66.9 F
Washington DC
June 15, 2021
Satenaw Ethiopian News/Breaking News
Amharic News

በአማራ ከልል የምጣኔ ሀብቱ ለውጥ እንዲያስመዘግብ ሥራዎች እየተሠሩ እንደሆነ ተመላከተ፡፡

በአማራ ከልል የምጣኔ ሀብቱ ለውጥ እንዲያስመዘግብ ሥራዎች እየተሠሩ እንደሆነ ተመላከተ፡፡

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 13/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ 84 በመቶ የሚኾነው ሕዝብ ከእጅ ወደ አፍ በሆነ የግብርና ሥራ እንደሚተዳደር መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ የሀገሪቱ የሳይንስና የቴክኖሎጅ ሽግግር ዕድገትም ገና ዳዴ የሚልበት ደረጃ ላይ ነው የሚገኘው፡፡ የሕዝቡ ቁጥርም ከኢኮኖሚው ዕድገት ጋር ባልተመጣጠነ መንገድ እያደገ እንደሚገኝ ነው ባለሙያዎች የሚገልጹት፡፡

በአማራ ክልል የምጣኔ ሀብት ለውጥ ለማምጣት በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጽሕፈት ቤት የልማት አማካሪዎች ቡድን ተቋቁሞ በግብርና፣ በቱሪዝም፣ በማኑፋክቸሪንግ እና በማዕድን ዘርፎች እና ችግሮች ላይ ጥናት አድርጓል፡፡ ፍኖተ ካርታም ተዘጋጅቷል፡፡ ዘርፎቹም በክልሉ ለሥራ ዕድል ፈጠራ እና ለምጣኔ ሀብት ካላቸው አስተዋጽኦ አኳያ ተመርጠዋል፡፡

በቡድኑ የፖሊሲ ባለሙያ አቶ አብነት በላይ እንዳሉት የግብርናው ዘርፍ ለሀገር ውስጥ የምርት ዕድገት ከሚያበረክተው አስተዋጽኦ አኳያ አንዱ ትኩረት የተሰጠው ዘርፍ ነው፡፡ በዚህም በግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ ውስጥ መዋቅራዊ ሽግግር ለማምጣት ከዘልማዳዊ አሠራር በመላቀቅ የተሻሻሉ የግብርና ግብዓቶችን እና የቴክኖሎጅ ውጤቶችን መጠቀም ዓላማ ያደረገ ነው፡፡

በተበጣጠሰ መሬት የውኃ ሃብትን በመጠቀም በዓመት ሥስት ጊዜ የማምረት አቅምን ማሳደግ፣ ኩታ ገጠም ሰብል ልማትን መተግበር ላይ ትኩረት ይደረጋል፡፡ ብሔራዊ ባንክ እና ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማትን በመጠቀም የብድር አቅርቦትን ማመቻቸት እና የግል ሴክተሩን በማሳተፍ በግብርናው ዘርፍ የምጣኔ ሃብት ሽግግር ለማምጣት ዓላማ ያደረገ ፍኖተ ካርታ መሆኑን አቶ አብነት ገልጸዋል፡፡ ይህንን ለማድረግ መንግሥትን ጨምሮ የሁሉም አጋር አካላት ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን አስቀምጠዋል፡፡

በአማራ ክልል ግብርና ምርምር ኢንስቲቲዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር እና ተመራማሪ ኤርሚያስ አባተ (ዶክተር) እንዳሉት አንድ ሀገር የምግብ ዋስትናውን ማረጋገጥ ካልቻለ ብቁ፣ አምራች እና ተመራማሪ ዜጋ መገንባት እና የሀገርን ሉዓላዊነት ማስጠበቅ አይቻልም፡፡

የግብርናውን ዘርፍ ለማሳደግ የፖሊሲ እሳቤዎች ሊኖሩ እንደሚገባ ዶክተር ኤርሚያስ አስቀምጠዋል፡፡ አግሮ ኢንዱስትሪዎችን በማስፋት በገጠር የሚታየውን የሰው ኀይል ጫና መቀነስ እና ወደ ‹‹ፋርም ሜካናይዜሽን›› ማስፋት እንደሚገባም መክረዋል፡፡ የአርሶ አደሮችን ክህሎት እና ሙያ የሚያግዝ የኤክስቴንሽን ሥራ መሥራት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ ምርታማነትን ሊያሳድጉ የሚችሉ ቴክኖሎጅዎችን እና የተሻሻሉ ግብዓቶችን በስፋት መጠቀም እንደሚያስፈልግም አስቀምጠዋል፡፡ እነዚህን ግብዓቶች አርሶ አደሮች ገዝተው እንዲጠቀሙ የብድር አቅርቦት ማመቻቸት ይገባል፡፡

በመንግሥት የሚሠሩ የመስኖ፣ የመንገድ እና መሰል መሰረተ ልማቶች በበቂ ሁኔታ ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባም ዶክተር ኤርሚያስ አመላክተዋል፡፡ እነዚህ ምቹ ሁኔታዎች በተሟሉባቸው አንዳንድ አካባቢዎች ጭምር አርሶ አደሩ ያመረተውን ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያቀርብ ገበያ በመፍጠር በኩል የሚታዩ ውስንነቶችን ማስተካከል እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

የውጭ ምንዛሬ ችግርን ለመቅረፍ በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳደሪ የሆኑ ምርቶችን ማምረት ይገባል ነው ያሉት፡፡ የግብርና ምርቶችን አቀነባብሮ እና አሽጎ ለዓለም ገበያ ማቅረብ የሚችሉ የግሉ ዘርፍ እና የአርሶ አደር ድርጅቶችን መፍጠር እንደሚገባም ዶክተር ኤርሚያስ በመፍትሄነት አስቀምጠዋል።

ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሠራ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡

Source link

Related posts

የአቃቂ ጨፌ ሁለት የተማከሉ ፍሳሽ ማጣሪያ ጣቢያዎች ተመረቁ

admin

ለ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ በመራጮች ምዝገባ ሂደት ለሚያጋጥሙ ችግሮች መፍትሔ እየሰጠ መሆኑን የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ገለጸ።

admin

“ለውጭ ኃይሎች ልናረጋግጥላቸው የምንወደው የወልቃይት ጠገዴ አማራዎች ያስመለስነው ማንነት እንጂ የነጠቅነው መሬት የለም” አቶ አሸተ ደምለው የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ አስተዳዳሪ

admin