73.2 F
Washington DC
June 14, 2021
Satenaw Ethiopian News/Breaking News
Amharic News

“በሐበሻ ማንም የማይበደልበት ሥርዓትን ያቆመ ንጉሥ አለ” ነብዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ)

“በሐበሻ ማንም የማይበደልበት ሥርዓትን ያቆመ ንጉሥ አለ” ነብዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ)

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 05 /2013 ዓ.ም (አሚኮ) በአሁኑ ጊዜ በጆኦ ፖለቲካል አቀማመጡ “የአፍሪካ ቀንድ” በሚል ስያሜ የሚጠራው አካባቢያዊ ቀጣና ቀደም ባለው ዘመን ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ አንድምታ በተቸረው አጠራር ዘይላ እና ሐበሻ በሚሉ መጠሪያዎች ይታወቅ እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ያወሳሉ፡፡

ቀጣናው ኢትዮጵያን፣ ኤርትራን፣ ጅቡቲን፣ ሱዳንን እና ሶማሊያን የሚያጠቃልልም እንደነበር ይነገራል፡፡ አካባቢውን የአረቡ ዓለም ሀገራት “አልሐበሻ” ሲሉት ምዕራባዊያን ደግሞ “አቢሲኒያ” እያሉ ይጠሩታል፡፡ በዚሁ አካባቢ የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ቀደምት እና ስልጡን የነበረ ዘይላ የሚባል የኢስላማዊ መሳፍንት ሥርዓት ዘርግተው እንደነበርም ይነገራል፡፡ በመካከለኛው ዘመን በእነዚህ ሃይማኖታዊ ሥርዓተ መንግሥታት መካከል ተደጋጋሚ ጦርነቶች ይስተናገዱ ስለነበር ቋሚ የሆነ ድንበርም አልነበራቸውም፡፡

የአካባቢው መልካ ምድራዊ አቀማመጥ ከአፍሪካ ጣራ ራስ ደጀን እስከ አፍሪካ ወለል ዳሎል፤ ከታላቁ የዓባይ ሸለቆ እስከ አዋሽ ሰርጥ በርሃማ ቦታዎችን የሚያካልል በመሆኑ ሕዝቦቹ ከባህል እስከ አኗኗር ዘይቤ፤ ከአምልኮ ስፍራዎች እስከ ሥነ ልቦናዊ ውቅር ድረስ ጉራማይሌ እንደሆነ እልፍ ዘመናትን አስቆጥሯል፡፡

በአጭሩ የአፍሪካ ምሥራቃዊ ሰርጥ ምድር ክርስቲያናዊ ስርወ መንግሥታት የሆኑት ሐበሾች እና ኢስላማዊ አስተምህሮን የሚከተሉት የዘይላ ሙስሊሞች የሚጋሩት የድንበር አካባቢ ነበር፡፡ ለበርካታ ዘመናት በተለይም በመካከለኛው ዘመን እነዚህን ጎሳዎች አንድ አድርጎ የሚመራ ሉዓላዊ መንግሥት ባለመኖሩ በርካታ አካባቢያዊ መሳፍንቶች ተፈጥረውበት ነበር፡፡ አካባቢው ዓለምን አጃይብ ያሰኙ እና ያስደመሙ ከሀረር እስከ አፋር፣ ከዳውሮ እስከ ባሌ፣ ከደራ እስከ ሽዋ፣ ከጎንደር እስከ ላስታ፣ ከአክሱም እስከ ሀረር የተዘረጉ ስልጣኔዎችን እና የንግድ መስመሮችን ዘርግቶ አልፏል፡፡

የክርስቲያኖች እና ዓረቦች የሁለትዮሽ ግንኙነት ከእስልምና ሃይማኖት መስፋፋት በፊት ዘመናትን ያስቆጠረ እንደነበር ታሪክ ይገልጻል፡፡

ነብዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) በተከታዮቻቸው እና ቤተሰቦቻቸው ላይ እጅግ የከፋ ጭቆና፣ ሰቆቃ እና ስቃይ በመበርከቱ ወደ ሐበሻ ምድር እንዲሸሹ ማዘዛቸው ይነገራል፡፡ “በሐበሻ ማንም የማይበደልበት ሥርዓትን ያቆመ ንጉሥ አለ” ማለታቸው የአካባቢውን ቀደምት ስልጡን ሥርዓት ያመላክታል፡፡ ሙስሊሞች የሐበሻ ምድር የጅሀድ አቅጣጫ እና ትኩረት እንዳትሆን የመወሰናቸው ሚስጥርም የዚሁ መልካም ግንኙነት ውጤት ተደርጎ ይወሰዳል፡፡

በ14ኛው፣ 15ኛው እና 16ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ላይ የተካሄዱት የአውሮፓ የመስቀል ጦርነቶች ለቀጣናው መልካም ግንኙነት ሳንካ መፍጠሩ ግን አልቀረም ነበር፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የየወቅቱን ፖለቲካዊ ነፋስ እና ቅቡልነት እያየች ካባ ቀያሪዋ ሰሜን አፍሪካዊቷ ሀገር ግብፅ በአፍሪካ ቀንድ ከባቢ ለሚኖሩት የሁለቱ ሃይማኖቶች ተከታይ ሕዝቦች መልካም ግንኙነት ቅርቃር መሆኗ አይካድም፡፡ በተለይም ከ13ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ኢትዮጵያን በአራቱም አቅጣጫ የሚያዋስኗት ሀገራት እና ሕዝቦች እስልምናን ከተቀበሉ በኋላ የዓባይ ውኃን ሙሉ በሙሉ የመቆጣጠር ፍላጎት ያላት ግብፅ የኢትዮጵያን የውስጥ ሰላም በማደፍረስ አንድነቷን ለማዳከም አይነተኛ ስልት ለማድረግ ስትታትር ተስተውሏል፡፡

እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጳጳሳትን ሾማ የምትልከው ሀገር ግብፅ ሆና ሳለ ለራሷ የምትሰጠው ስያሜ እና ኢትዮጵያ ላይ የምትለጥፈው ታርጋ በተቃርኖ የተሞላ መሆኑ ሌላው ማሳያ ነበር፡፡

በአፍሪካ ቀንድ ቀጣና በተለይም በኢትዮጵያ እና አካባቢው የከተሙ ነባር ሕዝቦች ምስቅልቅል ህይዎትን እንዲያሳልፉ የውጭ ኀይሎች ተፅዕኖ ቀላል አልነበረም፡፡ ኢትዮጵያን በአራቱም አቅጣጫ በሚያዋስኗት ሀገራት በሙሉ በሙስሊም ሕዝቦች ላይ የደረሰው ጭቆና እና እንግልት ቀላል ያልሆነ ቁጥር ያለው ሕዝብ ወደ አፍሪካ ቀንድ እና ምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት በተለይም ኢትዮጵያ እንዲሰደዱ አድርጓቸዋል፡፡ በወቅቱ ደግሞ ኢትዮጵያ በምሥራቁ እና የአረቡ ዓለም ሀገራት የነበራት መልካም ሥም እና ዝናም የዳበረ እንደነበር ልብ ይሏል፡፡

በሌላ በኩል በተለይም ከ940 እስከ 980 ዓ.ም ድረስ አካባቢውን የተቆጣጠረችው ዩዲት በሕዝበ ክርስቲያኖች ላይ ያደረሰችው የከፋ ጭፍጨፋ ነዋሪዎቹን ቆዳቸው በመከራ የደነደነ እንዲሆን አስገድዷቸዋል፡፡

ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች ከሌሎች የሚለዩት እስልምናቸውን ከኢትዮጵያዊነታቸው ጋር አጣጥመው የሚያራምዱ መሆናቸው ነው፡፡ ኢትዮጵያ በዘጠነኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጨረሻ ጀምሮ የቀጣናውን የባሕር ዳርቻዎች ሁሉ መቆጣጠር ችላ ነበር፡፡ በ10ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ደግሞ በቀጣናው ከፍተኛ የንግድ እና የባሕር በር አውራ መሆኗን ያልወደዱት ምዕራባዊያን በሌላ የተልዕኮ ግጭት እንድትዳከም ይሹ ነበር፡፡

በ13ኛው ክፍለ ዘመን ደግሞ በዘይላ እና ዳህላክ ደሴቶች ውስጥ የሚኖሩ ሕዝቦችና መሪዎቻቸውም ሐበሾች እንደነበሩ ይነገራል፡፡ በወቅቱም ከኢትዮጵያ ጀምሮ እስከ ሞዛምቢክ እና ዛምቤዚ ወንዝ ድረስ የኢትዮጵያዊያን ሙስሊም እና ክርስቲያን ሕዝቦች አንድነት በንግድ እንቅስቃሴ ጎልቶ የወጣበት ጊዜ ነበር፡፡

በኢትዮጵያዊያን ሙስሊም እና ክርስቲያኖች መካከል ግጭት ለመፍጠር የተለያዩ ሙከራዎች ተደርገዋል፡፡ በተለይ ግብፅ የዓባይን ውኃ ብቻዋን ለመጠቀም ካላት ፍላጎት የመነጨ ግጭቶችን ለመፍጠር የጣረች ሲሆን ምዕራባዊያን ደግሞ በቀይ ባህር አካባቢ የነበሩ ሙስሊም ኢትዮጵያዊያንን ለማስለቀቅ ያደረጉት ሙከራ ተጠቃሽ ነው፡፡

የታሪክ ድርሳናት በየዘመናቱ ከተፈጠሩት ኹነቶች መካከል ከሞላ ጎደል ከትበው ካስቀሩት እውነት የምንረዳው ነገር ቢኖር ከአፍሪካ ሀገራት ግብፅ እና ከቀሪው ዓለም ምዕራባዊያን የቀጣናውን ጆኦ ፖለቲካል የበላይነት ለመቆጣጠር ምን ያህል ጥረት እንዳደረጉ ያሳያል፡፡

አሁን ላይ ኢትዮጵያዊያን ሙስሊምና ክርስቲያኖች በተደጋጋሚ በተጎነጎነባቸው የተንኮል እና የክፋት መንገዶቻቸው ፈተና እንዲገጥማቸው ለማድረግ አልፎ አልፎ ብቅ ጥልቅ የሚሉ ሴራዎች ቢኖሩም ለዘመናት ተሰናስሎ የዘለቀው አብሮነት ግን በቀላሉ የሚታጠፍ አልሆነም፡፡

ሁዳ ቲቪን፣ ኢትዮ ኢስላሚክን እና የኢትዮጵያ ጥንታዊ ታሪክ ማጣቀሻን በመረጃ ምንጭነት ተጠቅመናል፡፡ ኢድ ሙባረክ!

በታዘብ አራጋው

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡

Source link

Related posts

ጁንታው በዋሻ ውስጥ ሆኖ የትግራይን ህዝብ ለማደናገር የሚያደርገው ጥረት አይሳካም- መከላከያ ሰራዊት

admin

ቦርዱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የስርዓተ-ፆታ አካታችነት ሀገራዊ ጥናት ላይ ከሲቪል ማህበራት ጋር እየተወያየ ነው

admin

ለኢንዱስትሪ ሽግግር ዩኒቨርሲቲዎች የንድፈ ሃሳብ ትምህርትን ከተግባር ጋር በማዋህድ መስጠት እንዳለባቸው የኢትዮጵያ ቴክስታይል እና ፋሽን ቴክኖሎጅ ኢንስቲትዩት ገለጸ፡፡

admin