51.91 F
Washington DC
May 12, 2021
Satenaw Ethiopian News/Breaking News
Amharic News

‹‹በቅዱሳን ምድር ረቂቅ ምስጢር›› | የአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት

‹‹በቅዱሳን ምድር ረቂቅ ምስጢር››

ባሕር ዳር፡ ጥር 15/2013 ዓ.ም (አብመድ) ከጥንት ጀምሮ ለሊት በሰዓታቱ፣ ነግ በኪዳኑ፣ ሰርክ በምህላው አምልኮተ እግዚአብሔር ይፈጸምበት የነበረ፣ በአሁኑ ዘመን ድንቅ የጥበብ አሻራ ያረፈበትንና 55 ፍልፍል ዋሻዎች የሚገኙበትን የደብረ ከርቤ ዳግማዊ ጎለጎታ ማዕዶተ ቅድስት አርሴማ አንድነት ገዳም ቢጎበኙ ሀሴትን ይጎናጸፋሉ፡፡

ገና ከኢየሱስ ክርስቶስ ልደት አስቀድሞ ኢትዮጵያ የቃልኪዳን ሀገር መሆኗ በነበያት ተነግሮላታል፣ ተከትቦላታልም። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ከአንደኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ በራሷ ሐዋርያ አማካኝነት ሃይማኖታዊ አስተምሕሮ መጀመሯም በጽሑፍ ተሰንዷል። ክርስትናን በመንበረ ጵጵስና ደረጃ አደራጅታ ሃይማኖታዊ ሥርዓቱን ለምዕመን ማድረስ የጀመረችው ደግሞ በአራተኛው ክፍለ ዘመን ነው።

ከምሥረታዋ ማግሥት ጀምሮ ቅዱሳን ነገሥታትና ቅዱሳን አበው ቴክኖሎጂን ሳይጠቀሙ ከዘመናቸው የቀደመ ሥራ ሠርተው አልፈዋል። መጥረቢያ እና ዶማ ተጠቅመው አለትን በመፈልፈል በርካታ ቤተ መቅደሶችን አንጸዋል።

ለዚህም በአራተኛው ክፍለ ዘመን በአብርሃ ወአጽብሃ የተፈለፈለው የውቅሮ አብርሃ ወአጽብሃ ቤተክርስቲያን እና በ11ኛው ክፍለ ዘመን በንጉሥ ላልይበላ በምድረ ሮሃ በአምሳለ መስቀል የታነጸው የላልይበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያን ዐብይ ማሳያዎች ናቸው።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በሥነ ጽሑፍ፣ በሥነ ሕንፃ፣ በሥነ ጥበብ፣ በታሪክ ስነዳ፣ በማሕበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና በልዩ ልዩ ዘርፎች ፈር ቀዳጅ ሆና ሀገራዊ ፈይዳ ያላቸው የልማት ሥራዎችን በመሥራት ለአያሌ ዘመናት የኢትዮጵያ ባለውለታ ሆና ቆይታለች። ልክ እንደ ጥንቱ በአሁኑ ዘመንም የሃይማኖት አባቶች ዋሻ ፈልፍለው ቤተ መቅደስን አንጸዋል፣ ከዘመናት በኋላ በስፋት ሊነገርላቸውና ሊከተብላቸው የሚችል ሀገራዊ ቅርሶችንም አፍርተዋል።

ለዚህም የደብረ ከርቤ ዳግማዊ ጎለጎታ ማዕዶተ ቅድስት አርሴማ አንድነት ገዳም አንዱ ማሳያ ነው። ይህን ገዳም ለመጎብኘት ከደብረብርሃን ከተማ በሰሜን ምዕራብ አቅጣጫ ሰባት ኪሎሜትርን መጓዝ ይጠይቃል። የደብረ ከርቤ ዳግማዊ ጎለጎታ ማዕዶተ ቅድስት አርሴማ አንድነት ገዳም በ1986 ዓ.ም ከዓለት የተፈለፈለው አባ ገብረ ኪዳን ገብረ ማርያም በተባሉ አባት ነው። ገዳሙ መነኮሳት ተሰብስበው በኢትዮጵያ ብሎም በመላው ዓለም ፍቅርና ሰላም እንዲሰፍን ይጸልዩበት ዘንድ ከዓለት የተፈለፈሉ በርካታ ቤተ መቅደሶችና ዋሻዎች መገኛ ነው።

አባ ገብረ ኪዳን ገብረ ማርያም በትውልድ ሥፍራቸው አምቦ በሃይማኖት ትምሕርት ታንጸው ካደጉ በኋላ በታላቁ የዝቋላ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም የምነና ሕይወታቸውን ጀምረዋል። በመቀጠል ወደ ጻድቃኔ ማርያም በመሄድ ሱባዔ ከገቡ በኋላ በ1984 ዓ.ም ከደብረ ገነት ሳሪያ ቅዱስ ሚካኤል (የዛሬው ኩክየለሽ ማርያም ገዳም) የኩክየለሽ ማርያምን ቤተ መቅደስ፣ ቤተ ሥላሴን፣ ቤተልሄሙን፣ የአባ ኃይለ ጊዮርጊስንና የራሳቸውን በአት ወይም የጸሎት ቤትን ጨምሮ ሰባት ዋሻዎችን ፈልፍለዋል።

ታህሳስ 05/1986 ዓ.ም ደግሞ ረድኤተ እግዚአብሔርን አጋዥ አድርገው ዓለትን በምሳር ፈልፍለው አምስት ቤተ መቅደሶችን እና 50 ዋሻዎችን በአጠቃላይ 55 ዋሻዎችን ፈልፍለው ለመንፈሳዊ አገልግሎቶች እንዲያመቹ የደብረ ከርቤ ዳግማዊ ጎለጎታ ማዕዶተ ቅድስት አርሴማ አንድነት ገዳምን አንጸዋል። ቦታው መንፈሳዊ ክብር ያገኘው በአጼ ዘርአያቆብ የንግሥና ዘመን እንደሆነ ቢነገርም በዮዲት ጉዲት ጊዜ አብያተ ክርስቲያናት ሲቃጠሉ፣ ክርስቲያኖችም ሲሳደዱ፣ ምእመኑ ከሃይማኖት መሪዎች ጋር ጽላቶችን ይዘው ተሸሽገውበታል፣ ብዙ ቅዱሳንም በቦታው ተቀምጠው እንደነበር ተመላክቷል።

ቤተ መቅደሶች እና ዋሻዎቹ ከመታነጻቸው አስቀድሞ የተሰወሩ ቅዱሳን ይኖሩበት እንደነበር፣ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ለሊት በሰኣታቱ፣ ነግ በኪዳኑ፣ ሰርክ በምህላው አምልኮተ እግዚአብሔርን ይፈጽሙ እንደነበርም በገዳሙ ከተዘጋጀ መጽሄት መረዳት ተችሏል። የሃይማኖቱ አባቶች ያገኟቸው አጽመ ቅዱሳን፣ ነዋየ ቅድሳት (ጥንታዊ ከበሮ፣ መቁጠሪያ፣ መስቀል፣ መቋሚያ፣ የጸሎት መጻሕፍትና ሌሎች መገልገያዎችም በማሳያነት ተጠቅሰዋል። የአባ ገብረ ኪዳን ገብረማርያም የመንፈስ አባት የነበሩት አባ የሺጥላ ገብረ እግዚአብሔር ቀድመው የተናገሩት ትንቢት ጊዜው ሲደርስ ተፈጸመ፣ በደብረ ከርቤ ዳግማዊ ጎለጎታ ገዳም ቤተ መቅደሶችና ዋሻዎች ተፈልፍላው አገልግሎት ሰጡ።

የአባ ገብረኪዳን ገብረማርያም ደቀ መዝሙርና በአሁኑ ጊዜ የገዳሙ አበሚኔት በመሆን እያገለገሉ የሚገኙት አባ ተክለዮኀንስ ገብረ ወልድ በጊዜው የነበረውን ድንቅ ገቢረ ተአምራት በአካል የተመለከቱ ናቸው። የገዳሙን ጥንታዊነት በማንሳት ዋሻው ሲፈለፈል እስከነበረው አጠቃላይ መንፈሳዊ እንቅስቃሴ አሰናስለው ነግረውናል።

በ20ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ አባ ገብረኪዳን ገብረማርያም ብዙ ፈተናዎችን አልፈው ዋሻ ፈልፍለው ለአገልግሎት አብቅተዋል ይላሉ የገዳሙ አበምኔት። ልዩ ልዩ የገዳሙን ክፍሎችና ፍልፍል ዋሻዎችን አሣይተውኛል፡፡

በመጀመሪያ የተመለከትነው የገዳሙን ጸበል መገኛ ነው። የገዳሙ ፀበል የሚፈልቀው ከአለት ውስጥ ተፈልፍሎ ከተሠራው ቤተ መቅደስ ውስጥ ነው። አለቱን ፈልፍለው፣ ጠባቡን ቦታ በማስፋትና ገደሉን ሜዳ በማድረግ ዋሻውን ያነጹት አባት በተመሳሳይ የፀበሉን ቦታ ፈልፍለው በማነጽ ፀበሉን ለምዕመኑ መንፈሳዊ አገልግሎት አብቅተዋል። በድንቅ ጥበብ የተሠራው የቅድሥት አርሴማ ፀበልም የገዳሙ ፀበል በሚገኝበት ቦታ በተለየ ዋሻ ውስጥ ይገኛል።

በሌላ የገዳሙ ክፍሎች ብዙ የቤተ እግዚአብሄር አገልግሎቶች የሚከወኑበትን የመጥምቀ መለኮት ዮሐንስ ገድል ቤት፣ ወደ ኢትዮጵያ ገብተው ከቦታ ቦታ ተዘዋውረው ያስተማሩት ዘጠኙ ቅዱሳን፤ በትግራይ ውስጥ ዘጠኝ ገዳማት እንዳላቸው የሚያመሰጥር ገድል የሚደረስበትን ቦታ አይተናል። የሐዋርያት አምድ እየተባሉ የሚታወቁት ጴጥሮስ፣ ያዕቆብና ዮሐንስ ሚስጥረ መለኮት በደብረታቦር እንዴት እንደተገለጸላቸው የሚያጠይቅ ክፍልም በገዳሙ ከታነጹት መካከል አንዱ ነው።

በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በስፋቱ ለየት ያለ፣ በአንድ በር ገብቶ ውስጥ ላይ ሦስት በሮች ያሉት፣ ሦስቱንም የቤተክርስቲያን ክፍሎች (ቅኔ ማህሌት፣ ቅድስትና መቅደስ) ያካተተ ፍልፍል ዋሻ የሚገኘው በዚሁ ገዳም በታነጸው የአባ ህርያቆስና ቅዱስ ኤፍሬም ቤተ መቅደስ ውስጥ ነው። ምዕመን ህይወታቸውን እንዴት በፍቅርና በሰላም መምራት እንዳለባቸው፣ በእምነታቸው ጸንተው መኖር እንዳለባቸው ለማስተማር አብርሃምና የሳራን ህይወት የሚያመሰጥረው ቤተ ሰላም (ቤተ አብርሀም) የፍልፍል ዋሻው አንዱ አካል ነው። በጸሎት ለተወሰኑ አባቶች እንዴት መራዳትና መጽናት እንዳለባቸው ገድል የሚተረጎምበት እና ማስተማሪያ ክፍልም ይገኛል።

ጥሩ ሥራ ያልሠራ የሚቀጣበትን የሚያመሰጥር የጨለማ ቦታ አለ። ይህ ክፍል እስከ 318 ሜትር ርቀት እንዳለውም የገዳሙ አስተዳዳሪ አብራርተውልናል። አምስት ቤተ መቅደሶችን እና 50 ዋሻዎችን በአጠቃላይ 55 ዋሻዎች ያሉት ገዳሙ ለገሀዱ አለም ትልቅ ትሩፋት አለው። የደብረ ከርቤ ዳግማዊ ጎለጎታ ማዕዶተ ቅድስት አርሴማ አንድነት ገዳም የመንፈስ ብርታት፣ ቁርጠኝነት፣ ጽናትና ስኬት በተግባር የታዩበት፣ ለመንፈሳዊ ብቻ ሳይሆን ለገሀዱ ዓለም ተምሳሌት የሚሆን ታላቅ ገቢር የተፈጸመበት መንፈሳዊ ቦታ ነው።

“ገዳሙ ለዓለማዊ ሕይወት ያለው አስተምህሮ በጣም ከፍተኛ ነው” በማለትም የገዳሙ አጠቃላይ ነባራዊ ሁኔታ ትውልዱ በእምነቱ ጸንቶ በየጊዜው የሚገጥሙትን ፈተና በጥበብ እንዴት ማለፍ እንዳለበት፣ ለልማት፣ መልካም ሥራ ሠርቶ ለማለፍ፣ ፍቅርን፣ አንድነትን እና መተሳሰብን ለማጎልበት፣ የዓላማ ጽናትን በመረዳት ለስኬት መድረስን እንደሚያስተምር አብራርተዋል።

ይህንን አስተምህሮ ገቢር ማድረግ ቢቻል ኢትዮጵያ ውብ፣ የለማች እንደምትሆንም ነው አባታዊ ምክራቸውን የለገሱት። የገዳሙ መንፈሳዊ እንቅስቃሴው በዚህ የተገደበ አይደለም። በገዳሙ በጸሎት ተወስነው የሚገኙ መነኮሳት ስለ ዓለም መዳን እንዲሁም ስለ ሰላም መስፈን አጥብቀው ይጸልያሉ።

በሌላ በኩል ከ1988 ዓ.ም ጀምሮ አሳዳጊ የሌላቸውን ህጻናት አሰባስቦ በመንከባከብ፣ በማሳደግና በማስተማር ወደሥራ ዓለም እንዲቀላቀሉ አብቅቷል። በአሁኑ ጊዜም ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የሚማሩ መኖራቸውንም የገዳሙ አስተዳዳሪ ገልጸዋል።

ጠዋሪ ቀባሪ የሌላቸውን አዛውንቶች በገዳሙ በማሰባሰብ የመንከባከብ ሥራም በገዳሙ ይከናወናል። ይህንን የሚያደርገው ከበግና ከወተት ላም ርባታ፣ ከእደጥበብ ሥራ፣ ከምዕመናን በሚሰባሰብ ገንዘብ፣ የተለያዩ የአትክልትና ፍራፍሬ ልማትን በስፋት በማልማትና ሌሎች የውስጥ ገቢ ማሳደጊያ ዘዴዎችን በመጠቀም ነው።

የገዳሙ መንፈሳዊና ታሪካዊ ዳራ እንዲህ በትንሹ ተወርቶ የሚያልቅ አይደለም። የገዳሙ የጥበብ ሥራ ድንቅ ነው። ረቂቅም ነው። በቦታው ለተገኘ መንፈስን ያድሳል፣ ሀሴትን ያጎናጽፋል፣ ተስፋን ያለመልማል። የኢትዮጵያውያንን የመቻል ጥግም በአግባቡ ያስረዳል። ድንቅ የጥበብ አሻራ ያረፈበትን ልዩ ስፍራ መጎብኘት መንፈስን ያድሳል።

ዘጋቢ:- ደጀኔ በቀለ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡

Source link

Related posts

በድባጤ ወረዳ ሳስ ማንደን ቀበሌ የእርቅ ስነ-ስርዓት ተፈፀመ

admin

በኢፌዴሪ አየር ኃይል የኤር ሎጅስቲክስ በህግ ማስከበር ዘመቻው ኃላፊነታቸውን ለተወጡ እና ለተቋማዊ የለውጥ ጉዞ የድርሻቸውን ላበረከቱ የሰራዊቱ አመራሮችና አባላት እውቅና ሰጠ

admin

የሕወሓት ቡድን ከስድስት ቢሊየን ብር በላይ ገንዘብ ለወንጀል መፈጸሚያነት እንዳያውል መደረጉን ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አስታወቀ፡፡

admin