45.84 F
Washington DC
May 8, 2021
Satenaw Ethiopian News/Breaking News
Amharic News

“…ሰብዓዊ እርዳታ እየቀረበ አይደለም የሚሉ አካላት የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ነው” – ዶ/ር ሙሉ ነጋ

ጁንታው ትግራይን ለ፴ ዓመታት ያስተዳደረው በሴፍቲ ኔት ነው

በትግራይ ክልል የሰብዓዊ እርዳታ እየቀረበ እንዳልሆነ ተደርጎ የሚናፈሰው ወሬም ከእውነት የራቀ ነው አሉ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶ/ር ሙሉ ነጋ።

የፌዴራል መንግሥት በክልሉ የተጠናከረ ሰብአዊ ድጋፍ እያደረገ ነው ሲሉ ተናግረዋል። “ድጋፉ እየቀረበ አይደለም” በሚል ሃሰተኛ መረጃ የሚያናፍሱ አካላት የፖለቲካ ትርፍ በመፈለግ የሚፈጽሙት ድርጊት ነው ሲሉም ገልፀዋል።

በክልሉ የመብራት፣ የውሃ እና የባንክ አገልግሎቶች በበርካታ አካባቢዎች መጀመራቸውን አንስተው፤ አገልግሎት ባልተጀመረባቸው አንዳንድ አካባቢዎች ደመወዝ ላልተከፈላቸው የመንግስት ሰራተኞች እንዲከፈላቸው እየተሰራ ነው ብለዋል።

ሥራ አስፈጻሚው ዶክተር ሙሉ ነጋ በተለይ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ የትግራይ ሕዝብ ካለበት የባሰ ሰብዓዊ ችግር ውስጥ እንዳይገባ የፌደራል መንግሥቱ በከፍተኛ ትኩረትና ቁርጠኝነት አጋርነቱን እያሳየ መሆኑን የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ሥራ አስፈጻሚ ገለጹ። እስከ አሁን ባለው ሁኔታ 2 ነጥብ 5 ሚሊየን የሚደርስ ሕዝብ እርዳታ እንደሚፈልግ መገመቱን ጠቁመዋል።

ጁንታው በስልጣን ላይ በነበረባቸው ወቅቶች በክልሉ ቁጥራቸው ከፍ ያለ የህብረተሰብ ክፍሎች በሴፍቲኔት እየታገዙ ይኖሩ ነበር። አሁን ደግም በሕግ ማስከበር ዘመቻው ምክንያት ከቀያቸው የተፈናቀሉ ዜጎች ተጨማሪ ድጋፍ ፈላጊ መሆናቸውን አመልክተዋል።

የኤሌክትሪክ፤ የቴሌኮምና ባንክ አገልግሎቶች ተቋርጦ በመቆየቱ ምክንያት ከዚህ ቀደም ድጋፍ የማይፈልጉ ሁሉ አሁን ድጋፍ ፈላጊ ሆነዋል፤ የፌደራል መንግሥቱ ይህንን ሁኔታ ከግምት በማስገባት ህብረተሰቡ የተባባሰ ችግር ውስጥ እንዳይገባ በከፍተኛ ቁርጠኝነት እየሰራና እያገዘ መሆኑን አስታውቀዋል።

እንደ ዶክተር ሙሉ ገለጻ ከዚህ ቀደም በክልሉ የነበረው የኢኮኖሚ እድገት ጥሩ ቢሆን ኖሮ ለጥቂት ጊዜያት እንኳን ይህንን ችግር ማለፍ ይቻል ነበር፤ ሆኖም ክልሉ ቀድሞም የተጎዳ ስለነበር እንደዚህ ዓይነት ችግር ሲጨመርበት ከፍተኛ የሰብዓዊ ድጋፍ ፍላጎት ተከስቷል ብለዋል።

ጁንታው ቡድን ጦርነት የለኮሰበት ወቅት አርሶ አደሩ የዘራውን ምርት በሚሰበስብበት ጊዜ መሆኑ ችግሩን በከፍተኛ ሁኔታ እንዳባባሰው የተናገሩት ዶክተር ሙሉ፣ በዚህም በክልሉ የተሰበሰበ ምርት የለም፤ የእርዳታና የድጋፍ ፍላጎቱም ይህንን ሁሉ ከግምት ያስገባ ስለመሆኑም ጠቁመዋል።

“አሁን እንደ መጀመሪያ ገንዘብ ያለውም ሰው እርዳታ ማግኘት ይፈልጋል፤ ሆኖም ባንኮች ወደ ስራ እየገቡ በመሆኑ ህብረተሰቡ ገንዘብ ማውጣት ከጀመረ የተረጂው ቁጥር ይቀንሳል። እስከ አሁን ባለው ሁኔታ ግን 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን የሚደርስ ሕዝብ እርዳታ እንደሚፈልግ ይገመታል፤ እዚህ ላይ ግን ቁጥሩ ከዚህም ሊጨምር ይችላል” ብለዋል።

በሌላ በኩል በትግራይ ክልል የተካሄደውን የህግ ማስከበር ዘመቻ ተከትሎ በመቀሌ ከተማ ድገፍ ለሚሹ ወገኖች ድጋፍ የአስቸኳይ ጊዜ የምግብ ርዳታ እየተደረገ መሆኑ ተገለጸ።

በትግራይ ክልል ጊዚያዊ አስተዳደር የመቀሌ ከተማ ከንቲባ አቶ አታኽልቲ ሃይለስላሴ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በከተማዋ ለሚኖሩና ከተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው ለመጡ 379 ሺህ አቅመ ደካሞችና አረጋዊያን ድጋፍ ለማድረግ የሚያስችል  ዝግጅት ተጠናቆ ርዳታ እየቀረበ ይገኛል።

እንደ አቶ አታኽልቲ ገለጻ፤ እስካሁን ለ180ሺ ዜጎች ስንዴ እና ዱቄት እንዲሁም ለህጻናት ደግሞ አልሚ ምግቦች ተሰጥቷል።

የተቀሩት ድጋፍ የሚሹ ወገኖች ደግሞ በቀጣይቀናት ውስጥ እርዳታው እንደሚሰጣቸው  ከንቲባው ገልፀዋል።

የትግራይ ክልልን መልሶ በመገንባት ሂደት ሁሉም ኢትዮጵያዊያን የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ አመራሮቹ ጥሪ ማቅረባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ

Print Friendly, PDF & EmailSource link

Related posts

ግብጽና ሱዳን በዓባይ ተፋሰስ በሚከናወኑ የተፈጥሮ ሀብት ሥራዎች ሊሳተፉ እንደሚገባ ባለሙያዎች ገለጹ፡፡

admin

የጥፋት ሀይሎችን ህግ ፊት ለማቅረብ መንግስት እየሰራ ይገኛል- የሰላም ሚኒስቴር

admin

አፍሪካ እና ሩሲያ ባህላዊ ትስስራቸውን መልሰው በመገንባት ወዳጅነታቸውን ማጠናከር ይገባቸዋል – ጠ/ሚ ዐቢይ

admin