70 F
Washington DC
April 10, 2021
Satenaw Ethiopian News/Breaking News
Amharic News

በምርት ማሳደግ ላይ የተሠራው ሥራ ገበያ ትስስር ላይ ባለመተግበሩ ኪሳራ እያጋጠማቸው እንደሆነ አርሶ አደሮች ተናገሩ።

በምርት ማሳደግ ላይ የተሠራው ሥራ ገበያ ትስስር ላይ ባለመተግበሩ ኪሳራ እያጋጠማቸው እንደሆነ አርሶ አደሮች ተናገሩ።

ባሕር ዳር፡ የካቲት 29/2013 ዓ.ም (አብመድ) የተሻሻሉ አሠራሮችን በአነስተኛ መሬት በመተግበር ባለሀብት መሆን እንደሚቻል በተግባር ማሳየት መቻላቸውን በደቡብ ጎንደር ዞን ፎገራ ወረዳ የአንጎት ቀበሌ አርሶ አደሮች ተናግረዋል። አርሶ አደር አለምነው በሬ እንዳሉት በአካባቢያቸው የሚፈሱ ወንዞችን በመጥለፍ በዓመት እስከ ሦስት ጊዜ በመስኖ በማልማት ውጤታማ ሆነዋል። በተለይም ደግሞ የተሻሻለ የሽንኩርት ዘርን በመስመር በመዝራት እና ማዳበሪያ በመጠቀም ከዚህ በፊት ከአንድ ሄክታር መሬት ይገኝ ከነበረው ከእጥፍ በላይ ምርት ማግኘታቸውን ነው የነገሩን።

ሌላው አርሶ አደር ሢሳይ አገኘሁ እንደገለጹት ለ10 ዓመታት ያህል በመስኖ ልማት ቢሰማሩም የመጀመሪያዎቹን 7 ዓመታት ዘልማዳዊ አሠራር በመከተላቸው ከእጅ ወደ አፍ ባለፈ ተጠቃሚ መሆን አልቻሉም። ባለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ ግን የተሻሻሉ አሠራሮችን በመተግበራቸው የተሻለ ምርት በማግኘታቸው 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የከተማ ቦታ መግዛት ችለዋል። በዚህ ዓመት ደግሞ በአንድ ሄክታር ተኩል መሬት በመጀመሪያ ዙር መስኖ 42 ኩንታል ነጭ ሽንኩርትና ጤፍ ማግኘታቸውን ነግረውናል። አርሶ አደሮቹ ለሁለተኛ ዙር መስኖ እርሻ የማሳ ዝግጅት እያደረጉ ይገኛሉ። በመስኖ ልማት የምርት ጭማሪ ቢታይም በዚህ ወቅት የገበያ ችግር አጋጥሞናል ነው ያሉት።

የሊቦ ከምከም ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት የአትክልትና ፍራፍሬ መስኖ አጠቃቀም ቡድን መሪ ነጋ ወንዱ በወረዳው 8 ሺህ ሄክታር መሬት በአንደኛ ዙር መስኖ ተሸፍኗል፤ አጠቃላይ በመስኖ ከተሸፈነው 62 በመቶ አትክልት፣ 23 በመቶ አዝርዕት፣ ቀሪው ደግሞ ጥራጥሬና ቅመማቅመም ሰብሎች ናቸው። ከ56 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች በልማቱ ተሳትፈዋል ብለዋል። 870 ሺህ ኩንታል የሚገመት ምርት ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል። የግብርና የኤክስቴንሽን ስርጸት ማደግ እና ከመስኖ የሚገኘው ገቢ መጨመር ለመስኖ እንቅስቃሴው ማደግ በምክንያትነት ተቀምጠዋል።

May be an image of grass

በ2013 ዓ.ም የርብ ግድብ ውኃ በመለቀቁ እስከ ጣና ሐይቅ የሚገኙ የወረዳው ቀበሌዎች ያለምንም የውኃ እጥረት በሠፊው እያመረቱ ነው። ይሁን እንጂ ገባር ወንዞች እና ምንጮችን አርሶ አደሩ ከአቅም በላይ እያመረተባቸው ስለሚገኝ የውኃ እጥረት አጋጥሟል ብለዋል። ችግሩንም ለመፍታት ከወንዞችና ግድቦች በተጨማሪ አርሶ አደሮች የከርሰ ምድር ውኃን ጭምር በሠፊው በመጠቀም ላይ እንደሚገኙ ነግረውናል።

በክልሉ በተመሳሳይ ጊዜ ተመሳሳይ ምርት መመረቱ እና በሀገር አቀፍ ደረጃ በነበረው የሠላም እጦት ምክንያት የገበያ ችግር ማጋጠሙን ቡድን መሪው ገልጸዋል። ችግሩን ለመፍታት 420 ሺህ ኩንታል በግብይት ለማስተሳሰር ከንግድና ገበያ ልማት እንዲሁም ከማኅበራት ጋር የምርት ልየታና ገበያ ጥናት በቅንጅት እየተሠራ እንደሚገኝም አስታውቀዋል። ለዚህም 17 የገበያ ቡድኖች ተደራጅተዋል ነው ያሉት። በቀጣይ ምርቱ ሳይበላሽ ጊዜ ጠብቆ ለገበያ ለማቅረብ የሚያስችሉ ዘመናዊ ማቀዝቀዣ መጋዝኖች ማዘጋጀት የመንግሥት ቀዳሚ ተግባር እንደሚሆን ጠቁመዋል። በወረዳው በ2013 ዓ.ም የመጀመሪያ ዙር መስኖ ልማት ከ13 ሺህ 100 ኩንታል በላይ ማዳበሪያ እና ከ7 ሺህ 100 ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር ጥቅም ላይ ውሏል።

የደቡብ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ ምክትል ኀላፊ በለጠ ተስፋዬ በዞኑ በአንደኛ ዙር መስኖ ከ30 ሺህ 600 በላይ ሄክታር መሬት መልማቱን ገልጸዋል። ምርታማነትን ለማሳደግም የተሻሻሉ አሠራሮችን እና የቴክኖሎጂ ውጤቶች ተግባራዊ ተደርገዋል ብለዋል። በዚህም አጠቃላይ በመስኖ ከለማው መሬት ውስጥ 90 በመቶ የሚሆነውን በመስመር ለመዝራት ታቅዶ 83 በመቶ ማሳካት እንደተቻለም ነግረውናል። ከ46 ሺህ በላይ ኩንታል ማዳበሪያ እና ከ14 ሺህ 800 በላይ ኩንታል ምርጥ ዘር ጥቅም ላይ ውሏል ነው ያሉት። ክልሉ ደግሞ ከአራት እስከ መቶ ሄክታር መሬት የማልማት አቅም ያላቸው 245 የውኃ መሳቢያ ጄኔሬተሮች ድጋፍ አድርጓል ብለዋል።

የገበያ ትስስር ችግሩን ለመፍታት ከነጋዴዎች ጋር የማስተሳሰር ሥራ ቢሠራም በተፈለገው መጠን ችግሩን መቅረፍ አለመቻሉን ነው ምክትል ቢሮ ኃላፊው የገለጹት። ይህ ደግሞ ምርት ማሳደግ ላይ የተሠራውን ሥራ ያህል የገበያ ትስስር ላይ አለመተግበሩ ማሳያ መሆኑን አቶ በለጠ አንስተዋል። በቀጣይ የሚያጋጥመውን የገበያ ችግር ለመፍታት ከ’አግሪካልቸራል ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ’ ጋር በመተባበር በወረታ ከተማ የማቆያ መጋዝን ለመገንባት የቦታ ርክክብ መደረጉን አንስተዋል።

ፎገራ፣ ደራ፣ ሊቦ ከምከም እና እብናት ወረዳዎች በዞኑ ከፍተኛውን የመስኖ እርሻ ልማት ድርሻ የሚይዙ አካባቢዎች መሆናቸውን ከዞኑ ግብርና መምሪያ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሰራ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡

Source link

Related posts

የፀጥታው ምክር ቤት በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ገንቢ ሚና ሊጫወት እና ከኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ጎን ሊቆም ይገባል – የኢትዮጵያ አሜሪካውያን የዜጎች ምክር ቤት

admin

“ኢትዮጵያ ድርድሩ በአፍሪካ ሕብረት በኩል እንዲካሄድ የያዘችው አቋም ለሕብረቱ ያላትን ክብርና እውቅና የሚያሳይና የሚደነቅ ነው” መሀመድ አል አሩሲ አክቲቪስትና የፖለቲካ ተንታኝ

admin

ጠቅላዩ “የኦሮሞን ጥያቄ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ እየሰራን ነው” ሲሉ እኛ የሚገባን….?!? (ተፈራ ወንድማገኝ)

admin