71.98 F
Washington DC
May 17, 2021
Satenaw Ethiopian News/Breaking News
Amharic News

በበዓል ወቅት በጤና እንዲውሉ፤አመጋገበዎን ያስተካክሉ፡፡

በበዓል ወቅት በጤና እንዲውሉ፤አመጋገበዎን ያስተካክሉ፡፡

ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 21/2013 ዓ.ም (አሚኮ) አጿማትን ተከትለው በሚመጡ በዓላት አመጋገብን ማስተካከል እንደሚገባ የሥነ ምግብ ባለሙያዎች ይመክራሉ፡፡ በበዓል ወቅት ያለውን የአመጋገብ ልምድ በተመለከተም አሚኮ የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዎችን አነጋግሯል፡፡

ወጣት ሙሉቀን በሪሁን የትንሣኤ በዓል በመጣ ቁጥር የሚያስታውሰው አንድ ክስተት አለ፤ ቅባት የበዛበት ምግብ ተመግቦ ለህመም የተጋለጠበትን ጊዜ፡፡ በአንድ ወቅት ቅባት የበዛበት ምግብ ለሠውነቱ ባለመስማማቱ በዓልን በህክምና እንዲያሳልፍ ተገዷል፡፡ ከዚያ በኋላ ትንሣኤን ቀለል ባሉ ምግቦች የመፈሰክ ልምድ እንዳዳበረ ይናገራል፡፡ ትንሣኤ ከረጅም ጊዜ ጾም በኋላ የሚመጣ በዓል በመሆኑ ቅባት የበዛበት ምግብ እና አልኮል መጠቀም ተገቢ አለመሆኑንም ነግሮናል፡፡ “የጨጓራችን መጎዳት ለሌላ ተጨማሪ ህመም ሊጋልጥ ስለሚችልም ጥንቃቄ ማድረግ ተገቢ ነው” ብሏል፡፡

ሌለዋ አስተያየት የሰጡን ወይዘሮ ፈንታ ይሁኔ ለበዓል ቅባት የበዛበት ምግብ ማዘጋጀት የተለመደ ቢሆንም መጥኖ መሥራት ተገቢ መሆኑን መክረዋል፡፡ በቀደመው ጊዜ የሁዳዴ ጾም መፈሰኪያ ተብሎ ተልባ እና ሱፍ ይዘጋጅ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ ጤናችን ለመጠበቅ ሠውነታችንን ቀስ በቀስ አለማምደን መመገብ አለብን ነው ያሉት ወይዘሮ ፈንታ፡፡

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሥነ ምግብ እና አመጋገብ ትምህርት ክፍል መምህርት ገነት እንዳልክ በበዓል ወቅት አመጋገባችን ጤናማ መሆን እንዳለበት ተናግረዋል፡፡ መምህርት ገነት እንዳሉት የአብዛኛው ኢትዮጵያውያን የበዓል አመጋገብ ተመሳሳይ ነው፡፡ ጾም ሲፈታ የእንስሳት ተዋጽኦዎችን ማለትም ሥጋ፣ ዶሮ፣ እንቁላል፣ ወተት፣ ቅቤ እና መሰል ምግቦች መመገብ የተለመደ ነው ብለዋል፡፡ “ይህ ደግሞ ለረጅም ጊዜ ከቅባት ርቆ የቆየው ጨጓራችን በአንድ ጊዜ ለመቀበል ይቸገርና ለህመም እንጋለጣለን” ነው ያሉት፡፡

የሥነ ምግብ መምህሯ እንደገለጹት በበዓል ወቅት የምንመገባቸው የእንስሳት ተዋጽኦዎች በተፈጥሮአቸው ከፍተኛ ቅባት አላቸው፤ በተጨማሪ ወጥ ለማጣፈጥ የምንጨምረው ዘይት ቅባት (የፕሮቲን) መጠኑ ከፍተኛ በመሆኑ ችግሩን ያባብሰዋል፡፡

እንደ መምህር ገነት ገለጻ በጾም ወቅት የምንመገባቸው ምግቦች ቅባት ያልበዛባቸው በመሆናቸው ጨጓራ ለሥርዓተ ልመት ይጠቀምባቸው የነበሩ ንጥረ ነገሮች (ኢንዛይሞች) መጠናቸው ይቀንሳል፡፡

ጨጓራ ከለመደው ሥርዓት የወጣ አመጋገብ ማለትም ቅባት የበዛባቸውን ምግቦች መመገብ ስንጀምር ሆድ መንፋት፣ ማቃጠል፣ ቁርጠት፣ የምግብ ፍላጎት መቀነስ እና መሰል ህመሞች መሰማት ይጀምራሉ ነው ያሉት፡፡

“ሰውነታችን ወደ ውስጥ የገባውን ቅባት በሚፈልገው መጠን ከተጠቀመ በኋላ ቀሪው በስብ መልክ ለተጓዳኝ በሽታ ያጋልጣል” ብለዋል፡፡ መምሕሯ እንዳሉት እንደነዚህ ዓይነት ችግሮች እንዳይከሰቱ በቅድሚያ ጾም ሲፈታ ዝቅተኛ የቅባት መጠን ያላቸውን እንደ አትክልት እና ፍራፍሬ እንዲሁም ጭማቂ የመሳሰሉ ምግቦችን መመገብ ተገቢ ነው፤ ይህም ሰውነታችን ቀስ በቀስ ቅባቱን እንዲለማመደው ያደርጋል፡፡

በተጨማሪ በ24 ሰዓታት ውስጥ ከሁሉም የምግብ ክፍሎች ማለትም ከጥራጥሬ፣ ከአትክልትና ፍራፍሬ ከእንስሳት ተዋጽኦ የተሰባጠረ ጤናማ አመጋገም ተግባራዊ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል፡፡

በባሕላዊ መንገድ የሚዘጋጁ እንደተልባና ሱፍ ምግቦችን ቀድሞ በመመገብ ከአፍ ጀምሮ እስከ ጨጓራ ያለውን የሥርዓተ ልመት አካሎች ወደ መደበኛው ሥራቸው እንዲመለሱ ማድረግ ተገቢ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የምግብ መጠንን በመቀነስና የአልኮል መጠጦችን ባለመጠቀም በበዓል ወቅት የሚከሰቱ ህመሞችን ማስወገድ እንደሚቻልም መክረዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡

Source link

Related posts

የኦሮሚያ ክልል በማንነት ላይ የሚደርሰውን ጥቃት በማስቆም በክልሉ ለሚኖረው ሕዝብ ደኅንነት በትኩረት ሊሠራ እንደሚገባ

admin

ተስፋየ ገብረአብ፡ የወያኔው ኦቶ ዲትሪኽ – መስፍን አረጋ | Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider

admin

በዚህ ወቅት ከገጠመው ችግር ለመውጣት የሰከነ ውይይት እና በሥነ ምግባር የተገራ የሥነ ተግባቦት አውድ መፍጠር እንደሚያስፈልግ ተገለጸ፡፡

admin