48.78 F
Washington DC
April 13, 2021
Satenaw Ethiopian News/Breaking News
Amharic News

ሰላም ለአገራችን፣ምህረት ለሕዝባችን – ጆቢር ሔይኢ ከሁስታን ቴክሳስ | Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider

የኢትዮጵያ ሕዝቦች የዘላለም ጥያቄ፣”ሕዝባዊ መንግሥት” የሚል ነበር።ራሱ በመረጠው  መንግሥት ለመተዳደር።ነገር ግን የኢትዮጵያ ሕዝብ የራሱ የሆነ መንግሥት ኖሮት አያውቅም። ቀድሞ ነገሥታት ዘር በመቁጠር፣በባርነትና በገባርነት ይገዙት ነበር። ወታደራዊ ደርግም፣ለአስራ ሰባት አመት የገዛን፣ በጠብ መንጃ አፈሙዝ በማስገደድ ነበር።ኢሕአዴግ ለሃያ ሰባት አመት የገዛንም፣  የብሔር ብሔረሰቦችን ጥያቄ በከፊል በመመለሱና የኤርትራንም  ሕዝብ የነጻነት ውሳኔ በማክበሩ ነበር።

ይህ ግን የሁሉም አቋዋም አይደለም፣ ከብልጽግና ፓርቲ አባላትና ደጋፊዎች መካከልም እንኳ፣  መሣፍንታዊውን አገዛዝ የሚያወድሱ፣ ሕገ መንግሥቱንና የፌድራል ግንኙነትን የሚያወግዙ አሉ።ስለዚህም የዘውድ አገዛዝ ናፋቂ፣ የልሙጥ ባንዲራ አምላኪዎች ናቸው ወደ ቀደመው የጭቆና ሥርዓት ሊመልሱን፣ በግልጽን በስውር ተደራጅተው፣  እርስ በርስ የሚያፋጁን ።ይህ ደግሞ  ማንንም ከየትም አያደርስም፣ ማንም በማንም ሀብት፣ ንብረትና መብት ላይ አዛዥ ሊሆን አይችልም።

ሕገ መንግሥቱ ለብሔር ብሔረሰብ የሠጠውን መብት በመቃወም፣ ነዋሪውን ሕዝብ በመናቅ፣ እየገደሉና እያዋረዱ፣በፌስ ቡክ ጫጫታ፣በከንቱ ራስን ማጋነን ፋዬዳም ዬለውም።እንደ እውነቱ ከሆነ ይህ ነው  የመደብ ቅራኔን በማቻቻል፣ ሕዝቦችን በብሔራቸው ጎራ የሚያሰልፈው። ስለሆነም በሕዝቦች መካከል ያለው  ቅራኔ ሳይፈቱ፣ ችግሩን ሰውሮ፣ ብሔር ብሔረሰቦችን እንደ መንጋ አፍኖ፣ መንጋጋት የትም አያደርስም ውጤቱ ዞሮ፣ ዞሮ፣ በዜሮ ማብዛት ይሆናል።

የብሔር ጥያቄን በሚመለከት መሪዎቻችን  እንደሚያስቡት የብሔር ጥያቄ፣ የቋንቋ ጥያቄ ብቻ አይደለም። እንግሊዝና አሜሪካ አንድ ቋንቋ ይናገራሉ፣ ነገር ግን የአንድ ብሔር አባል  አይደሉም። ኦሮሞዎች በኬኒያና በኢትዮጵያ ይኖራሉ፣ በመካከላቸው የአገር ወሰን ስለ አለ፣ የአንድ ብሔር አባል አይደሉም።ስለሆነም ብሔር በጂኦግራፊ ተለይቶ የታወቀ የራሱ የሆነ የመኖሪያ አካባቢ ያለው ነው።ይህ ብቻ አይደለም ብሔር ባህል፣ታሪክና የሥነ ሊቡና ዘይቤ ያዳበረና የጸና ማኅበረሰብ ነው።

ከእነዚህ ባሕርያቱ መካከል አንዱን  ሲጎዱበት ነው፣ ብሔሩ ተቆጥቶ ከሌላው ብሔር ጋር የሚጋጨው።ለዚህም ነበር ኦሮሞዎች ከሱማሌ በተፈናቀሉ ጊዜ፣ የኦሮሚያ ምክር ቤት ተፈናቃዮቹን በፍጥነት ተቀብሎ፣ በክልሉ በማስፈር ቅራኔውን ያረገበው።ሌሎች ግን ይህን ብሔራዊ ግዴታቸውን መወጣት ተስኖአቸው ነው፣ በሌሎች ላይ የሚደነፉት።

ኢሕአዴግም እኮ ይህንኑ የብሔሮች ጥቅም ባለማከበሩ ነበር ከብሔር ብሔረሰቦች ጋር እሳትና ጭድ ሁኖ፣ በአገአዚ ጦር እየገደለና እያሠረ ይገዛ የነበረው።የብልፅግና ፓርቲም ያንኑ የኢሕአዴግን ተግባር በመድገም ላይ ይገኛል፣ስለሆነም ነው የኦሮሞ አባቶች “ላም እሳት ወለደች፣ እንዳትልስ እሳት ሆነባት፣ እንዳትተው ልጅ” በማለት በጸጸት አንገታቸውን ለመድፋት የተገደዱት።

ሀቁ ይህ ከሆነ  የታሰባው ምርጫ ምን ይፈይዳል?እንዴትስ ሰላምን ሊያሰፍን ይችላል? ምርጫው የብሔር ጩቆናን የሚያባብስ፣ ሕዝቡን  ለኮሮና በሽታ የሚያጋልጥ ከሆነ፣ ጥቅሙ ምንድን ነው?

እንደሚታወቀው በአገራችን የፓርላሜንተሪያዊ ቅርጸ መንግሥት፣ ከገዥው ፓርቲ ቁጥጥር ውጭ ሊሆን የሚችል አንድም  የመንግሥት አካል የለም።መከላከያው፣የሕዝብ ተወካዮችም ሆኑ፣ የፌድሬሽን ምክር ቤት፣ የፍትሕ አካላትም ሆኑ፣ ምርጫ ቦርድ፣ ሁሉም የገዥው ፓርቲ  የኢኮኖሚና የፖለቲካ ጥገኞች ናቸው። ታዲያ ገለልተኛ ዳኛና ምርጫ አስፈጻሚ ከየት ሊመጣ ነው? ምርጫ በዚህ ሁኔታን  ጊዜ የሚካሄደው።

ለማስታወስም ያህል የኢሕአዴግም ሆነ የብልጽግና ፓርቲ መዋቅር፣ በመንግሥት ተቋም ውስጥ፣ ከላይ እስከታች የተዘረጋ ነው። ገዥው ፓርቲ በዚህ መዋቅሩ በመጠቀም የፈቀደውን ማስመረጥ ይችላል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚሰየመው ደግሞ ራሱ ባስመረጣቸው የሕዝብ ተወካዮች ነው።በዚህ ላይ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥልጣን፣ የአገሪቱና የፓርቲውም መሪ፣የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ፣በሁሉም ላይ አድራጊና ፈጣሪ ናቸው።ታዲያ ይህ ከፈላጭ ቆራጭ  የንጉሥ አገዛዝ በምን ይለያል?

ሕዝባችን እስከ አሁን አሮጌውን የዘውድ አገዛዝ፣ ከትከሻው አሽቀንጥሮ ጥሎታልና ከእንግዲህ ለማንም አያጎበድድም። ወታደራዊ አገዛዝም አይመጥነንም።ለብሔር ጭቆናም ዕድል ፈንታ አንሰጥም። በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥትም ቢሆን፣ የብሔር ጥያቄን ዴሞክራሲያዊ በሆነ መልኩ ካልፈታ በስተቀር፣ በጠብ መንጃ አፈሙዝ አስገድዶ ማንንም ሊገዛ አይችልም። ቅራኔን በማፈን፣ዘላቂ ሰላምንም ሆነ ብልጽግናን ማምጣት አይቻልም።ዛሬ ቢታፈን ነገ መፈንዳቱ አይቀርምና!

የመንግሥት ሥልጣንንም በሚመለከት፣ የኢትዮጵያ አቢዮታዊ ዴሞክራሲ ቅርጸ መንግሥት፣ለነፃ የገቢያ ኢኮኖም አይማጥንም። ወጭና ጠላትን ማብዛት፣ ሕዝቡን ግራ ለማጋባት ካልሆነ በስተቀር።ስለዚህም ጎራ መለየት የግድ ነውና፣ሕገ መንግሥቱንና ቅርጸ መንግሥቱን ልንገነባው ከምንፈልገው ማኅበራዊና የኢኮኖሚ ሥርዓት ጋር ማጣጣም ይገባናል።

ስለሆነም ለአገራችን ሰላምና ለሕዝባችን ብልፅግና ቅድመ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ስለሚገባ፣ የምርጫ ቅስቀሳን በመግታት፣

ሀ/ ለፖለቲካ እስረኞችና ለተቃዋሚዎች ሁሉ  ምሕረት ማድረግ፣

ለ/  በአፍሪካ ኅብረትና በሃይማኖት አባቶች አደራዳሪነት፣ መንግሥትንና የሕወሐትን አመራር በማግባባት፣ሰላምን በማስፈን፣ ሁሉንም ወደነበረበት ቦታ በመመለስ፣ አገርን ከጥፋት ሕዝብን ከእልቂት መታደግ፣

ሐ/ ከየዞኑ አንዳንድ የሕገ መንግሥት ጉዳይ የኮሚሽን አባላትን ማስመረጥ፣

መ/ የሕዝብ ቆጠራን በማካሄድ በነዋሪው ሕዝብ ፈቃድ የወሰን ጥያቄን መፍታት፣

ሠ/ የተቀርጸውን ሕገ መንግሥት፣ በሕዝበ ውሳኔ ማጸደቅ፣

ረ/ በተሻሻለው ሕገ መንግሥት መሠረት መርጫ በማካሔድ  አገርን ከጥፋት ሕዝብን ከልቂት መታደግ ይገባል።

ይህ ከሆነ ሕዝባችን ተረጋግቶ፣ ወደ ልቡናው ስለሚመለስ፣ የክረረው ቅራኔ ረግቦ፣  አንዱ የሌላውን የልብ ትርታ በማድመጥ፣ አንተ ትብስ አንቺ ትብሽ በማለት ተከባብሮ በሠለም አብሮ ይኖራል።

ለዚህም  ቸሩ ፈጣሪ አምላካችን፣ ከምህረቱ ብዛት ራርቶልን፣ አገራችንን ከክፋት ኃይላት ይታደግ ዘንድ፣አዘውትረን በፊቱ በመውደቅ እንማጸነዋለን! በቅዱስ ልጁም ስም እንለምነዋለን! እርሱም ቸርና ርሁሩህ አምላክ ነውና እጁን ዘርግቶ ከጠላቶቻችን ሁሉ ይጋርደናል! ይታደገናል! አሜን!

ጆቢር ሔይኢ ከሁስታን ቴክሳስ፣

Source link

Related posts

የተፈራው አልቀረም ሙሉ ነጋ(ዶ/ር)  ዳግማዊ ስብሃት ነጋን ሆነው መጥተዋል!?! (ታምሩ ገዳ)

admin

ኢትዮጵያ እና ጂቡቲ በቴሌኮሙዩኒኬሽን ዘርፍ ያላቸውን አጋርነት ለማጠናከር ተስማሙ

admin

“ዘመቻው ቢያልቅም ዘመቻው የፈጠራቸው ዕድሎችም፤ ዘመቻው ያስከተላቸው ጫናዎችም አላለቁም” ሙአዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት

admin