51.91 F
Washington DC
May 13, 2021
Satenaw Ethiopian News/Breaking News
Amharic News

በነዳጅ ምርት አቅርቦትና ስርጭት ያሉ እጥረቶችን ለመፍታት እንደሚሠራ የአማራ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ገለፀ፡፡

በነዳጅ ምርት አቅርቦትና ስርጭት ያሉ እጥረቶችን ለመፍታት እንደሚሠራ የአማራ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ገለፀ፡፡

ባሕር ዳር፡ ጥር 19/2013 ዓ.ም (አብመድ) ቄስ እንዳለ ሞላ የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ ናቸው፡፡ ቤተሰቦቻቸዉን የሚያስተዳድሩት ባለ ሦስት እግር ተሸከርካሪ (ባጃጅ) አገልግሎት በመስጠት በሚያገኙት ገቢ ነው፡፡ግብራቸውን በወቅቱ እንደሚከፍሉ የተናገሩት ቄስ እንዳለ በቤንዚን ማጣት የተነሳ ቤተሰቦቻቸዉን ማስተዳደር እንደከበዳቸው አስረድተዋል፡፡ ቤንዚን ለማግኘት እንቅልፋቸውን በማጣት ሌሊት ማደያ ቢሰለፉም የፈለጉትን በወቅቱ ሊያገኙ እንዳልቻሉ ተናግረዋል፡፡

“ቤንዚን ከማደያ ማግኘት ስላልቻልን ከጥቁር ገበያ ለመግዛት እየተገደድን ነው፡፡ እኛ ብዙን ጊዜ የምንሠራው በቀን 300 ብር አይዘልም፤ ከጥቁር ገበያ አንድ ሊትር ቤንዚን በ50 ብር ነው እየገዛን ያለነው፣ እንዲህ እየተሠራ የት ይደረሳል? በተጨማሪም ተገልጋይ የሆነው ሕዝብም እየተንገላታ ነው” ብለዋል ቄስ እንዳለ፡፡ እርሳቸዉን ጨምሮ ሌሎች አሸከርካሪዎች በቤንዚን ማጣት ለችግር መዳረጋቸውን ነው የገለፁት፡፡

የሞተር አሽከርካሪው አብርሃም ተከስተ ደግሞ የቤንዚን እጥረት የተከሰተው የሚመለከታቸው አካላት ኀላፊነታቸውን በአግባቡ ባለመወጣታቸው ነው ብሏል፡፡ “ሁሉም ሰው ቤንዚን በጀሪካን ለመቅዳት የሚያስችለውን ማስረጃ ይዞ ይመጣል፤ የማስረጃ ወረቀት ደግሞ አግባብነት በሌለው መልኩ ሊመጣ ይችላል፤ ይህ አሠራር ነው ቤንዚንን ወደ ጥቁር ገበያ እያስገባ ያለው፤ ይህ ግዴለሽነት የተሞላበት አሠራር ሊስተካከል ይገባል” ነው ያለው፡፡

የባሕር ዳር ቁጥር 4 ኖክ ማደያ ሥራ አስኪያጅ አቶ ክንድዬ መኮንን ለቤንዚን እጥረት መከሰት በዋነኝነት የአቅርቦት ችግር ነው ብለዋል፡፡ ድርጅቱ በየቀኑ ነዳጅ ለማስገባት ጥያቄ ቢያቀርብም መፍትሄ እንዳላገኘ ተናግረዋል፡፡

የሥራ ኃላፊዎች ሳይቀሩ ቤንዚን በጥቁር ገበያ እየተሸጠ መሆኑን እንደሚገልጹ ነግሮናል፡፡ “ለምን የጸጥታ አካላትና ሌሎች ተቆጣጣሪ አካላት የጥቁር ገበያ ምንጭን ማግኘት ተሳናቸው? እኛ ለባለ መስኖ አርሶ አደሮች 20 ሊትር፣ ለባለ ጀልባዎች 60 ሊትርና ለመኪኖች ቤንዚን እንድንቀዳ ንግድና ገበያ ልማት አቅጣጫ ቢሰጠንም የማስረጃ ወረቀቱን የሚጽፍላቸው ግን ሌላ አካል በመሆኑ እስከ 300 ሊትር ቤንዚን እንድንቀዳላቸው ያስገድዱናል፡፡ እኛ ሕግን አክብረን ስንሠራ ባለ ጉልበት ያስቸግረናል፤ ለመደባደብ የሚመጡም ደንበኞች አሉ” ብለዋል ሥራ አስኪያጁ፡፡ ጉዳዩ አፋጣኝ መፍትሄ ሊሰጠው እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

የአማራ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ በክልሉ የነዳጅ አቅርቦት ችግርና መፍትሄዉ ጋር በተያያዘ ከባለድርሻ አካላት ጋር ዛሬ በባሕር ዳር ውይይት አድርጓል። መንግሥት የነዳጅ ድጎማን በማድረግ የ 3 ቢሊዮን ዶላር ነዳጅ ግዢ ቢፈጽምም ለአማራ ክልል የሚደርሰው ድርሻ በግልጽ እንዳልተቀመጠ የአማራ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ምትክል ኀላፊ አቶ ተዋቸው ወርቁ አስረድተዋል፡፡

በክልሉ 100 ሺህ የሚደርሱ ተሽከርካሪዎች፣ 206 ማደያዎች ፣19 ነዳጅ አቅራቢ ኩባንያዎችና ሦስት ስትራቴጂክ የነዳጅ ማከማቻዎች እንዳሉ አቶ ተዋቸው ባቀረቡት የዳሰሳ ጥናት አስረድተዋል፡፡

የነዳጅ አቅራቢ ኩባንያዎች በገቡት ውል መሠረት ነዳጅ እያቀረቡ አለመሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የነዳጅ ማደያ ቁጥር ማነስ፣ የኩባንያዎች አገልግሎት አሰጣጥ ችግር መኖር፣ ነዳጅ ከወደብ ተነስቶ ወደ ማደያ እንጂ ወደ ማከማቻ አለመግባት፣ ሕገ ወጥ ንግድ በሚፈለገው ልክ ያልተቀረፈ መሆኑ ለእጥረቱ መከሰት ዋንኛ ምክንያት መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

የነዳጅ መሠረተ ልማቶችን ማስፋፋት፣ ስትራቴጂክ ማከማቻዎች መዘርጋት፣ ሕገ ወጥ የነዳጅ ንግድን ሙሉ በሙሉ ማስቆም፣ በሃገሪቱ ያለውን የነዳጅ ክፍፍል ፍትኃዊ ማድረግ ዓበይት መፍትሄ እንደሆኑ ምክትል ኀላፊው አስረድተዋል፡፡

ከየተቋማት የተውጣጣ ግብረ ኃይል ማቋቋም፣ ቅንጅታዊ አሠራርን መዘርጋት እና አስተማሪ ርምጃ መውሰድ ደግሞ በመፍትሄነት ተጠቅሰዋል፡፡ ችግሩን ለመቅረፍ ቢሮው እንደሚሠራም በውይይቱ ተጠቅሷል፡፡

ዘጋቢ:- ብሩክ ተሾመ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡

Source link

Related posts

ቀደምት የስልጣኔ አሻራዎችን ለአንድነትና ለአገራዊ ብልፅግና ጥቅም ላይ ማዋል ይገባል ተባለ

admin

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የምርት መቀበያ መጋዘን ግንባታ በቴፒ ገንብቶ ማጠናቀቁን ገለጸ

admin

ʺጨዋታ ሲመስለን ታምር ሆኖ ፍቅር አለበሰን”

admin