40.51 F
Washington DC
April 17, 2021
Satenaw Ethiopian News/Breaking News
Amharic News

“ቀጣዩን ሀገራዊ ምርጫ ከማድረግ የተሻለ አማራጭ ባለመኖሩ ለስኬታማነቱ መሥራት ይገባል” የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳደር የሕግ ጉዳዮች አማካሪ

“ቀጣዩን ሀገራዊ ምርጫ ከማድረግ የተሻለ አማራጭ ባለመኖሩ ለስኬታማነቱ መሥራት ይገባል” የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳደር የሕግ ጉዳዮች አማካሪ

ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 01/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳደር የሕግ ጉዳዮች አማካሪ መርሐፅድቅ መኮንን ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ስኬታማ ሆኖ እንዲጠናቀቅ በሀገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች የሚስተዋሉ ማንነትን መሰረት ያደረጉ ሰብዓዊ ጥቃቶችን ማስቆም እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡ የሕግ ጉዳዮች አማካሪው ዘር ተኮር ጥቃቶችን በማስቆምም የሕዝብን የጋራ እና የግል ደኅንነት ማረጋገጥ እንደሚገባ ገለጸዋል፡፡ ምርጫው በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት በሀገሪቱ ለሚፈጠረው ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ጉዳዮች ጠቀሜታው የጎላ በመሆኑ በመራጩ ሕዝብ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም ጠቅሰዋል፡፡

አቶ ኤፍሬም ማዴቦ “ኢትዮጵያና ሕገ መንግሥታዊ ምርጫዎቿ” በሚለው መጽሐፋቸው እንደገለጹት በኢትዮጵያ ታሪክ ሕዝብ ለመጀመሪያ ጊዜ የፓርላማ ተወካዮቹን የመረጠው በ1949 ዓ.ም ነበር፡፡ ምክር ቤቱ የላይኛው እና የታችኛው በመባል በሁለት የተከፈለ እንደነበርም ታሪክ ያወሳል፡፡ በደርግ ዘመን የነበረው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ደግሞ “ብሔራዊ ሸንጎ” ተብሎ 835 መቀመጫዎች ነበሩት፡፡ አንድ ወጥ ምክር ቤትም እንደነበር አቶ ኤፍሬም ማዴቦ ከትበዋል፡፡ በዘመነ ኢሕአዴግ ደግም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀጥተኛ ምርጫ በየአምስት ዓመቱ በሕዝብ የሚመረጥ ሲሆን 547 መቀመጫዎች አሉት፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፌዴራል መንግሥት ሕግ አውጭ እና ከፍተኛው የመንግሥት ስልጣን አካል ከመሆኑም በላይ የሀገሪቱን የመከላከያ እና ደኅንነት ተቋሞች ያደራጃል፡፡ ጦርነትና አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የማወጅ፣ አዲስ ግብር የመጫን፣ የፌዴራል ፍርድ ቤት ዳኞችን እና የሚኒስትሮች ምክር ቤት አባላትን ሹመት የማጽደቅ እንዲሁም የፌዴራል በጀትን እና ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን የማፅደቅ ስልጣንና ኀላፊነት አለበት፡፡

የፌዴሬሽን ምክር ቤት ከየብሔረሰቡ የተውጣጡ 112 አባላት እንዳሉት የርእሰ መሥተዳድሩ የሕግ ጉዳዮች አማካሪ አቶ መርሐፅድቅ መኮንን ገልጸው አባላቱ የሚመረጡት በክልል ምክር ቤቶች ነው ብለዋል፡፡ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሕገ መንግሥት መተርጎም፣ በክልሎች መካከል የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን መርምሮ መፍትሔ መፈለግ፣ ገቢ ማከፋፈል፣ የድጎማ ቀመር ማዘጋጀት እና በየትኛውም ክልል ሕገ መንግሥቱን የሚፃረር ተግባር ሲፈፀም የፌዴራሉ መንግሥት ጣልቃ እንዲገባ የመጠየቅ ስልጣን እንዳለውም አማካሪው ይገልፃሉ፡፡

በመሆኑም በሕዝብ ቀጥተኛ ተሳትፎ የሚከናወነው ምርጫ የሀገሪቱን መፃዒ እጣ ፋንታ እንደሚወስን የገለጹት አቶ መርሐፅድቅ ሀገራዊ ፋይዳውን የሚመጥን ቅድመ ዝግጅትም ያስፈልገዋል ባይ ናቸው፡፡

በሀገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች የሚታየው የሠላም እጦት የምርጫውን ሂደት እንዳያውክ ስጋት አለ፡፡ ነገር ግን ምርጫውን ከማድረግ የተሻለ አማራጭ ስለማይኖር መንግሥት፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎች እና መራጩ ሕዝብ ሂደቱን ከተፅዕኖ ነፃ ለማድረግ መሥራት ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት አማካሪው፡፡

አቶ መርሐፅድቅ ከሀገራዊው የሠላም እጦት መካከል አንዱ እና ዋናው በኦሮሚያ እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች የሚስተዋለው አማራ በመሆናቸው ብቻ በዜጎች ላይ የሚፈፀመው ጥቃት እየተደጋገመ መምጣቱ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ቀጣዩ ሀገራዊ ምርጫ ስኬታማ ሆኖ እንዲጠናቀቅም የሕዝብን የጋራ እና የግል ደኅንነት ማስጠበቅ አስፈላጊ ነው ይላሉ፡፡መንግሥት የዜጎቹን ደኅንነት ማስጠበቅ ዝቅተኛ ግዴታው ቢሆንም በምርጫ ወቅት ግን የዜጎች ደኅንነት ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ መሆን አለበት ነው ያሉት፡፡

መራጩ ሕዝብም አሁን የሚስተዋሉትን ሀገራዊ ፈተናዎች ለመሻገር ምርጫ ሁነኛ የዲሞክራሲያዊ መንግሥት መገለጫ መሆኑን በማመን በቅድመ ምርጫ፣ በምርጫ እና በድኅረ ምርጫ ወቅት ተባባሪ መሆን አለበት ነው ያሉት፡፡

አቶ መርሐፅድቅ ምርጫው በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት በሀገሪቱ ለሚፈጠረው ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ጉዳዮች ፋይዳው የጎላ በመሆኑ በመራጩ ሕዝብ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችም በአማራጭ የፖሊሲ ሐሳብ፣ በጋራ ትብብር እና በሀገራዊ መግባባት ላይ የተመሰረተ የውድድር አውድ መፍጠር እንዳለባቸው መክረዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡

Source link

Related posts

በስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ዜጎች በዕውቀት ላይ ተመስርተው እንዲመርጡ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ ተገለጸ።

admin

በድሬዳዋ ከተማ በከተማ ልማታዊ ሴፍትኔት ፕሮጀክት ታቅፈው የነበሩ አባወራዎች ተመረቁ

admin

1 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር በመዝረፍ ወንጀል የፈጸሙ ተከሳሾች በ16 ዓመት ፅኑ እስራት ተቀጡ

admin