76.68 F
Washington DC
June 17, 2021
Satenaw Ethiopian News/Breaking News
Amharic News

በትግራይ ክልል የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ለማሳደግ እየተሠራ እንደሚገኝ ጤና ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

በትግራይ ክልል የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ለማሳደግ እየተሠራ እንደሚገኝ ጤና ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

በክልሉ ሆስፒታሎችና ጤና ጣቢያዎች ተደራጅተው አገልግሎት እንዲሰጡ እየተደረገ መሆኑም ተመላክቷል፡፡

ባሕር ዳር፡ ሰኔ 02/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ መግለጫ ዛሬ ተሰጥቷል፡፡ በመግለጫው በተለይም ትግራይ ክልልን መልሶ ለማቋቋም የተከናወኑ ተግባራት ትኩረት ተደርጎባቸዋል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪ የዓለም አቀፍ ግንኙትና ሚዲያ ዘርፍ ኃላፊ ቢለኔ ስዩም በሳምንቱ የተከናወኑ ዐበይት ተግባራትን አስታውሰዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በማሰሮ ደንብ የትምህርት ቤት ግንባታ የመሠረት ድንጋይ ማስቀመጣቸው፣ የመገጭ ግድብ ግንባታን መጎብኘታቸው፣ የጣና በለስ ቁጥር አንድ ስኳር ፕሮጀክትን መርቀው ሥራ ማስጀመራቸው፣ የደብሊው ኤ ዘይት ፋብሪካን ማስመረቃቸው እንዲሁም የፌዴሬሽን ምክር ቤት ለ2014 በጀት ዓመት በጀት መያዙ በመግለጫው የተነሱ ዐበይት ተግባራት ናቸው፡፡

በትግራይ ክልል አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን አደራጅቶ ወደ ሥራ በማስገባት ሂደቱ የጤና ተቋማትን ሥራ ለማስጀመር በጤና ሚኒስቴር በኩል የተሠሩ ሥራዎችን አስመልክቶም ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በትግራይ ክልል የጤና ተደራሽነትን ለማሳደግ ከፌዴራል መሥሪያ ቤቱ የተቋቋመ ግብረኀይል ከክልሉ ጤና ቢሮና ከአጋር አካላት ጋር እየሠራ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡

የጤና ተቋማት ሥራ እንዲጀምሩ ከማድረግ አንጻር 55 በመቶ የሚሆኑ የክልሉ ሆስፒታሎችና 52 በመቶ የሚሆኑት ጤና ጣቢያዎች ተደራጅተው አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን አመላክተዋል፡፡ በነዚህ ጤና ተቋማትም ከ95 በመቶ በላይ የጤና ባለሙያዎች በዕለታዊ የሥራ ገበታቸው መገኘታቸውን ገልጸዋል፡፡ በቀጣይም 40 ሆስፒታሎችን እና 58 ጤና ጣቢያዎችን መልሶ ወደ ሥራ ለማስገባት ጥናት ተሠርቶ በጀት ተመድቧል፡፡

ለጤና ተቋማቱ ግብዓት እየተሰራጨ ይገኛል ያሉት ሚኒስትሯ የተሠራጨው ግብዓትም ጥቅም ላይ እየዋለ እንደኾነ ነው የተናገሩት፡፡ ከ108 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸው መድኃኒቶችና ልዩልዩ የሕክምና መሳሪያዎች ወደ ትግራይ ክልል መላካቸውን ያስታወቁት ዶክተር ሊያ በኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ ኤጄንሲ በኩል ተጨማሪ የህክምና ቁሳቁስ እንዲደርስ መደረጉንም አመላክተዋል፡፡

በአጠቃላይ በሚኒስቴሩና በኤጄንሲው ወደ 250 ሚሊዮን ብር በጤናው ዘርፍ ለትግራይ ክልል ወጪ ተደርጓል፡፡

በክልሉ በነበረው የጸጥታ ችግር አምቡላንሶች ለጉዳት ተዳርገዋል ያሉት ሚኒስትሯ 20 አምቡላንሶችን ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱና ከክልሎች ድጋፍ መደረጉን ጠቅሰዋል፡፡ በዚህ ጊዜ 58 አምቡላንሶች በሥራ ላይ ውለዋል፤ ተጨማሪ 65 አምቡላንሶችን ሥራ ለማስጀመርም ጥገና እየተደረገላቸው ይገኛል፤ ተጨማሪ ተሸከርካሪዎች እንዲገቡም ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል ዶክተር ሊያ በሰጡት መግለጫ፡፡

በተንቀሳቃሽ የጤና አገልግሎት ዘርፍ በመንግሥትና በአጋር ድርጅቶች እያንዳንዳቸው 68 የጤና ባለሙያ ያሏቸው 65 ተንቀሳቃሽ የጤና አገልግሎት ሰጪ ቡድኖች ተቋቁመዋል፡፡ እነዚህ ቡድኖች በተለይ በእናቶችና በሕጻናት ጤና ተደራሽ ለመኾን እንደሚሠሩ አስታውቀዋል፡፡ በዚህም ባለፉት ሁለት ወራት ከአምስት ዓመት በታች ለኾኑ ከ75 ሺህ በላይ ሕጻናት ለምግብ እጥረት እንዳይጋለጡ የመለየት ሥራ ተሠርቷል፡፡ ለከፋ የምግብ እጥረት የተጋለጡ 2 ሺህ 780 ሕጻናት ደግሞ የምገባና ሕክምና ስነ ስርዓት መካሄዱን አስታውቀዋል፡፡

የፌዴራል መንግሥት 120 የጤና ባለሙያዎችን አሠማርቶ በክልሉ ተፈናቅለው በጊዜያዊ መጠለያ ለሚገኙት 24 ሰዓት በነጻ የሕክምና ድጋፍ እየተሰጠ ነው፡፡ ከፍተኛ የሰው ብዛት ባለባቸው 17 ጊዜያዊ ማእከላትም ጊዜያዊ ጤና ጣቢያ ተቋቁሟል ብለዋል፡፡

በትግራይ ክልል የኮሮናቫይረስን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የምርመራና ክትትል ሥራ በመቀሌ ፣ በአዲግራትና በአክሱም ተጀምሯል፡፡ በቀጣይም በማይጨው፣ ውቅሮ፣ ሽሬ፣ ኩሂያ፣ ለማስጀመር ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ክትባት የማዳረስ እንቅስቃሴውም ተጠናክሮ መቀጠሉን አመላክተዋል፡፡ እስካሁን አገልግሎት መስጠት በጀመሩት የጤና ተቋማት የእናቶችና የሕጻናት ጤናን ጨምሮ በኤች አይ ቪ፣ በቲቢ፣ በተላላፊና ሌሎች በሽታዎች ከ409 ሺህ በላይ ሰዎች የህክምና አገልግሎት አግኝተዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Source link

Related posts

የቱሪዝም ዘርፉን በዲጂታል ቴክኖሎጂ ለማዘመን የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ

admin

“ተዋግተን አይደለም ስንተኛ ብንውል እንኳን መቀሌና አዲስ አበባ አይገቡም” ጄኔራል ባጫ

admin

የመራጮች ምዝገባ ለሁለት ሳምንት ተራዘመ

admin