79.57 F
Washington DC
June 13, 2021
Satenaw Ethiopian News/Breaking News
Amharic News

“ምርጫው የተሳካ እንዲሆን ሁሉም የድርሻውን መወጣት አለበት” ርእሰ መሥተዳድር አገኘሁ ተሻገር

“ምርጫው የተሳካ እንዲሆን ሁሉም የድርሻውን መወጣት አለበት” ርእሰ መሥተዳድር አገኘሁ ተሻገር

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 02 /2013 ዓ.ም (አሚኮ) የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን (ኢጋድ) የግጭት ቅድመ ማስጠንቀቂያና ምላሽ ቡድን በባሕር ዳር ውይይት እያካሄደ ነው፡፡ ኢጋድ በኢትዮጵያ የግጭት ቅድመ ማስጠንቀቂያና ምላሽ ዘዴ እንደገና ማቋቋሚያ አውደ ጥናት ዛሬ በባሕር ዳር መካሄድ ጀምሯል፡፡

የግጭት ቅድመ ማስጠንቀቂያና ምላሽ ዘዴ በኢጋድ አባል ሀገራት የተመሰረተው በ2002 ነው። ዘዴውም በምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት የግጭት መነሻዎችን ቀድሞ በመተንበይ ጥንቃቄና ምላሽ መስጠት የሚያስችል ነው።

በምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት የግጭት ቅድመ ማስጠንቀቂያና ምላሽ ዘዴ የግጭት ተንታኙ ዶክተር ሰንዳይ አንጎማ ኦኮሎ እንዳሉት ምሥረታው ውጤታማ የግጭት መከላከል፣ መቆጣጠርና አፈታት ዘዴን ተቋማዊ በሆነ መልኩ በጋራ ለመከላከል መሠረት የተጣለበት ነው። ይሕም ግጭቶችን ቀድሞ ለማስቀረት በመረጃ ላይ የተመሰረተ ትንታኔ በመሥጠት ለሁሉም የአፍሪካ ሀገራት ምሳሌ የሚያደርግ ነው፡፡

የኢጋድ የግጭት ቅድመ ማስጠንቀቂያና ምላሽ ዘዴ ከተመሠረተ ጀምሮ በድንበር ተሻጋሪ ግጭቶች ላይ ብቻ ትኩረቱን አድርጎ ሲሠራ ነበር፡፡ ከቅርብ ጊዜያት ጀምሮ ግን አድማሱን አስፍቶ በመሥራት ላይ ይገኛል፤ በማኅበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊ፣ በአስተዳደራዊ፣ በጸጥታና አካባቢያዊ ጉዳዮች ላይ እንደሚሠራም ዶክተር ሰንዳይ ተናግረዋል፡፡

ዛሬ መካሄድ የጀመረው አውደ ጥናት በኢትዮጵያ ያለውን የግጭት ቅድመ ማስጠንቀቂያና ምላሽ ቡድን እንደገና ለማጠናከርና የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶችን ተሳትፎ ለማረጋገጥ ያለመ ነው፡፡

የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አገኘሁ ተሻገር ሀገራዊ ለውጡ ብዙ እድሎችን ቢያስገኝም ለውጡ እንዳይሳካ በሚፈልጉ ኀይሎች ሴራ በርካታ ችግሮች ማጋጠማቸውን አንስተዋል፡፡ በየአካባቢው የሚታዩ ግጭቶችን አስቀድሞ በትንበያ መፈታት እንደነበረባቸው አንስተዋል፤ ዛሬ የተጀመረው ውይይት በኢትዮጵያ ለሚያጋጥሙ ችግሮች ቀድሞ ጥሩ ምላሽ ለመስጠት እንደሚያስችልም ተናግረዋል፡፡

ስድስተኛው ሀገራዊና ክልላዊ ምርጫ ዴሞክራሲያዊ፣ አሳታፊ እና ለሀገሪቱ የዴሞክራሲ መዳበር መሠረት እንደሚሆን አስታውቀዋል፡፡ ርእሰ መሥተዳድሩ አገኘሁ እንዳሉት ምርጫው የተሳካ እንዲሆን ሁሉም የድርሻውን መወጣት አለበት፤ ኢጋድም ምርጫው ሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የሚጠበቅበትን ሚናውን እንዲወጣ ጠይቀዋል፡፡

ኢትዮጵያ የታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር ሙሌት ለማከናወን የምታደርገው ጥረት እንዳይሳካ ግብጽና ሱዳን አቅደው እየሠሩ መሆኑን አንስተዋል፤ አንዱ የግጭት ምንጭም ሊሆን ስለሚችል ኢጋድ የኢትዮጵያን ፍላጎት በሚገባ ተረድቶ ሀቁን ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የማስረዳት ኀላፊነት እንዳለበት ጠቅሰዋል፡፡

በሰላም ሚኒስቴር የሕግ ማስከበር ዘርፍ ሚኒስቴር ዲኤታ ፍሬዓለም ሽባባው በምሥራቅ አፍሪካ ሀገራም በግጭት ቅድመ ማስጠንቀቂያና ምላሽ በኩል አስፈላጊው መረጃ ደርሶ ችግሮችን መቀነስ የሚያስችሉ በርካታ ኹነቶች እንዳሉ አንስተዋል፡፡

ዓለም አቀፉን የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ጨምሮ በኢትዮጵያ የተከሰተው የጎርፍ አደጋ፣ የበርሃ አንበጣ መንጋና መሰል ችግሮች በትብብር የሚመከቱ ናቸው ብለዋል ወይዘሮ ፍሬዓለም፤ ሽብርተኝነትን ጨምሮ ዓለም አቀፍ ቀውሶች በርካታ በመሆናቸው ሰው ሠራሽ ግጭቶችን በጋራ በመመከት ሕብረተሰቡን ከአደጋ ተጋላጭነት ለመከላከል በቀጣናው ቅድመ ማስጠንቀቂያ አስፈላጊ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ ለዚህም አጎራባች ሀገራት በጋራ ማቀድ፣ በጀት መመደብ እና አብረው መምራት ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት፡፡

የቀጣናውን ሰላም ለመጠበቅ በፈጣን የመረጃ ልውውጥ አብሮ መሥራት ወሳኝ መኾኑን አንስተዋል፤ ይሕም በተለይ በኢትዮጵያ የሚፈጠሩ ችግሮችን ለማስቀረት ይረዳል ብለዋል፡፡

በምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ባለስልጣን የግጭት ቅድመ ማስጠንቀቂያና ምላሽ ዘዴ በኢትዮጵያ የተጀመረው ውይይት በቀጣይ ሦስት ቀናት የሚቀጥል ይሆናል፡፡ በውይይቱ የኢጋድ ተወካዮች፣ የፌዴራልና የአማራ ክልል ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እየተሳተፉ ነው፡፡

ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡

Source link

Related posts

በደገሀቡር እና በጅግጅጋ ሪፈራል ዩኒቨርስቲ ሆስፒታል ያገባኛል ኢኒሼቲቭ ተጀመረ

admin

ደረቅ ቆሻሻን መልሶ በመጠቀም ከ432 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ ተገኘ

admin

ካናዳ 132 ነጥብ 9 ሚሊዮን ዶላር ለአየር ንብረት ለውጥ ፈንድ ልታበረክት ነው፡፡

admin