79.57 F
Washington DC
June 13, 2021
Satenaw Ethiopian News/Breaking News
Amharic News

“በሥራ ዓለም አይቻልም የሚሉ ድምፆችን አትስሟቸው” የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር ፈንታ ማንደፍሮ (ዶክተር)

“በሥራ ዓለም አይቻልም የሚሉ ድምፆችን አትስሟቸው” የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር ፈንታ ማንደፍሮ (ዶክተር)

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 19/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር እና የአማራ ብረታብረት፣ ኢንዱስትሪና ማሽን ቴክኖሎጂ ልማት ኢንተርፕራይዝ የቦርድ ሰብሳቢ ዶክተር ፈንታ ማንደፍሮ ከድርጅቱ ሠራተኞች ጋር ውይይት አድርገዋል። ለሠራተኞችም የማነሳሻ ንግግር አድርገዋል። ዶክተር ፈንታ ማንደፍሮ የአማራ ብረታብረት ኢንተርፕራይዝ በሀገሪቱ ታላቁ እንዲሆን አስቡ፣ እንዲሆንም ትጉ ነው ያሉት።

ለውጥ ማምጣት የሚቻለው እያንዳንዱ ሰውና ተቋም ሠርቶ የሚያመጣው የሥራ ውጤት እንጂ ምዕናባዊ አይደለምም ብለዋል። በችግር መከበብ ለችግር መፍትሔ ማምጫ መንገድ እንጂ አምኖ ሰጥሞ መቅረት አይደለም ያሉት ዶክተር ፈንታ ትልቁ ጠላታችን የራሳችን አመለካከት መጥፎ መሆን ነው ብለዋል። ማንኛውም ሰው አመለካከቱን ማሠር አይገባም ያሉት ዶክተር ፈንታ ይቻላልን ያሳዩ አባቶች አሉ፣ እነርሱን አርዓያ ማድረግ ይገባል ብለዋል።

በአመለካከት ቀድሞ አሸንፎ መግባት እንጂ አስቀድሞ ተሸንፎ መግባት አያስፈልግምም ብለዋል። እንችላለን ካልን እንችላለን፤ እንችላለን ባልነው ልክ አለመሥራታችን ነው እንዳንችል ያደረገን ነው ያሉት። እስከመጨረሻዋ ሰዓት ተስፋ ያልቆረጠ ሰው ስኬታማ ይሆናል። በሥራ ዓለም ውስጥ ተስፋ መቁረጥ አይገባም ነው ያሉት።

በሥራ ዓለም “አይቻልም የሚሉ ድምፆችን አትስሟቸው” ብለዋቸዋል። እንዲሆን ከፈለጋችሁ ሥሩ፣ ያለ ዋጋ የሚገዛ ወርቅ የለም፣ የትም ቦታ ብትጣሉ መዋኘት እንደምትችሉ እመኑ፣ በራሳችሁ ቁሙ፣ በራሳችሁ ተማመኑ፣ በራስ መተማመን የስኬት ምንጭ ነው ብለዋል። ራሥን ሳይቀይሩ የአካባቢውን ተፅዕኖ መቀዬር አይቻልምም ነው ያሉት።

በሕይወት ለውጥ የሚያመጣው አሁንና የቀረው እንጂ በቀረው መቆዘም አይደለም ነው ያሉት። በእኛ እጆች ያሉት ዛሬና ነገ ናቸው፣ የገጠመንን ችግር እኛ በማንፈልገው መንገድ ቢሆንም ሥራን መቀጠል ይገባል ብለዋል። ተቋሙ ትልቅ ራዕይ ያለው ነው ያሉት ዶክተር ፈንታ ዋጋ በመክፈል አዲስ ተቋም በመመስረት ሕዝብን ማሻገር ይገባልም ነው ያሉት።

ቦርዶች ተቋማት እንዲጎለብቱ ድጋፍ ማድረግ መቻል አለባቸውም ብለዋል። ለውጥ ላብን ይጠይቃል በዝማሬ የሚመጣ አይደለም፣ የዛሬን ጥቅም በመተው ለነገ በማሰብ ነው ለውጥ የሚመጣው ነው ያሉት። እምነታችን ወደ ተግባር ለመቀየር እምነታችን የሚስተካከል ሥራ መሥራት ይጠይቃል ያሉት ዶክተር ፈንታ ተቋሙ የግሉንና የመንግሥትን የልማት ድርጅቶችን የማሽን ምርቶችን በቅርበት በማቅረብ የኢኮኖሚ ሽግግር መሰላል ሆኖ ያገለግላል ብለዋል። የክልሉ መንግሥትም ለተቋሙ በክትትል ድጋፍ እንደሚያደርግ አስገንዝበዋል።

የአማራ ብረታብረት፣ ኢንዱስትሪና ማሽን ቴክኖሎጂ ልማት ኢንተርፕራይዝ ተወካይ ኢንጂነር ዳንኤል ጌራ ሠራተኞች ተቋሙን በሚመጥን መልኩ ብቁ ሁነው እንዲገቡ ለማድረግ እየተሠራ ነው ብለዋል። ተቋሙ ከፍተኛ እውቀት እና ክህሎት ስለሚጠይቅ የሰው ኃይሉን ለማጠናከር እየተሠራ መሆኑን ነው የተናገሩት።

አሁን ላይ ወደ መደበኛ ሥራ ለመግባት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም አስታውቀዋል። በተቋሙ ውስጥ አዲስ መዋቅር መሠራቱንም ተናግረዋል። የተቋሙን ሠራተኞች በአመለካከት ለመገንባት ተከታታይ ማነቃቂያዎች እና ውይይቶች እየተደረጉ ስለመሆናቸውም ገልጸዋል።

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ተቋሙ በታለመለት ልክ እንዳይሄድ አድርጎታል ያሉት ተወካይ ሥራ አስፈፃሚው በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ወደ ሀገራቸው እንደሄዱ ያልተመለሱ ሠራተኞች ስለ መኖራቸውም ተናግረዋል። የማሽን ተከላ ሥራውን የሚፈፅሙትና ወደ ሀገራቸው ቻይና ሄደው ያልተመለሱትን ሠራተኞች በበይነ መረብ እያገኙ የማሽን ተከላ ሥራቸውን እያከናወኑ እንደሆነ ተናግረዋል።

413 ማሽነሪዎችን ለማምረት ውል ይዘው እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውንም አስታውቀዋል። የትራክተር ምርቶችን በ2014 ዓ.ም ለማድረስ የሚያስችል ሥራ እየተሠራ መሆኑን ነው የተናገሩት።

የአማራ ብረታብረት፣ ኢንዱስትሪና ማሽን ቴክኖሎጂ ልማት ኢንተርፕራይዝ ምክትል ሥራ አስፈፃሚ ወርቁ ያየህ በተቋሙ አዲስ አደረጃጀትና የሰው ኃይል አለ ብለዋል። ተቋሙን ውጤታማ ለማድረግ ከፍተኛ እውቀት እንደሚጠይቅ የተናገሩት ምክትል ሥራ አስፈጻሚው ባለፉት ዓመታት እውቀት ሲፈጠርበት ቆይቷል ነው ያሉት።

የመምራት ብቃት ያላቸው መሪዎችን ማካተታቸውንም ተናግረዋል። የተቋሙን ሠራተኞች በተለያዩ መንገዶች በማነቃቃት በሥራቸው ውጤታማ እንዲሆኑ የማድረግ ሥራ እንደሚሠራም ገልጸዋል።

የአማራ ብረታብረት፣ ኢንዱስትሪና ማሽን ቴክኖሎጂ ልማት ኢንተርፕራይዝ የባሕር ዳር ፋውንደሪ ማሽነሪ ፋብሪካ ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ዘላለም በላይ በቁጭት የተቋቋመ ተቋም መሆኑን እና በቆይታውም ሦስት ፋብሪካዎችን ማቋቋሙን ገልጸዋል። በሀገሪቱ ውስጥ ከሚገኙ ተመሳሳይ ተቋማት የተሻለ የሰው ኃይልና ማሽን ያለው ነው ብለዋል።

የባሕር ዳር ፋውንደሪ ፋብሪካ በወር 10 ሺህ ቶን ብረት ማቅለጥ ይችላል ብለዋል። አብዛኞቹ ማሽኖች ደረጃቸውን የጠበቁና በኮምፒውተር የታገዙ ናቸው። ድርጅቱ በሥሩ በርካታ ድርጅቶችን መፍጠር የሚችል ድርጅት ነውም ተብሏል።

የአማራ ብረታብረት፣ ኢንዱስትሪና ማሽን ቴክኖሎጂ ልማት ኢንተርፕራይዝ ከ700 በላይ ማሽኖች አሉት። የብረታብረት ኢንጂነሪግ ተቋማት ተጠቃሚ እንዲሆኑ በትኩረት የሚሠራ ነው። እስካሁን ድረስ በሀገር ውስጥ የማይመረቱ መገጣጠሚያዎችን ያመርታል። ሙሉ ለሙሉ ወደ ሥራ ሲገባ የክልሉን ብሎም የኢትዮጵያውያን የኢኮኖሚ ሽግግርን ከፍ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል። ብቁ የሆነ ቴክኖሎጂ ማምረት ብቻ ሳይሆን ብቁ የሆነ የሰው ኃይል የሚያፈልቅም እንደሆነ ተመላክቷል።

ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡

Source link

Related posts

ቡና ባንክ በተለያዩ መርሃ ግብሮች ዕጣ የወጣላቸውን ደንበኞቹን ሸለመ

admin

በፋና ላምሮት የድምፃዊያን ውድድር ዮናታን ዳመነ አንደኛ በመውጣት የ200 ሺህ ብር አሸናፊ ሆነ

admin

አቶ ተኮላ አይፎክሩ የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር ሆነው ተሾሙ | Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider

admin