች አካላት የተሳተፉበት ነው፡፡ በገቢዎች ሚኒስቴር የኮምቦልቻ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ሥራ አስኪያጅ አቶ ያረጋል ኃይሉ፣ በታክስ አስተዳደሩ እየተመዘገቡ ያሉ የሚበረታቱ ስኬቶች የመንግሥትን የፋይናንስ አቅም በማጠናከር የዜጎችን ኑሮ ለማሻሻል የሀገርን ደኅንነት ለማስከበርና በምጣኔ ሀብት ራስን ለመቻል በሚደረገው ጥረት የአሠራር የአደረጃጀትና ከገቢም አንጻር መሻሻል መኖሩን አንስተዋል፡፡
ነገር ግን አንዳንድ ሕገ-ወጥ ነጋዴዎች የግብይት ሥርዓቱን እንደሚረብሹ ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል፡፡ ችግሩ በጤናማ የግብይት ሥርዓቱ ላይ ጫና እየፈጠረ ስለመሆኑም ጠቅሰዋል፡፡ ይህን ችግር የገቢዎች መሥሪያ ቤት ብቻውን ሊፈታው ስለማይችል ለአጋር አካላት ግንዛቤ መፍጠር አስፈልጓል ብለዋል፡፡
በገቢዎች ሚኒስቴር የሕግ ተገዢነት ዘርፍ ሚኒስቴር ድኤታ አቶ ዘመዴ ተፈራ በታክስ አስተዳደር ስርዓቱ ውስጥም ከታክስ በመሸሽና ታክስን በመሰወር ወይም በማጭበርበር በርካታ ወንጀሎች ይፈጸማሉ ብለዋል፡፡
ወንጅሉን ጥቂት አካላት የሚሠሩት ቢሆንም እያደገ ከሄደ ሀገርን እንደ ሀገር ብሎም ማኅበረሰቡን ሊጎዱ የሚችሉ ድርጊቶች ናቸው ብለዋል፡፡ በዘርፉ ሕግ እንዲከበር አጋር አካላት በታክስ አስተዳደሩ ምንነት፣ ድርጊቶችን አረዳድ ምን እንደሚመስል በንድፈ ሀሳብና በተግባር እውቀት ለማስጫበጥ የሚደረገው አንዱ አካል መሆኑን ነው የገለጹት፡፡
ከችግሩ ለመውጣትም ግብር ከፋዩ፣ የመንግሥት አስፈፃሚ አካላት በተለይም በሕግ ማስከበር ሥራ ላይ ያሉ የፖሊስ፣ አቃቢያን ሕግና ዳኞች በእጅጉ ወሳኝ ናቸው ብለዋል፡፡
በታክስ አስተዳደሩ እየተፈጠሩ ያሉትን የወንጀል ድርጊቶች አስመልክቶ የግንዛቤ ማስጨበጫ የተሰጣቸው ተሳታፊዎችም ምክክሩ በእውቀት ላይ ተመስርቶ ለመሥራት እንደሚያግዛቸው ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ:– ደጀን አምባቸው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡