70 F
Washington DC
April 10, 2021
Satenaw Ethiopian News/Breaking News
Amharic News

በትግራይ ክልል ለ2 ነጥብ 5 ሚሊየን ተሰዎች እርዳታ ለማቅረብ በቂ ዝግጅት ተደርጓል – የብሔራዊ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን 

አዲስ አበባ ፣ ጥር 13 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በትግራይ ክልል በሕግ ማስከበር ሥራው ሰብዓዊ ቀውስ ገጥሟቸዋል ተብሎ የተገመቱትን 700 ሺህ ሰዎች ጨምሮ ለ2 ነጥብ 5 ሚሊየን ሰዎች እርዳታ ለማቅረብ በቂ ዝግጅት መደረጉን የብሔራዊ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ገለጸ።

ኮሚሽነሩ ምትኩ ካሳ ዛሬ በሰጡት መግለጫ በክልሉ የሕግ ማስከበር ሥራው ከመጀመሩ በፊት 1 ነጥብ 8 ሚሊየን ሰዎች እርዳታ እየተደረገላቸው እንደነበረና ይህም ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል።

ከእነዚህ ውስጥ 1 ነጥብ 1 ሚሊየን የሚሆኑት የልማታዊ ሴፍቲኔት ተጠቃሚዎች ሲሆኑ 600 ሺህ ሰዎች ደግሞ የዕለት ደራሽ እርዳታ እየተደረገላቸው መሆኑን ተናግረዋል።

ቀሪዎቹ 110 ሺህ ሰዎች ደግሞ ቀደም ሲል በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ተከስቶ በነበረው ግጭት ተፈናቅለው በክልሉ የሚገኙ ተረጂዎች መሆናቸውንም ኮሚሽነሩ አስረድተዋል።

በክልሉ በተካሄደው ሕግ የማስከበር ሥራ ሊረዱ የሚችሉ ተጨማሪ ሰዎችን ለመለየት በደቡባዊ፣ ማዕከላዊና ምሥራቃዊ ትግራይ መንግስትና የተለያዩ ዓለም አቀፍ የረድኤት ተቋማት በጥምረት የዳሳሳ ጥናት ማካሄዳቸውንም ጠቁመዋል።

በዳሰሳ ጥናቱ በአሁኑ ወቅት የሁለቱ አካባቢዎች ጥናቶች መጠናቀቃቸውንና አንዱ ጥናትም በመካሄድ ላይ መሆኑን ተናግረዋል።

“በሁለቱ ጥናቶች መሰረት በሕግ ማስከበር ሥራው የተረጂዎች ቁጥር 700 ሺህ ሊደርስ እንደሚችል በመገመቱ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ተዘጋጅተናል” ብለዋል።

ይህንን ቁጥር በክልሉ ከዚህ ቀደም ከነበሩት 1 ነጥብ 8 ሚሊየን ተረጂዎች ጋር በመደመር፤ በጥቅሉ ለ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሰዎች ድጋፍ ለማቅረብ መዘጋጀታቸውን ጠቁመዋል።

ለክልሉ ድጋፍ የሚውል 311 ሺህ 526 ኩንታል የእህል ክምችት በመንግስት ማዕከላዊ መጋዘንና በአጋር አካላት መጋዘን ውስጥ መኖሩን ጠቁመዋል።

በተጨማሪም 60 ሺህ ኩንታል ዱቄት፣ 1 ነጥብ 7 ሚሊየን ሊትር የምግብ ዘይት እና 173 ሺህ 200 ኩንታል ስንዴ ወደ መቀሌ እየተጓጓዘ መሆኑን ጠቁመዋል።

“እነዚህን ድጋፎች በክልሉ ለተቋቋሙት 92 የምግብ ማሰራጫ ማዕከላት በማከፋፈል ለተረጂዎች በተገቢው መልኩ እንዲደርሱ ይደረጋል” ብለዋል።

በክልሉ የአቅርቦት ከፍተት አለመኖሩን የጠቆሙት ኮሚሽነሩ፤ የእህል ክምችቱ ከ2 ነጥብ 5 ሚሊየን በላይ ተረጂዎችን ለመርዳት እንደሚያስችልም ነው የገለጹት።

እንደኮሚሽነሩ ገለጻ፤ ልዩ እርዳታ ለሚሹ የማኅበረሰብ ክፍሎች (ህጻናት፣ አረጋዊያን፣ አካል ጉዳተኞችና ህሙማን) የአየር ትራንስፖርት በመጠቀም አፋጣኝ እርዳታ እየቀረበ ይገኛል።

አንዳንድ ዓለም አቀፍ ተቋማት በክልሉ የተረጂዎች ቁጥር ‘ይህን ያህል ደርሷል’ እያሉ የሚያወጧቸው ቁጥሮች የፌደራል መንግስቱ ያላጸደቀውና ትክክል ያልሆኑ መሆናቸውንም አረጋግጠዋል።

በሌላ በኩል በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በመተከል ዞን በቅርቡ 97 ሺህ 613 ሰዎች መፈናቀላቸውንና እነዚህንም ሰዎች የመርዳት ሥራ መጠናከሩን ገልጸዋል።

በዞኑ ሰብዓዊ እርዳታዎችን ለማስተባበር የሚያስችል የአስቸኳይ ጊዜ ማስተባበሪያ ማዕከል በዞኑ ግልገል በለስ ከተማ መቋቋሙን ተናግረዋል።

እስካሁንም 51 ሺህ 408 ኩንታል ምግብ ነክ ድጋፍ እንዲሁም 281 ሺህ 480 አልባሳትን ጨምሮ የተለያዩ የማብሰያ ቁሶችን ድጋፍ መደረጉን ገልጸዋል።

የማስተባበሪያ ማዕከላቱ ከተለያዩ አጋር አካላት ጋር በቅንጅት የሚያከናውኑት ይህንንና ሌሎች የሰብዓዊ እርዳታ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ጠቁመዋል።

በሁለቱም ክልሎች የሚገኙ ተረጂዎችን መልሶ የማቋቋም ሥራው በቀጣይ እንደሚካሄድም አቶ ምትኩ ማረጋገጣቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 Source link

Related posts

የቱሪዝም ዘርፉን በዲጂታል ቴክኖሎጂ ለማዘመን የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ

admin

“ኢትዮጵያዊነት የማይደበዝዝ ይልቁንም በይበልጥ የሚደምቅና የሚፈካ የጋራ ማንነታችን ሊሆን ይገባል” ርእሰ መሥተዳድር አገኘሁ ተሻገር

admin

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለተሳሳተው ካርታ ይቅርታ ጠየቀ – ESAT Amharic

admin