76.68 F
Washington DC
June 17, 2021
Satenaw Ethiopian News/Breaking News
Amharic News

ምክር ቤቱ 26 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት አጸደቀ፡፡
ምክር ቤቱ 26 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት አጸደቀ፡፡
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 03/ 2013 ዓ.ም (አሚኮ) የኢፌዴሪ 5ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 6ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 14ኛ መደበኛ
ስብሰባው 5 ጉዳዮችን አጀንዳ አድርጎ ተወያይቷል፡፡ ምክር ቤቱ ለፌዴራል መንግሥት የ2013 በጀት ዓመት ተጨማሪ በጀትና
የወጪ አሸፋፈን ማስተካከያን በቀጥታ ወደ ቋሚ ኮሚቴው ሳይመራ ዝርዝር ውይይት ተደርጎበት ውሳኔ እንዲሰጠው ማድረግ
ቀዳሚ አጀንዳው አድርጓል፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ2013 በጀት ዓመት ሥራ ላይ እንዲውል ጠቅላላ ብር 476 ቢሊዮን ብር በጀት ማጽደቁ
ይታወሳል። በወቅቱ የነበረው የበጀቱ ዝግጅት የማክሮ ኢኮኖሚ ሁኔታዎችን ተለዋዋጭነት ታሳቢ ያደረገ እንደነበር ያወሱት
የመንግሥት ተጠሪ ረዳት ሚኒስትር ጫኔ ሽመካ አሁን እንደ ሀገር ለገጠሙ የኢኮኖሚ ተግዳሮቶች መፍትሔ ለመስጠት በ2013
በጀት ላይ ለውጦችን ማድረግ የሚያስገድድ ሆኖ ተገኝቷል ብለዋል፡፡
የቀረበው የተጨማሪ በጀት ጥያቄና የወጪ አሸፋፈን ማስተካከያ ተግባራዊ እንዲሆን ሲሉ በቀጥታ ጉዳዩ ለቋሚ ኮሚቴው
ሳይመራ ለሕዝብ እንደራሴዎቹ ዝርዝር የውሳኔ ሀሳብ አቅርበዋል፡፡ ተጨማሪ በጀት አስፈላጊነትን በተመለከተ ማብራሪያ የሰጡት
የመንግስት ተጠሪ ረዳት ሚኒስትሩ ከውጭ የሚገኘው የቀጥታ ድጋፍ በመቀነስ ምክንያት በሀገር ውስጥ ቀጥታ ብድር መሸፈን
በማስፈለጉ፤ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ሕግን ለማስከበር ከተወሰደው እርምጃ ጋር ተያይዞ የተከሰቱ ወጪዎች፣ በድርቅ ለተጎዱ፤
ለተፈናቀሉ እና ለተመላሾች ለዕለት ዕርዳታ፣ ኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መከላከል፣ ለማዳበሪያ ድጎማ፣ ለጎርፍ መከላከል፣ ለማዕድንና
ነዳጅ ሚኒስቴር ለአቅም ግንባታ ፕሮጀክት እና የመጠባበቂያ በጀት በመጠናቀቁ በቀጣይ ወራቶች ለሚያስፈልጉ የተለያዩ
ወጪዎች ለመጠባበቂያ በጀት መመደብ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል ብለዋል፡፡
የተለያዩ ወጪዎችን ቀጥታ የበጀት ድጋፍ ለማድረግ እና በተገቢው መልኩ ለመሸፈን እንዲቻል በሚል ከመንግሥት ጎን ለመሆን
ፈቃደኛ ከሆኑ የልማት አጋሮች ጋር የገንዘብ ድጋፍ ስምምነቶች መደረጋቸው ተነስቷል፡፡ ከደቡብ ኮሪያ መንግሥት የቀጥታ ድጋፍ
በብድር የተገኘ የ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር፤ የኮሮናቫይረስ ቀውስ አስቸኳይ ምላሽ የበጀት ድጋፍ፣ ከአፍሪካ ልማት ባንክ 5 ነጥብ 3
ቢሊዮን ብር ለኢትዮጵያ የኮሮናቫይረስ መከላከል ምላሽ በጀት የድጋፍ ፕሮገራም እና ከጀርመን ተራድኦ በዕርዳታ 4 ነጥብ 7
ቢሊዮን ብር እንዲሁም ከአውሮፓ ሕብረት በዕርዳታ የብር 230 ሚሊዮን በድምሩ የብር 11 ነጥብ 8 ቢሊዮን የተጨማሪ የበጀት
ድጋፍ ስምምነቶች መደረጋቸውን ተጠሪ ሚኒስትሩ ለሕዝብ እንደራሴዎቹ አብራርተዋል፡፡
የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ሊያስከትል የሚችለውን የኢኮኖሚ ጫና ለመቀነስ እንዲያስችል የኮሮናቫይረስ ትረስት ፈንድ እና ከሀገር
ውስጥ ለጋሽ ግለሰቦችና ከዚህ ቀደም ከተሰበሰበው ሌሎች ልዩ ልዩ ገቢዎች 7 መቶ ሚሊዮን ብር ገቢ እንደሚገኝ ታሳቢ ተደርጎ
ከሀገር ውስጥ ታክስ ካልሆኑ ገቢዎች ተጨማሪ በጀት ቀርቧል፡፡
በአጠቃላይ ከቀጥታ ድጋፍ እና ከሀገር ውስጥ ታክስ ካልሆኑ ገቢዎች 125 ቢሊዮን ብር እንደሚገኝ ታሳቢ ተደርጎ በጀቱ ነው
የቀረበው፡፡
የወጪ ታሳቢዎች ደግሞ በቅርቡ በሀገሪቱ የሰሜኑ ክፍል በተደረገው ሕግ የማስከበር ሥራ ለመከላከያ ሠራዊት ለተለያዩ
የሎጂስቲክ ማሟያ ወጪዎች፤ ለሠራዊቱ የግዳጅ ቀለብና እንዲሁም ከዚሁ ጋር ተያያዥ ለሆኑ ጉዳዮች፣ ለተፈናቀሉ፣ በተፈጥሮ
አደጋ ምክንያት ዕርዳታ ለሚፈልጉ፣ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ለመከላከል ተጨማሪ በጀቱ ተግባር ላይ ይውላል ተብሏል፡፡
ለ2013 በጀት ዓመት ለመጠባበቂያ የጸደቀው 13 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ጥቅም ላይ በመዋሉ እና ለዩኒቨርሲቲዎች እና ለሌሎች
ባለበጀት መስሪያቤቶች ደመወዝ፣ አበል እና ጡረታ እንዲሁም ከውጭ ምንዛሪ ለውጥ ምክንያት የምንዛሪ ማካካሻና አስፈላጊ
ለሆኑ ሥራ ማስኬጃ ወጪዎች የቀረበውን የተጨማሪ በጀት ጥያቄ ለማስተናገድ እንዲቻል ለመጠባበቂያ በጀት የሚያስፈልግ 6
ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር፣ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት በመንግሥት የሚደረገውን እንቅስቃሴ ለማገዝ ከአውሮፓ ሕብረት ጋር
በተደረገው ስምምነት ለከተማ ምግብ ዋስትና የሴፍቲኔት ፕሮግራም ጊዜያዊ ተጠቃሚዎች ድጋፍ በተጨማሪ 2 መቶ 30
ሚሊዮን በመጠባበቂያ በጀት መልክ እንዲያዝ ቀርቧል፡፡
ምክር ቤቱ በሀገር ውስጥ ባንክ ብደር የሚሸፈን 26 ቢሊዮን ብር የፌዴራል መንግሥት ተጨማሪ በጀት እና የወጪ አሸፋፈን ረቂቅ
አዋጅን አጽድቋል፡፡
የካቲታል ገበያ ረቂቅ አዋጅ፤ የፌዴራል ጥብቅና አገልግሎት ፈቃድ አሰጣጥ እና አስተዳደር፤ የፌዴራል የድጎማ በጀትና የጋራ
ገቢዎች ክፍፍል ሥርዓትና ተቋማዊ አደረጃጀት ረቂቅ አዋጆች ላይ የቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ ምርምሮ ምክር ቤቱ አጽድቋል፡፡
ምክር ቤቱም ረቂቅ አዋጁን አዋጅ ቁጥር 1247/2013 አድርጎ በሙሉ ድምጽ አጽድቆታል፡፡
ዘጋቢ፡- ጋሻው ፋንታሁን
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m


Previous articleየአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ በቅርቡ ተግባራዊ የሚኾን አዲስ የሥርዓተ ትምህርት ይፋ አድርጓል፡፡


Source link

Related posts

በትግራይ ክልል ለተፈጠረው ሰብዓዊ ቀውስ ተጠያቂው ህወሃት ነው ሲል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም ሰነድ አረጋገጠ፡፡

admin

የጃዋር ቅዠትና የበቀለ የተላላኪነት ፖለቲካ – የለማ ሃዲድ መሳት

admin

ሰራተኞች እያሳዩት ያለው መዘናጋት የኮቪድ 19 ወረርሽኝ እንዲስፋፋ እያደረገ ነው-የኢትዮጵያ ሰራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን

admin