55.89 F
Washington DC
April 13, 2021
Satenaw Ethiopian News/Breaking News
Amharic News

ቃና ዘገሊላ | የአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት

ባሕር ዳር፡ ጥር 12/2013 ዓ.ም (አብመድ) ቃና ዘገሊላ ኢየሱስ ክርስቶስ የመጀመሪያውን ታምሩን የገለጸበት ቦታ ነው፡፡ ቃና ዘገሊላ ሁለት ትርጉም አለው፡፡ አንደኛው በገሊላ አውራጃ የምትገኝ ቃና የተባለች መንደር ስትሆን ሁለተኛው ኢየሱስ ክርስቶስ የገለጸው የመጀመሪያ ተዓምር ስያሜ ነው፡፡ ቃና ዘገሊላ ኢየሱስ ክርስቶስ በዶኪማስ ቤት ተገኝቶ ውኃውን ወደ ወይን የቀየረበትና ጋብቻን የባረከበት ዕለት ነው፡፡ ቃና ዘገሊላ በዕለቱ የተደረገውን ተዓምር ይዞ የበዓል ስያሜ ሆኖ መሰጠቱን በምዕራብ ጎጃም ሀገረ ስብከት የጉባኤ ቤት መምህር ገብረመድህን እንየው ነግረውናል፡፡

ኢየሱስ ክርስቶስ በዮርዳኖስ ወንዝ በደቀ መዝሙሩ በዮሐንስ እጅ ተጠመቀ፡፡ ሳይውል ሳያድር በገዳመ ቆሮንጦስ ገብቶ 40 ቀንና 40 ሌሊት ፀለየ፡፡ ከገዳመ ቆሮንቶስ ሲወርድ የካቲት 23 ቀን በዶኪማስ ቤት ተገኝቶ ውኃውን ወደ ወይን የቀየረበት የመጀመሪያው ተዓምር ነው ብለዋል መምህር ገብረመድህን፡፡

እንደ መምህር ገብረመድህን ገለጻ በዶኪማስ ቤት ድንግል ማርያም፣ ልጇ ኢየሱስ ክርስቶስና ደቀ መዛሙርቱ ተገኝተው ነበር፡፡ ይህ ተዓምር የካቲት 23 ቀን ይፈጸም እንጅ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በዓሉን ጥር 12 ቀን ከጥምቀት በዓል ጋር አስተሳስራ በደመቀ ሁኔታ ታከብራለች፡፡ የቃና ዘገሊላ በዓልም የውኃ በዓል ስለሆነ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንም ከጥምቀት በዓል ጋር አስተሳስራ የምታከብርበት ምክንያቱ ይህ መሆኑን መምህሩ ነግረውናል፡፡

መምህር ገብረመድህን እንዳሉት ምዕመኑ ከቃና ዘገሊላ ትምህረት መውሰድ ይገባዋል፡፡ የመጀመሪያው ምሳሌነቱ ካለማወቅ ወደ ማወቅ መምጣትን ነው፤ ጋኖቹ ባዶ ነበሩ በወይን ተሞልተዋል፡፡ እኛም የሰው ልጆች በጥበብ ልንሞላ ይገባል፡፡ ሌላው አክብሮትንና አንድነትን እንማርበታለን፤ ዶኪማስ ድንግል ማርያምን በሰርጉ እንድትታደም ሲጠራት ብቻዋን አልነበረም፤ ከልጇ ጋር እንጅ፤ ልጇን ጠርቶ ዝም አላለም ደቀ መዛሙርቱን ጨምሮ ጠርቷል፡፡ እናም ይህን በዓል ስናከብር አንዳችን ለአንዳችን ያለንን ክብር ልናሳይበት ይገባል ብለዋል፡፡

መምህር ገብረመድህን ከቃና ዘገሊላ ልንማር ይገባል ያሉት ሌላው ጉዳይ አንዳንችን የአንዳችንን ጭንቀት መገንዘብ፣ መረዳት፣ ተረድተን ዝም ማለት ሳይሆን መፍትሄ ማፈላለግና ማገዝ እንደሚጠበቅብን ነው፡፡ ምክንያቱም ድንግል ማርያም ሰርጉን ሲያስተናግዱ የነበሩ ሰዎች ሲጨነቁ አይታ ለልጇ “ወይኑ አልቆባቸዋል” አለችው፤ እርሱም መፍትሔ ሆናቸው፡፡

ምዕመኑ በዓሉን ለማክበር ሲወጣ በልማድ ሳይሆን አስተምህሮውን በማወቅ፣ ያወቅነውን ሳንበርዝ በመቀበል፣ የተቀበልነውን ለሌሎች በማስተላለፍ፣ ማስተላለፍ ብቻ ሳይሆን በመጠበቅም መሆን እንዳለበት መምህሩ አስረድተዋል፡፡

መምህር ገብረመድህን ቃና ዘገሊላን ስናከብር የጋብቻን ክቡርነት መረዳት ይገባልም ብለዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ

ፎቶ፡- ከድረ ገጽ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡

Source link

Related posts

የንግዱ ማህበረሰብ ህግን አክብሮ በተረጋጋ ሁኔታ እንዲንቀሳቀስ የከተማ አስተዳደሩ በልዩ ትኩረት እንደሚሰራ ተገለፀ

admin

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሕጋዊ ሰውነት እንዲኖረው ምክክር እየተደረገ ነው

admin

ጥቃቱ ቆሞ ሰላም እንዲፈጠር የጸጥታ አስከባሪ አካላት ኀላፊነታቸውን እንዲወጡ በአጣዬ ከተማ ከጥፋቱ የተረፉ ተጎጂዎች ጠየቁ፡፡

admin