66.9 F
Washington DC
June 15, 2021
Satenaw Ethiopian News/Breaking News
Amharic News

“በሞትን አትግፉን፣ ብትችሉ ካሳ ባትችሉ ግን ዳግም ግፍ በቃን” የካድራወንዝ ከተማ ነዋሪዎች

“በሞትን አትግፉን፣ ብትችሉ ካሳ ባትችሉ ግን ዳግም ግፍ በቃን” የካድራወንዝ ከተማ ነዋሪዎች

ባሕር ዳር፡ ሰኔ 04/ 2013 ዓ.ም (አሚኮ) አሸባሪው ትህነግ በግፍ የጨፈጨፋቸው የካድራወንዝ (ማይካድራ) ከተማ ነዋሪዎች የትህነግን ግፍ በማውገዝና የውጭ ጣልቃ ገብነትን በመቃወም ሰልፍ አካሂደዋል። የግፍ ፅዋ የፈሰሰባት፣ የንጹሃን ደም የተደፋባት፣ የጨካኞች የመጨረሻው የጭካኔ ጥግ የታየባት፣ እናት የልጇ አንገት ሲቆረጥ፣ ያዘለችው ልጅ ከጀርበዋ ሲወርድ የማስቆም እድል አልነበራትም። አንጀቷ እያረረ፣ ፊቷ እየጠቆረ የልጇን አንገት ሲቆረጥ ተመለከተች እንጂ።

“ክፉ ሰው ከክፉ ልቡ መዝገብ ክፉ ነገር ይናገራል መልካም ሰው ከመልካም ልቡ መዝገብ መልካም ነገር ያኖራል” እንዳለ ክፉዎች ከክፉው ልባቸው ውስጥ የቋተውን ጥላቻ በንጹሃን ላይ ደፉት። የበረሃዋ ከተማ ካድራወንዝ (ማይካድራ) በሀዘን ተዋጠች፣ ጎዳናዎቿ በዋይታ ተመሉ፣ ደም ፈሰሰ፣ ምድሯ አዘነች፣ ሰማይ ታዘበች፣ ገዳዮች እሳት የያዘውን መቅረብ አልቻሉም ነበርና ፊታቸውን ያዞሩት እሳት ወደ አልያዙት ነበር። ፈሪ ከጀግና ፊት አይቆመም፣ የትህነግ ቡድንም ያደረገው ይህን ነበር። የጀግናው ግንባር ሲለበልበው ፊቱን አዙሮ ንፁሃንን ጨፈጨፈ። ምን ቢጨክኑ ይሆን ያን ያደረጉት? ከተማዋ በሀዘን ተመላች፣ እናቶች እንባቸው እንደ ቦይ ፈሰሰ፣ አንጄታቸው ተላወሰ፣ የጣዕረሞት ደምፅ የበዛባት፣ የጭንቅ ጭንቅ የታየበት ቀን ነበር። ከተማዋን የሀዘን ጨለማ ዋጣት፣ አካባቢውን ድምፅ አናወጣት፣ ክቡር የሰው ልጆች ፈትፍተው ባጎረሱ፣ አውልቀው ባለበሱ፣ ቦታ ለቀው ባሳረሱ፣ የግፍ ግፍ ተፈፀመባቸው።

አባት ከልጆቹ ፊት ተገድሏል፣ እናት ከፊቷ ልጇ ተሰውቷል። ይህን ግፍ ግን ያየላቸው አልነበረም። ሚስት አጋሯን ተጠነጥቃለች። ወልቃይት ጠገዴ የግፍን አይነት ቆጥሯል፣ በመከራ ውስጥ ኖሯል። በካድራ ወንዝ የወረደው መከራ የፈሰሰው የደም ጎርፍ ሳይጠራ ወልቃይት ጠገዴ ላይ ወሳኝ ነን የሚሉት በዝተዋል፣ እጃቸውን ሊያስረዝሙ የሚፈልጉት ተበራክተዋል። እውን ለዚያ በግፍ ለተቀላ ማኅበረሰብ ይህ ይገባዋልን? ቢቻል ካሳ ባይቻል ግን የጠየቀው ማንነት ያንሰዋልን? የካድራወንዝ ነዋሪዎች የደረሳበቸው የግፍ ማዕበል ሳይደርቅ፣ ከተማዋን ያደማነው የሀዘን ድባብ ሳይገፈፍ ለሌላ ሀዘን ሊዳርጋቸው የሚከጅለውን የውጭ ጣልቃ ገብነት ለመቃወምና የአሸባሪው የትህነግን ግፍ ለማውገዝ አደባባይ ወጥተዋል።

ነዋሪዎቹ በሰልፋቸው አሸባሪው ትህነግ በወልቃይት ጠገዴ ያደረገው ጭፍጨፋ ይታወቅልን፣ በካድራ ወንዝ ያደረሰው የዘር ማጥፋት ወንጄል ይታወቅ፣ በማንነታችን አንደራደርም፣ ክብራችን የነካ ፍፃሜው ሞት ነው፣ ኢትዮጵያ የሰላም ሕዝብ መገኛ እንጂ የጦርነት መገኛ አይደለችም፣ የሀገራችን ሉዓላዊነት ማንም አይደፍርም፣ አሜሪካ እጇን ታንሳ የሚሉና ሌሎችን መልእክቶች አስተላልፈዋል።

ነዋሪዎቹ “በሞትን አትግፉን፣ ብትችሉ ካሳ ባትችሉ ግን ዳግም ግፍ በቃን፣ ከበደል ላይ በደል ይበቃናል፣ ከጭቆና የወጣን ሕዝብ ወደ ጭቆና መመለስ የማይታሰብ ነው” ሲሉም መልእክት አስተላልፈዋል።

የአማራ ልዩ ኃይል ወልቃይት ጠገዴ እንጂ ትግራይ ውስጥ የለም፣ የውጭ አካላት በሌለ ነገር ጫና ለማድረስ የምታደርጉት ጥረት አይሳካምም ነው ያሉት። በወልቃይት ጠገዴ ዘርን መሰረት ያደረገ ወንጄል ሲፈፀም እንደኖረም ገልጸዋል። አባታቸውን በግፍ የተነጠቁ ልጆችን ያሳደጉ የወልቃይት እናቶች ስለመኖራቸውና ልጆቹ ከፍ ሲሉም በአማራነታቸው ብቻ የአባቶቻቸው እጣ የደረሳባቸው ብዙዎች መሆናቸውንም ተናግረዋል።

ጣልያን የካቲት 12 በአዲስ አበባ ላይ እንዳደረሰችው ግፍ ሁሉ አሸባሪው ትህነግ በማይካድራ ነዋሪዎች ላይ ፈፅሟል ነው ያሉት። ማይካድራ የጥፋት መርከብ ወደብ ናትም ብለዋል። ከአሸባሪው ትህነግ ጎን የሚሰለፍ የትኛውም ኃይል የትናንቱ የመከራ ዘመን ዳግም እንዲደገም የሚፈልግ ስለመሆኑም ተናግረዋል።

መራር ዋጋ ተከፍሎ የተገኘውን ነፃነት የሀገር ውስጥም ሆነ የውጭ ኃይል ጣልቃ ገብቶ በማንነታችሁ እኔ ልወስን ሲል አንፈቅድምም ብለዋል። የወልቃይት ጠገዴ አማራዎች ያስመለስነው ማንነት እንጂ የወሰድነው መሬት የለንምም ነው ያሉት።

የአማራ ልዩ ኃይል ከወልቃይት ጠገዴ ይውጣ ማለት ከነውርም በላይ በማይካድራ ሰማእታት ላይ መሳለቅና ፈፅሞ አንቀበልም ብለዋል። “የሞትነው እኛው፣ በማንነታችን ተለይተን የተጨፈጨፍነው እኛው፣ ዙሪያ መለስ ተበዳዮች እኛው ሆነን ሳለን በውጭ ሚዲያዎች በዘመቻ የሐሰት ዜና እየተሠራብን ጩኸታችን ሊቀሙን ለሚሞክሩ መልሳችን አንድ ነው። እውነት አንዲት ናት ብትቀጥንም አትበጠስም በደላችን እስኪታወቅልን መታገላችን እንቀጥላለን” ነው ያሉት። የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ከሳ እንደሚሻም ገልጸዋል።

በግፍ ቀያቸውን ለቀው የኖሩ የወልቃይት ጠገዴ ተወላጆች ወደ ቃያቸው እንዲመለሱ የፌደራል መንግሥትና ሌሎች አካላት እንዲሠሩ ጠይቀዋል። ስለ ወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ማንነት ከራሱ በላይ ማንም ምስክር የለምም ብለዋል።

ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ- ካድራወንዝ (ማይካድራ)

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡

Source link

Related posts

“የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ 10ኛ ዓመት በተለያዩ ዝግጅቶች ይከበራል” የአማራ ክልል የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት

admin

“አሜሪካ ከመታሰሷ አስቀድሞ ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ ሕዝብ የሚኖርበት፣ መንግሥት ያለበት የሰሜን በጌምድር ጠቅላይ ግዛት ሆኖ የኢትዮጵያ ምድር መሆኑ ይታወቃል” ታሪክ አዋቂ

admin

በክልሉ የከተራና ጥምቀት በዓል ያለ የፀጥታ ችግር እንዲከበር ዝግጅት መደረጉን ፖሊስ አስታወቀ

admin