46.09 F
Washington DC
February 25, 2021
Satenaw Ethiopian News/Breaking News
Amharic News

በባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ከ500 በላይ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች የቦታ አቅርቦት ችግር ገጥሟቸዋል፡፡

በባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ከ500 በላይ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች የቦታ አቅርቦት ችግር ገጥሟቸዋል፡፡

ባሕር ዳር ፡ የካቲት 12/2013 ዓ.ም (አብመድ) የቦታ አቅርቦት ችግር ኢንቨስትመንቶችን ወደ ሥራ ለማስገባት ፈተና እንደሆነበት የከተማ አስተዳደሩ አስታውቋል፡፡ ይህ የተባለው በከተማ አስተዳደሩ ምክር ቤት 4ኛ ዙር ስምንተኛ ዓመት የሥራ ዘመን 21ኛ መደበኛ ጉባዔ ላይ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴውን አስመልክቶ በተሰጠ ማብራሪያ ነው፡፡

በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር የኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኀላፊ አላዩ መኮንን በሰጡት ማብራሪያ የባሕር ዳር ከተማ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ እየጨመረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በከተማዋ ለመሠማራት ጥያቄ የሚያቀርቡ ባለሀብቶችም በፍጥነት ወደ ሥራ በመግባት የሥራ ዕድል ፈጠራ ሚናቸውን እየተወጡ እንደሆነ አንስተዋል፡፡ በከተማዋ 104 ኢንዱስትሪዎች ሥራ ጀምረዋል፤ አቅማቸውን በማሳደግ አዳዲስ ማሽኖች እያስገቡ መሆኑም በጥሩ ጎን ተነስቷል፡፡ ተጨማሪ 305 ፕሮጀክቶች ደግሞ በግንባታ ሂደት ላይ ይገኛሉ ተብሏል፡፡ ይሁን እንጂ የከተማው ኢንቨስትመንት ብዙ ፈተናዎች እንደገጠሙት ተነስቷል፡፡ ከችግሮቹ መካከል የመንገድ፣ የውኃና የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማቶች አለመሟላት ተነስተዋል፡፡

በተያዘው ዓመት ችግሮቹን ለመፍታት በልዩ ትኩረት እየተሠራ መሆኑም ተመላክቷል፡፡ ለዚህም የክልሉ መንግሥት 10 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር መድቧል። መምሪያ ኀላፊው እንዳሉት በከተማ አስተዳደሩ 10 ሚሊዮን ብር በጀት ተይዞ ወደ ሥራ ተገብቷል፡፡ በተለይ በመንገድ መሰረተ ልማት ባለሀብቶች እንዲሳተፉ እየተደረገ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

የአንድ መስኮት አገልግሎት ባለመኖሩ ባለሀብቶች ለእንግልት መዳረጋቸውን በማንሳትም የአንድ መስኮት አገልግሎት ለመስጠት ጥናት እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ሌሎች ችግሮችንም ከቴክኒክና ሙያ ኮሌጁና ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር መፍትሔ እየተሰጠ እንደሆነ አመላክተዋል፡፡ የመሬት አቅርቦት ችግር በዘርፉ ያጋጠመ ሌላኛው ችግር መሆኑ ተመላክቷል፡፡

በተሰጠው መረጃ በአራት የኢንዱስትሪ መንደሮች 850 ሄክታር መሬት ተዘጋጅቶ ለ638 ባለሀብቶች ተላልፏል፤ ከኢንዱስትሪ መንደሮቹ ውጪ መሰጠቱም ተጠቅሷል፡፡ መምሪያ ኀላፊው እንዳሉት በባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ክልል ውስጥ ለኢንቨስትመንት የሚሆን ቦታ ባለመኖሩ ተጨማሪ ጥያቄዎችን ማስተናገድ አልተቻለም፡፡ ባለፉት ሦስት ዓመታት ለዘርፉ የተዘጋጀ ቦታ እንደሌለም አስታውቀዋል፡፡ በዚህም ከ500 በላይ ፕሮጀክቶች ተገምግመው በመሬት ችግር ግንባታ አልጀመሩም፡፡

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ማሻሻያ እየተደረገበት ያለው አዲሱ መዋቅራዊ ፕላን ችግሩን በጊዜያዊነት መፍታት የሚቻልበት ዕድል መኖሩን ኀላፊው አመላክተዋል፡፡ በአዲሱ መዋቅራዊ ፕላን 470 ሄክታር መሬት እንዲከለል በከተማ ኮሚቴው እንደተወሰነም ጠቅሰዋል፡፡ በዘርፉ የሚስተዋለውን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ግን በባሕር ዳር ዙሪያ ያሉ ዘጠኝ የገጠር ቀበሌዎችን ወደ ከተማ አስተዳደሩ ማካተት አስፈላጊ እንደሆነ አመላክተዋል፡፡

የብድር አገልግሎት ችግርም ባለሀብቶችን በከፍተኛ ደረጃ እየተፈታተነ ነው ተብሏል፡፡ አቶ አላዩ እንዳሉት ልማት ባንክ ብድር ካቆመ አንድ ዓመት አልፎታል፡፡ በዚህም 205 ፕሮጀክቶች ግንባታቸው ተጠናቅቆ በብድር እጦት ምክንያት ሥራ እንዳልጀመሩ ገልጸዋል፡፡ ወደ ሥራ ለማስገባት ብድር የሚያገኙበት ሁኔታ እየተመቻቸ መሆኑንም አመላክተዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡

Source link

Related posts

የኢትዮጵያ መንግሥት የድምበር ጉዳዩን በሠላማዊና ዲፕሎማሲያዊ አማራጭ ለመፍታት በቅድሚያ የሱዳን መንግሥት በኀይል የያዛቸውን ቦታዎች ለቆ መውጣት እንዳለበት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢፌዴሪ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ታዬ አፅቀሥላሴ አስገነዘቡ፡፡

admin

ኢትዮጵያን በቀጣይ 10 ዓመታት የአፍሪካ የብልፅግና ተምሳሌት ለማድረግ ተመራቂ ተማሪዎች በሀገሪቱ ልማት በመሳተፍ የድርሻቸውን እንዲወጡ የጠቅላይ ሚንስትሩ የደኅንነት አማካሪ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው ጥሪ አቀረቡ፡፡

admin

በደቡብ ክልል በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ እየቀረበ  ነው -የክልሉ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን

admin