43.27 F
Washington DC
March 1, 2021
Satenaw Ethiopian News/Breaking News
Amharic News

በደብረ-ብርሃን ጊዜያዊ መጠለያ የሚገኙ ተፈናቃዮች በዘላቂነት የሚቋቋሙበት ሁኔታ እንዲመቻችላቸው ጠየቁ፡፡

በደብረ-ብርሃን ጊዜያዊ መጠለያ የሚገኙ ተፈናቃዮች በዘላቂነት የሚቋቋሙበት ሁኔታ እንዲመቻችላቸው ጠየቁ፡፡

ባሕር ዳር፡ የካቲት 04/2013 ዓ.ም (አብመድ) በማንነታቸው ምክንያት ከተለያዩ ክልሎች የተፈናቀሉ 16 ሺህ 130 የአማራ ተወላጆች በሰሜን ሸዋ ዞን እንደሚገኙ ከዞኑ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ተጠሪ ጽሕፈት ቤት የተገኘ መረጃ ያመላክታል፡፡ ለተፈናቃዮች የሚደገረው ድጋፍ ሳይቆራረጥ እንዲደርስ እየተሠራ ቢሆንም ዘላቂ መፍትሔ እንዲሰጣቸው ተደጋጋሚ ጥያቄ ማቅረባቸውን በጽሕፈት ቤቱ የቅድመ ማስጠንቀቂያ የሎጂስቲክስ ባለሙያው ዘሪሁን ደምሴ ተናግረዋል፡፡

በ2012 ዓ.ም ጃዋር መሀመድ “ተከብቤያለሁ” ማለቱን ተከትሎ በኦሮሚያ ክልል በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ከዶዶላ ተፈናቅለው በደብረብርሃን ጊዜያዊ መጠለያ የሚገኙ ወገኖችን አብመድ አነጋግሯል፡፡ ተፈናቃዮቹ የደብረብርሃን ከተማ ሕዝብ እየተንከባከባቸው መሆኑን አንስተዋል፡፡ መንግሥትም ድጋፍ እያደረገላቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ይሁን እንጂ የሚደረግላቸው ድጋፍ ከፍላጎታቸው ጋር አለመመጣጠኑን እና በተጠለሉበት ቦታ ከፍተኛ ቅዝቀዜ መኖሩን አንስተዋል፡፡ ያለሥራ መቆየታቸው ሥነልቦናዊ ጫና እያሳደረባቸው መሆኑን ያነሱት ተፈናቃዮቹ በዘላቂነት መቋቋም የሚችሉበት ሁኔታ እንዲመቻችላቸው ጠይቀዋል፡፡ በዘላቂነት መቋቋም በሚችሉበት ሁኔታ ላይም ከአማራ ክልል መንግሥት ጋር ውይይት መደረጉን ተናግረዋል፡፡ ወደ ቀያቸው ለመመለስ የተረጋገጠ ሰላም ሊኖርና ዋስትና ሊሰጣቸው እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡

የሕግ የበላይነት በአስተማማኝ መልኩ ከተረጋገጠ ለመመለስ ዝግጁ መሆናቸውን የተናገሩ አስተያዬት ሰጪዎች በየጊዜው የሚፈጠር የጸጥታ ችግር ስጋት እንደሆነባቸው አንስተዋል፡፡

በሌላ በኩል በወቅቱ በደረሰባቸው ጥቃትና የስነልቦና ጫና ምክንያት ወደቀያቸው መመለስ እንደማይፈልጉ የተናገሩም አሉ፡፡ የአማራ ክልል መንግሥት ለመቋቋሚያ የሚሆን መሠረታዊ ነገሮችን እንዲያመቻችም ጠይቀዋል፡፡

የክልሉ አደጋ መከላከል ምግብ ዋስትና ፕሮግራሞችና ልዩ ድጋፍ የሚሹ አካባቢዎች ማስተባበሪያ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘላለም ልጃለም የፌዴራል መንግሥቱ ከክልሎች ጋር በትኩረት ሊሠራ ይገባል ብለዋል፡፡ ከማኅበረሰቡ ጋር ተቀላቅለው መኖር የሚፈልጉ ተፈናቃዮች ቢኖሩም በሕጋዊ ምክንያት ተፈናቃዮች ወደየቀያቸው መመለስ አለባቸው ብለዋል፡፡ ይሕም ማንኛም ሰው በየትኛውም ቦታ ተንቀሳቅሶ ሀብትና ንብረት አፍርቶ የመኖር ሕገ-መንግሥታዊ መብትን ለማስጠበቅ የታሰበ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ለዘመናት የገነቡት ማኅበራዊ ካፒታል እንዲጠበቅና የነበራቸው ጠንካራ መስተጋብር እንዲቀጥል ማድረግ እንደሚጠበቅም አስታውቀዋል፡፡

‹‹አማራ በአንድ ጠባብ ሜዳ የታጠረ እንዲሆን ማሰብ አባቶቻችን ዋጋ ከፍለው የታገሉለትን ታሪክ አሳልፎ እንደመስጠት ይቆጠራል›› ያሉት ኮሚሽነሩ የሚመለሱበትን ሁኔታ ለማመቻቸት በተለይ ከኦሮሚያ ክልል መንግሥት ጋር ውይይት መደረጉን ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን አስተማማኝ ሰላም አለመረጋገጡን አመላክተዋል፡፡ በጸረ አማራ ኃይሎች ላይ ርምጃ እስካልተወሰደ ድረስ የክልል መንግሥታት ግንኙነት ማድረጉ መፍትሔ እንደማያመጣም ጠቅሰዋል፡፡

የኦሮሚያ ክልል መንግሥት በውስጡ ያለውን ችግር መፍታት ይጠበቅበታል ያሉት ኮሚሽነር ዘላለም አስተማማኝ ሰላም እስኪሰፍን ድረስ ለተፈናቃዮቹ ድጋፍ ማድረጉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል፡፡

ኮሚሽነሩ እንዳሉት ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ ከኦሮሚያ፣ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ከደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እንዲሁም ከትግራይ ክልሎች የተፈናቀሉ 277 ሺህ የአማራ ተወላጆች በክልሉ ድጋፍ እየተደረገላቸው ነው፡፡ የተሳሳተ ትርክትና የሴራ ፖለቲካ ለችግሩ መነሻ መሆኑን ያነሱት አቶ ዘላለም የክልል መንግሥታትን መልካም ግንኙነት ለማጠናከር የተጀመረው እንቅስቃሴ ችግሩን ለመፍታት ተስፋ እንዳለው አመላክተዋል፡፡

ጉዳዩን አስመልክቶ የኦሮሚያ ክልል የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮችና የሠላም ሚኒስቴር ማብራሪያ እንዲሰጡን በስልክ ለማናገር ደውለን ስላልተመለሰልን ያደረግነው ጥረት አልተሳካም፤ መረጃውን እንዳገኘት የምናደርስ ይሆናል፡፡

ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡

Source link

Related posts

‹‹የአድዋ ድል ለኢትዮጵያዊያን ብቻ ሳይሆን ለመላው አፍሪካ የይቻላልን ስነ-ልቦና ያጎናጸፈ ነው›› የኢትዮጵያ አንድነት አርበኞች ግንባር

admin

አበሻ የማይለምደው የለም:-  የወገንን እልቂት የዘር ጭፍጨፋንም ለምዶት ቁጭ አለ…?!? (መርእድ እስጢፋኖስ)

admin

ሲዋጉና ሲያዋጉ የነበሩ 18 ከፍተኛ መኮንኖች በቁጥጥር ስር ዋሉ

admin