56.68 F
Washington DC
April 21, 2021
Satenaw Ethiopian News/Breaking News
Amharic News

“ሱዳን በጉልበት የያዘችውን ቦታ ለቅቃ እንድትወጣ የኢትዮጵያ መንግሥት የጊዜ ገደብ ሊኖረው ይገባል” የታሪክ ምሁር

“ሱዳን በጉልበት የያዘችውን ቦታ ለቅቃ እንድትወጣ የኢትዮጵያ መንግሥት የጊዜ ገደብ ሊኖረው ይገባል” የታሪክ ምሁር

ባሕር ዳር፡ የካቲት 18/2013 ዓ.ም (አብመድ) የሱዳን ወታደራዊ ክንፍ በጉልበት የተቆጣጠረውን የኢትዮጵያ ግዛት ለቅቆ እንዲወጣ የፖለቲካ ፓርቲዎችና መላው ኢትዮጵያውያን በጋራ መሥራት እንዳለባቸው ከአብመድ ጋር በስልክ ቆይታ ያደረጉ በወሎ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ምሁር ዶክተር ዓለማየሁ እርቅይሁን መክረዋል፡፡

የኢትዮ-ሱዳን ድንበር አከላለል ሀሳብ የተጠነሰሰው በድኅረ ዓድዋ ጦርነት (1898 ዓ.ም) ነው፡፡ ከአምስት ዓመታት በኋላ (በ1902 ዓ.ም) የሁለቱን ሀገራት ድንበር ማካለል የሚያስችል ባለ አምስት አንቀጽ ስምምነት በእግሊዝ መንግሥት ተወካይ ኮሎኔል ሀሪንግተን እና በአጤ ምኒልክ አማካኝነት ተደርጓል፡፡ ከስምምነቱ መካከል የመጀመሪያዎቹ ሁለት አንቀጾች ችግር እንዳለባቸው ዶክተር ዓለማየሁ ተናግረዋል፡፡

እንደ ዶክተር ዓለማየሁ ማብራሪያ የመጀመሪያው አንቀጽ ይዘት ወሰኑ የሚያርፍበትን ካርታ የሚያመላክት ነው፤ ሁለተኛው አንቀጽ ደግሞ የሁለቱ ሀገራት ተወካዮች የወሰን ማካለል ሥራውን ካከናወኑ በኋላ እንደሚጸና ይገልጻል፡፡ በተለይ ሁለተኛው አንቀጽ ሁለቱም ሀገራት እንዲወከሉ እድል ቢሰጥም እንግሊዞች በ1903 እ.አ.አ ሻለቃ ግዊን በሚባል ተወካያቸው አማካኝነት በፍላጎታቸው ላይ የተመሠረተ የድንበር ማካለል ሥራ ሠርተዋል፡፡ በዚህም በመተማ እና ቋራ አካባቢዎች ከ30 እስከ 40 ኪሎ ሜትር ድረስ ወደ ኢትዮጵያ ገብተው ከልለዋል፡፡ ከጓንግ ወንዝ በስተምሥራቅ ያሉ በርካታ አካባቢዎችም ወደ ሱዳን እንዲካለሉ ተደርጓል፡፡ ይህ የማካለል ሥራ በ1902 እ.አ.አ የተደረገውን ስምምነት የጣሰ እና የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የነካ በመሆኑ በኢትዮጵያ መንግሥት እና ሕዝብ ተቀባይነት እንዳላገኘ ዶክተር ዓለማየሁ ተናግረዋል፡፡

በዚያ መልኩ ቆይቶ እ.አ.አ በ1972 የኢትዮጵያና የሱዳን የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሮች ችግሩን ለመፍታት የሚያስችል የደብዳቤ ልውውጥ እንዳደረጉም አንስተዋል፡፡ የደብዳቤ ልውውጡ ሀገራቱ ችግሩን ለይተው መፍትሔ ለማስቀመጥ በግዊን መስመር ላይ በመርህ ደረጃ የተግባቡበት መሆኑን አንስተዋል፡፡ ይህ ማለት ግን ግዊን ያዘጋጀውን መስመር ኢትዮጵያ ለመቀበል ተስማምታለች ማለት እንዳልሆነ በአጽንዖት ተናግረዋል፡፡ ስምምነት እስከሚፈጠር ድረስም የሁለቱም ሀገራት አርሶ አደሮች ሳይፈናቀሉ ባሉበት ጸንተው እንዲቆዩ ተወስኖ ነበር፡፡

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ መፍትሔ ለመፈለግ ጥረት ሲደረግ ቆይቷል፡፡ ይሁን እንጂ የሱዳን አካሄድ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የሚነካ በመሆኑ ስምምነት ላይ መድረስ አልተቻለም፡፡ በአካባቢው ያሉ አርሶ አደሮችም ባሉበት ጸንተው ቆይተዋል፡፡

ሆኖም የኢትዮጵያ መንግሥት በሀገር ውስጥ ሕግ የማስከበር ዘመቻ በተሰማራበት ወቅት የሱዳን ወታደራዊ ክንፍ ስምምነቱን በመጣስ የኢትዮጵያን መሬት በኀይል ተቆጣጥሯል፡፡ ዶክተር ዓለማየሁ ድርጊቱ እ.አ.አ በ1902 እና በ1972 የተደረጉ ስምምነቶችን በመጣስ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የተዳፈረ መሆኑ በግልጽ መታወቅ አለበት ብለዋል፡፡

ታሪክ እንደሚያስረዳው ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር የምታደርገው ግንኙነት በሁኔታዎች የሚለዋወጥ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ጠንካራ ሀገር ስትሆን ሱዳን ወዳጅ መስላ ትቀርባለች፤ ችግር በሚገጥማት ጊዜ ደግሞ እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ብሔራዊ ጥቅሟን ትነካለች፤ ሉዓላዊነቷንም ትዳፈራለች፡፡

ዶክተር ዓለማየሁ እንዳብራሩት በደርግ ዘመነ መንግሥት የዚያድ ባሬ መንግሥት ኢትዮጵያን በወረረ ጊዜ የኢትዮጵያ ሠራዊት ትኩረት ወደ ምሥራቅ ኢትዮጵያ ነበር፡፡ በዚያን ጊዜ ሱዳን ጥቃት ፈጽማ ለረዥም ዓመታት በኢትዮጵያ አርሶ አደሮች እጅ የነበረ የእርሻ መሬትን ተቆጣጥራ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ጦርነቱን አሸንፎ የዚያድ ባሬን ወረራ ከቀለበሰ በኋላ ግን በኀይል የተቆጣጠረችውን መሬት ለቅቃ እንድትወጣ ተደርጋለች፡፡

በተመሳሳይ እ.አ.አ በ1980ዎቹ መጨረሻ ገደማ የውስጥ ችግርን ጠብቃ ሠራዊቱ ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ ሲንቀሳቀስ ወረራ መፈጸሟንም አስታውሰዋል፡፡ በቅርቡ የፈጸመችው ተግባርም ካለፉት ታሪኮቿ ጋር ተመሳሳይ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡ ሱዳን የኢትዮጵያን ግዛት በኀይል የተቆጣጠረችውም ከስምምነቶቹ አፈንግጣ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም ሱዳን ወደነበረችበት እንድትመለስ የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት በትኩረት መሥራት እንደሚገባቸው መክረዋል፡፡ “ሱዳን በጉልበት የያዘችውን ቦታ ለቅቃ እንድትወጣ የኢትዮጵያ መንግሥት የጊዜ ገደብ ሊኖረው ይገባል” በማለትም ተናግረዋል፡፡

የታሪክ ምሁሩ የሱዳን ወታደራዊ ክንፍ ሦስተኛ ወገን ለማስገባትም ጥረት እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ይህ ደግሞ ሁለቱም ሀገራት ነገሮችን መቆጣጠር ወደማይችሉበት ደረጃ ሊያደርሳቸው እንደሚችል አመላክተዋል፡፡

ሱዳን በኢትዮጵያ ላይ የሉዓላዊነት ጥሰት ፈጽማለች፡፡ አካባቢው ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ መሠረት ከመሆኑም ባሻገር ለሀገሪቱ ሕዝቦች የሕልውና ጉዳይ ነው፡፡ በመሆኑም መላው ኢትዮጵያዊያን እና የፖለቲካ ፓርቲዎች ከምን ጊዜውም በላይ በአንድነት በመቆም ችግሩን መቀልበስ እንደሚጠበቅባቸው መክረዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡

Source link

Related posts

በይርጋለም የተቀናጀ የግብርና ምርቶች ማቀነባበርያ ኢንዱስሪ ፓርክ የተሰማሩ ባለሀብቶች ከማህበራት ጋር ትስስር መፍጠራቸው ተገለፀ

admin

ጠቅላዩ “የኦሮሞን ጥያቄ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ እየሰራን ነው” ሲሉ እኛ የሚገባን….?!? (ተፈራ ወንድማገኝ)

admin

የጆ ባይደን አስተዳደር በህዳሴ  ግድብ ላይ ጣልቃ እንደማይገባ ተስፋ አደርጋለሁ- አምባሳደር አለማየሁ

admin