27.09 F
Washington DC
March 8, 2021
Satenaw Ethiopian News/Breaking News
Amharic News

በመስኖ ምርት ማግኘት ቢጀምሩም ገበያ ለማድረስ የመንገድ ችግር ስጋት እንደሆነባው አርሶ አደሮች ተናገሩ

አሶሳ ጥር 17 / 2013( ኢዜአ) በመስኖ እርሻ የተሻለ ምርት ማግኘት ቢጀምሩም ወደ ገበያ ለማድረስ የመንገድ ችግር ስጋት እንደሆነባቸው በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ባምባሲ ወረዳ አርሶ አደሮች ተናገሩ፡፡

የመስክ ምልከታ በተካሄደበት ወቅት ከወረዳው  አርሶ አደሮች መካከል ወጣት ሐንጉግ ሙሳ ለኢዜአ እንዳለው በመስኖ እርሻ አራት ሄክታር መሬት ላይ ሽንኩርት አልምቷል፡፡

ከአካባቢው ምርት ወደ ገበያ የሚቀርበው በሰው ትከሻ ረጅም መንገድ ተጓጉዞ እንደሆነ ጠቅሶ  በመንገድ ችግር ባመረቱት ልክ ተጠቃሚ ሳልሆን እቀራለሁ የሚል ስጋት እንዳደረበት ተናግሯል፡፡

በልማቱ ለሌሎች ወጣቶችም አርአያ በመሆን መደገፍ እንደሚፈልግ የተናገረው ወጣቱ  ዋና ችግራቸው የመንገድ እጦት መሆኑን ገልጿል።

እስከመጪው ግንቦት ወር ሶስት ጊዜ የተሻለ ለማምረት አቅዷል።

አርሶ አደር ኡመር አሸሪፍ በበኩላቸው በብድር ገንዘብ ያለሙትን  የሽንኩርት ምርት በቅርብ ቀን መሰብሰብ እንደሚጀምሩ አስረድተዋል፡፡

በሄክታር 200 ኩንታል የሚጠጋ ምርት እንደሚያገኙ የሚጠብቁ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ዋነኛ ችግራችን መንገድ ነው፤ አሁን መንግስትን የምንጠይቀው ችግራችንን ቀርፎልን በተሻለ ሠርተን ከድህነት እንድንወጣ እንዲያበረታታን ነው ብለዋል፡፡

የክልሉ ግብርና እና ተፈጥሮ ሃብት ቢሮ ሃላፊ አቶ ባበክር ከሊፋ በበኩላቸው እየጨመረ የመጣውን የአርሶ አደሩን በመስኖ የሚያመርተውን   የአትክልት ምርት ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እና ሌሎችም የገበያ አመራጮች ትስስር ለመፍጠር ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ይህም ሆኖ በመንገድ እጦት ወደ ገበያ ሳይቀርብ የሚቀርብ ከፍተኛ የአትክልት ምርት አለ ብለዋል፡፡

በገጠር ተደራሽ መንገድ ፕሮግራም  በአካባቢው መንገድ  በሚፈለገውን ያክል ሳይከናወን መቅረቱን ጠቅሰው  በቀጣይ እንዲሠራ ቢሮው የበኩሉን ጥረት እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሃሰን የመንገድ ተደራሽነት ጥያቄ የአርሶ አደሩ ብቻ ሳይሆን የክልሉ መንግስት መሠረተ ልማትን የማዳረስ ተቀዳሚ ትኩረት ነው ብለዋል፡፡

ባምባሲ ወረዳን ጨምሮ በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች በገጠር ተደራሽ መንገድ ፕሮግራም የተከናወኑ የገጠር መንገዶች እና አነስተኛ ድልድዮች በብልሹ አሰራር ምክንያት ተጀምረው የቀሩ እንዳሉ ጠቅሰው አንዳንዶቹ ደግሞ በበጋ ብቻ አገልግሎት እንደሚሰጡ ጠቁመዋል፡፡

አደረጃጀት፣ በጀት አጠቃቀም እና ተያያዥ ችግሮች የታዩበት ፕሮግራሙን  ሲመሩ በነበሩ አካላት ላይ ህጋዊ እርምጃ እንደተወሰደ ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል፡፡

የወረዳው አርሶ አደሮች ጥያቄ የቀረቡበትን አካባቢ ጨምሮ አስቸጋሪ የሆኑ የገጠር መንገዶችን የክልሉ መንግስት ተኩረት ሰጥቶ ይሰራል ብለዋል፡፡

በመስኖ እርሻ ውጤታማ እየሆኑ የሚገኙ አርሶ አደሮች ወደ ከተሞች በመምጣት በተሻለ ኢንቨስትመንት እንዲሠማሩ ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር በመነጋገር ከስምምነት መደረሱን ጠቅሰዋል፡፡

የወረዳው ህብረተሰብ ውጤታማ የሆነው በአካባቢው ሠላም በመኖሩ እንደሆነ የገለጹት አቶ አሻድሊ በዘላቂነት ከድህነት እንዲወጡ ከመንግስት እና ጸጥታ ሃይሉ የበለጠ ተቀናጅተው እንዲሰሩም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

Source link

Related posts

“ሱዳን በጉልበት የያዘችውን ቦታ ለቅቃ እንድትወጣ የኢትዮጵያ መንግሥት የጊዜ ገደብ ሊኖረው ይገባል” የታሪክ ምሁር

admin

ሱዳን ኢትዮጵያን የወረረችባቸው 10 ምክንያቶች (መስፍን ሙሉጌታ)

admin

“የሴቶችን መብት የሚያከብር ማኅበረሰብ እንገንባ!”

admin
free web page hit counter