76.62 F
Washington DC
June 15, 2021
Satenaw Ethiopian News/Breaking News
Amharic News

በአማራ ክልል የጎርፍ አደጋ ተጋላጭነትን ለመቀነስ እየሠራ መሆኑን የክልሉ አደጋ መከላከል፣ ምግብ ዋስትና ፕሮግራም እና ልዩ ድጋፍ የሚሹ አካባቢዎች ማስተባበሪያ ኮሚሽን ገለጸ፡፡

በአማራ ክልል የጎርፍ አደጋ ተጋላጭነትን ለመቀነስ እየሠራ መሆኑን የክልሉ አደጋ መከላከል፣ ምግብ ዋስትና ፕሮግራም እና ልዩ ድጋፍ የሚሹ አካባቢዎች ማስተባበሪያ ኮሚሽን ገለጸ፡፡

ባሕር ዳር፡ ሰኔ 02/ 2013 ዓ.ም (አሚኮ) በባለፈው ዓመት የክረምት ወቅት ከመደበኛ በላይ ዝናብ መጣሉን ተከትሎ በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በደረሰ የጎርፍ አደጋ በሰው፣ በሰብል፣ በእንስሳትና በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱ ይታወሳል፡፡ ጣና ሐይቅ ሞልቶ ባስከተለው የጎርፍ መጥለቅለቅም ሁለት የፎገራ ወረዳ ቀበሌዎች፣ አራት የሊቦከምከም ወረዳ ቀበሌዎችና አምስት የምሥራቅ ደንቢያ ወረዳ ቀበሌዎች መጎዳታቸውን አሚኮ ዘግቦ ነበር፡፡

በተመሳሳይ በሰሜን ሸዋ ዞን ልዩ ልዩ አካባቢዎች ጉዳት መድረሱ ይታወሳል፡፡ ርብ፣ አለማየሁና ጉማራ ወንዞች በሚገኙባቸው የፎገራና ሊቦከምከም ወረዳ አካባቢዎች ተደጋጋሚ አደጋ ይከሰታል፣ ሸዋሮቢትና ወልድያ ከተሞችን ጨምሮ በአማራ ክልል ተደጋጋሚ አደጋ የሚከሰትባቸው አካባቢዎች ናቸው፡፡

በፎገራ ወረዳ ብቻ ስምንት ቀበሌዎች በርብ፣ በአለማየሁ፣ በጉማራና በጓንታ ወንዞች ምክንያት እንዲሁም ጣና ሞልቶ ወደኋላ በመፍሰሱ በየዓመቱ ለጎርፍ አደጋ ይጋለጣሉ፡፡

በወረዳው አሚኮ ያነጋገራቸው የዋገጠራ ቀበሌ ነዋሪዎች ችግሩ በመጪው ክረምት ሊከሰት እንደሚችል ስጋት አላቸው፤ ከአሁኑ የጣና ሐይቅ መሙላት እንደጀመረም ተናግረዋል፡፡ የጉማራ ወንዝ የሚፈጥረው ችግር በጊዜ እልባት ባለመሰጠቱ ነዋሪዎቹን ስጋት ላይ እንደጣላቸው ነው የተናሩት፡፡ የወልድያ ከተማ ነዋሪዎችም በመጪው ክረምት የጎርፍ አደጋ ሊከሰት እንደሚችል ስጋታቸውን ለአሚኮ ተናግረዋል፡፡

የፎገራ ወረዳ አስተዳደር ነዋሪዎቹ ያነሱትን ስጋት ተጋርቷል፤ የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አለባቸው ደጀን እንዳሉት የታችኛው ርብ ግድብ የካናል ሥራ አለመጠናቀቅ የስጋቱ ምንጭ ነው፡፡ ችግሩን ለመፍታት የአማራ ዲዛይንና ቁጥጥር ሥራዎች ድርጅት በጥናት ላይ የተመሰረተ ዲዛይን ሠርቷል፤ ለዚህ በጀት የመደበ ሲኾን የዓባይ እና የጢስ እሳት የግንባታ ተቋራጮች የተለዩ አካባቢዎችን የማስተካከል ሥራ ጀምረዋል ብለዋል፡፡

የክልሉ አደጋ መከላከል ምግብ ዋስትናና ልዩ ድጋፍ የሚሹ አካባቢዎች ማስተባበሪያ ኮሚሽን 530 ሺህ ብር መድቦ እያሠራ እንደኾነም ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ ተቋራጮቹ በቂ ማሽን አለማስገባታቸውን ነው የገለጹት፡፡ ከጣና ጋር ለሚዋሰኑ ቀበሌዎች መንግሥት ያስቀመጠው መፍትሔ እንደሌለ ተናግረዋል፡፡ እንደ ዋና አስተዳዳሪው ገለጻ አደጋው የሚከሰት ከኾነ ሰዎችን ከስፍራው ለማስወጣት የሚያስችል ኮሚቴ ተቋቁሟል፡፡ ዋና አስተዳዳሪው መንግሥት ቦታዎችን ከማመቻቸት ጀምሮ የሚጠበቅበትን ይወጣል ብለዋል፡፡

የወልዲያ ከተማ ከንቲባ አህመድ ያሲን በበኩላቸው ከ2008 ዓ.ም ወዲህ የጎርፍ ተጋላጭነትን ለመቀነስ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ በዓለም ባንክ የካፒታል በጀት፣ በሮድ ፈንድና በከተማ አስተዳደሩ መደበኛ የካፒታል በጀት የቦይ ሥራ፣ በጋቢዮን የታገዘ ግንባታ፣ ባሕላዊ የቦይና የተፋሰስ ሥራዎች መሠራታቸውንም ገልጸዋል፡፡ ምንም እንኳን በርካታ ተፋሰሶች ቢሠሩም የከተማው ነዋሪዎች ከደለል ነፃ እንዲኾኑ ባለመሥራታቸው አሁንም የስጋት ምንጭ እንደኾኑ ተናግረዋል፡፡ ለዚህም ሕዝቡን ያሳተፈ የጽዳት ሥራ በየ15 ቀናት እንዲካሄድ አቅጣጫ ተቀምጧል ብለዋል፡፡

የክልሉ አደጋ መከላከል፣ ምግብ ዋስትና ፕሮግራምና ልዩ ድጋፍ የሚሹ አካባቢዎች ማስተባበሪያ ኮሚሽን እንዳስታወቀው የጎርፍ አደጋን ለማስቀረት የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡ በቢሮው ቅድመ ማስጠንቀቂያ ባለሙያ መልካሙ ጫኔ ከፌዴራል መንግሥት የተገኘውን 10 ሚሊዮን ብር ጨምሮ በክልሉ በጀትና በወርልድ ቪዥን የገንዘብ ድጋፍ በክልሉ የጎርፍ አደጋ ተጋላጭ በኾኑ 16 ወረዳዎች ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡ በዚህም 2 ሺህ 203 ሜትር ኪዩብ የጋቢዮን ግንባታ፣ 140 ኪሎ ሜትር ገደማ የቦይ ደለል ጠረጋና የዳይክ ሥራ እንዲሁም ሌሎች የመከላከያ ተግባራት እንደሚከናዎኑ አቶ መልካሙ አመላክተዋል፡፡ በመንግሥት በጀት ብቻ ውጤታማ ሥራ መሥራት ስለማይቻል ማኅበረሰቡ የድርሻውን ርብርብ እንዲያደርግም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡

Source link

Related posts

ፋሲል ከነማን በገቢ ለማጠናከር ያለመ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ-ግብር በጎንደር ተካሄደ

admin

ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ለአቶ አባ ዱላ ገመዳ እና ለአቶ አብዱላሂ አሊ ሸሪፍ የክብር ዶክትሬት አበረከተ

admin

ከሁለት ሚሊዮን በላይ ወጣቶች በበጋ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መሳተፋቸውን የአማራ ክልል ሴቶች፣ ሕፃናት እና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ አስታወቀ፡፡

admin