56.12 F
Washington DC
February 25, 2021
Satenaw Ethiopian News/Breaking News
Amharic News

በአማራ ክልል በአፈር አሲዳማነት በየዓመቱ ከስንዴ ምርት ብቻ እስከ 3 ቢሊዮን ብር የሚገመት ገንዘብ ይታጣል፡፡ ሀገሪቱ ደግሞ 9 ቢሊዮን ብር ከምርቱ ታጣለች።

በአማራ ክልል በአፈር አሲዳማነት በየዓመቱ ከስንዴ ምርት ብቻ እስከ 3 ቢሊዮን ብር የሚገመት ገንዘብ ይታጣል፡፡

ሀገሪቱ ደግሞ 9 ቢሊዮን ብር ከምርቱ ታጣለች።

ባሕር ዳር፡ ጥር 20/2013 ዓ.ም (አብመድ) በአማራ ክልል አጠቃላይ ከሚታረሰው መሬት 27 በመቶ የሚሆነው በአፈር አሲዳማነት የተጠቃ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ ገልጿል፡፡

በቢሮው የአፈር ለምነት ማሻሻያ ባለሙያ አብዮት መኮንን እንደነገሩን በክልሉ ውስጥ በ9 ዞኖችና በ87 ወረዳዎች የሚገኙ 1 ሺህ 69 ቀበሌዎች በአፈር አሲዳማነት የተጠቁ ናቸው።

በክልሉ አጠቃላይ ከሚታረሰው 4 ነጥብ 45 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ውስጥ ደግሞ 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በአፈር አሲዳማነት የተጎዳ መሆኑን ባለሙያው ነግረውናል። የተሻለ ዝናብ ባለባቸው እና የተሻለ የሰብል ምርት የሚመረትባቸው የክልሉ ምዕራባዊ ደጋማ ቦታዎች ደግሞ በአፈር አሲዳማነት ይበልጥ የተጋለጡ ናቸው፡፡

ምስራቅና ምዕራብ ጎጃም፣ አዊ ብሄረሰብ እና ደቡብ ጎንደር ዞኖች በከፍተኛ ሁኔታ በአፈር አሲዳማነት የተጠቁ ናቸው፤ ሰሜንና ማዕከላዊ ጎንደር፣ ሰሜን ሸዋ፣ ደቡብና ሰሜን ወሎ ዞኖችም ችግሩ መኖሩን ባለሙያው ገልፀውልናል። እነዚህ አካባቢዎች በአብዛኛው ተራራማና ተዳፋታማ በመሆናቸው መሬቱ በጎርፍ በመታጠቡ ለአፈር አሲዳማነት ችግር እንዲጋለጥ አድርጎታል ብለዋል፡፡

መሬት በተደጋጋሚ መታረስ፣ የሰብል ፈረቃ አለመኖር፣ ለመሬት የሚውል የተፈጥሮ ማዳበሪያ መጠን ዝቅተኛ መሆን፣ ሰው ሰራሽ ማዳበሪያ ላይ ጥገኛ መሆንም ለአፈር አሲዳማነት መፈጠርና መባባስ ምክንያቶች ናቸው ተብሏል።

ሀገሪቱ ከምታመርተው አጠቃላይ ምርት እስከ 35 በመቶ የሚሆነው የሚሸፈነው ከአማራ ክልል እንደሆነ ከግብርና ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ባለፉት ዓመታትም ክልሉ ትኩረት ሰጥቶ ካከናወናቸው ተግባራት መካከል የሰብል ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ላይ ነው፡፡ ይሁን እንጅ የሰብል ምርታማነት የሚወሰነው በአፈሩ ለምነትና ጤንነት ላይ በመሆኑ የአፈር ጤንነት እና ለምነት የተሰጠው ትኩረቱ ዝቅተኛ እንደነበር ግብርና ቢሮ አስታውቋል፡፡ ለዚህ ደግሞ በክልሉ አጠቃላይ ከሚታረሰው መሬት 27 በመቶ የሚጠጋው መሬት በአፈር አሲዳማነት የተጠቃ መሆኑን ቢሮ አመላክቷል፡፡

የአፈር አሲዳማነት ችግር ከ50 በመቶ እስከ መቶ በመቶ የሰብል ምርትን ይቀንሳል። ችግሩ በተባባሰባቸው አካባቢዎች ደግሞ ሙሉ ሙሉ ምርት ማምረት በማቆማቸው መሬቱን በባሕርዛፍ የቀየሩ፣ መሬታቸውን ጥለው ለሌላ ሥራ ወደ ከተማ የተሰደዱ አርሶ አደሮች መኖራቸውን ባለሙያው ነግረውናል።

ባለሙያው እንደገለፁልን በአፈር አሲዳማነት ችግር የአማራ ክልል በየዓመቱ ከስንዴ ምርት ብቻ እስከ 3 ቢሊዮን ብር የሚገመት ገንዘብ ይታጣል፡፡ ሀገሪቱ ደግሞ ከምርቱ 9 ቢሊዮን ብር ታጣለች ነው ያሉት፡፡

የአፈር አሲዳማነት ባለበት መሬት ላይ ችግሩ በኖራ ታክሞ ሳይቀረፍ እና አሲዳማነቱ ሳይስተካከል ሰው ሰራሽ ማዳበሪያ መጠቀም ደግሞ እስከ 43 ነጥብ 5 በመቶ የሚሆነው ሰው ሰራሽ ማዳበሪያ ይባክናል ፡፡

የአፈር አሲዳማነትን ችግር ለመቅረፍ የክልሉ መንግሥት ወደ ሥራ ከገባ 10 ዓመት ቢያስቆጥርም በችግሩ ስፋት ልክ መፍትሄ ማምጣት አለመቻሉን ባለሙያው ገልጸዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ በመንግሥት በኩል ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ ነው ባለሙያው የገለጹት፡፡

ኖራው የሚገኝበት፣ የሚመረትበት እና የአፈር አሲዳማነት ያለበት አካባቢ የተራራቀ በመሆኑ ምክንያት አርሶ አደሮች የሚፈልገውን የኖራ መጠን በሚፈልገው ቦታና ጊዜ እንዳያገኝ አድርጎታል ብለዋል፡፡

ኖራ ማቅረብ ብቻ ሳይሆን የቀረበውን ኖራ በአግባቡ እና የአፈር አሲዳማነትን ሊቀርፉ ከሚችሉ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ማዳበሪያ ጋር አቀናጅቶ የመጠቀም ችግሮችም እንደሚያጋጥም ባለሙያው አንስተዋል፡፡ በእነዚህ ችግሮች ምክንያት በአፈር አሲዳማነት ከተጠቃው 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ውስጥ መመለስ የተቻለው ከ10 ሺህ ሄክታር አይበልጥም። ከዚህ ውስጥ ደግሞ እስከ 6 ሺህ ሄክታር በአፈር አሲዳማነት የተጠቃ መሬት መመለስ የተቻለው ባለፉት ሶስት ዓመታት ነው ብለዋል። በዚህም መሰረት በአፈር አሲዳማነት በተጠቃ መሬት በሄክታር ይገኝ ከነበረው 6 ኩንታል ምርት በኖራ በማከም እና ሌሎች ሥራዎችን በተቀናጀ መንገድ በመሥራት በሄክታር ከ80 እስከ 300 በመቶ የምርት ጭማሪ ማምጣት መቻሉን ባለሙያው ነግረውናል።

ምርት አቁሞ በነበረ መሬት ላይ ደግሞ በሄክታር እስከ 40 ኩንታል ስንዴ ምርት ማግኘት መቻሉን ነው ባለሙያው የገለጹት። በዚህ ዓመት የአፈር አሲዳማነትን ችግር ለመቅረፍ ባለፉት አስር ዓመታት የታከመውን መሬት በአንድ ዓመት ለማከም እየተሠራ እንደሚገኝ ነው ባለሙያው ያመላከቱት፡፡ ይህን ተግባራዊ ለማድርግ ኖራን እንደማንኛውም የግብርና ግብዓት በሕብረት ስራ ማኅበራት በኩል ለማቅረብ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

ባለፉት 10 ዓመታት አሲዳማ አፈርን በኖራ በማከም የመሬትን ለምነት መመለስ የተቻለበትን መንገድ በቀጣይ በአንድ ዓመት ውስጥ መሥራት ካልተቻለ ችግሩን መቀነስ እንደማይቻልም ባለሙያው ገልጸዋል፡፡ መንግሥትም የአፈር አሲዳማነት ችግር ባለባቸው አካባቢዎች የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ በስነ ህይወታዊ አሰራር ተጠናክሮ እንዲሠራ ማድረግ እንዳለበት ባለሙያው አሳስበዋል።

ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሠራ

ፎቶ፡- ከግብርና ሚኒስቴር

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡

Source link

Related posts

ቦርዱ ሕጋዊ ሃላፊነቱን እና ግዴታውን እንደሚወጣ የቦርዱ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ አስታወቁ

admin

የደቡብ ክልል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በሀዲያ ዞን ሻሾጎ ወረዳ ያልተጠናቀቁ ፕሮጀክቶችን ጎብኝተዋል

admin

 ለጤናው ዘርፍ ከ21 ቢሊየን ዶላር በላይ ወጪ በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ያስፈላጋል- ዶ/ር ሊያ

admin