46.09 F
Washington DC
February 25, 2021
Satenaw Ethiopian News/Breaking News
Amharic News

ማኅበረሰቡ ሕጻናትን በአግባቡ የማስከተብ ልምድ ሊያዳብር እንደሚገባ የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ገለፀ፡፡

ማኅበረሰቡ ሕጻናትን በአግባቡ የማስከተብ ልምድ ሊያዳብር እንደሚገባ የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ገለፀ፡፡

ባሕር ዳር፡ ጥር 19/2013 ዓ.ም (አብመድ) በሀገር አቀፍ ደረጃ አስራ ሁለት አይነት በሽታ መከላከያ ክትባት በጤና ተቋማት ለህጻናት እየተሰጠ ነው፡፡ በባሕርዳር ከተማ አስተዳደር አባይ ጤና ጣቢያ ልጇን ለማስከተብ የተገኙት ወይዘሮ ጥሩጌጥ ወንድዬ ልጃቸውን ወቅቱን ጠብቀው እንደሚያስከትቡ ገልፀዋል፡፡ “ልጄን የማስከትበው ጤነኛ እንድትሆንና በእኔም ሆነ በህጻኗ ህይወት ላይ እንቅፋት እንዳይፈጠር በማሰብ ነው” ብለዋል፡፡ ወላጆች ልጆቻቸውን በክትባት ወቅቱን ሳያቆራርጡ ማስከተብ እንዳለባቸውም ተናግረዋል፡፡

ሌላዋ በጤና ተቋሙ ያገኘነናቸው ወይዘሮ ደጅይጥኑ በበኩላቸው በጤና ተቋሙ የክትባት አገልግሎት አሰጣጡ መልካም ነው ብለዋል፡፡ የመኖሪያ አካባቢያቸውን ቢቀይሩም በልጃቸው የክትባት ክትትል ላይ የገጠማቸው ችግር አለመኖሩን ነግረውናል፡፡ ልጆቻቸው ጤነኛ እንዲሆኑ የጤና ባለሙያዎችን ምክር ተግባራዊ እንደሚያርጉም ገልፀዋል፡፡

ሌሎች እናቶችም ልጆቻቸውን በአግባቡ በማስከተብ ከተላላፊ እና ተላላፊ ካልሆኑ በሽታዎች ሊከላከሉ ይገባል ነው ያሉት፡፡

በባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ጤና መምሪያ የአባይ ጤና ጣቢያ የክትባት ክፍል አስተባባሪ አቶ ሙሐመድ ተፈራ በጤና ጣቢያው ከጠይማ ቀበሌ በተጨማሪ ከዘንዘልማና ከወረብ ቀበሌ የሚመጡ እናቶች ይስተናገዳሉ ብለዋል፡፡

የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ጤና መምሪያ ከመድኃኒት አቅርቦት ኤጀንሲው ጋር በመተባበር መድኃኒት በወቅቱ ስለሚያደርሰን ክትባቱ ያለምንም መቆራረጥ እንደሚሰጥ ተናግረዋል፡፡

በጤና ጣቢያው 10 ያህል ክትባቶች ይሰጣሉ፤ ዘወትር ሰኞ እና ሐሙስ የሳንባ ነቀርሳ፣ የኩፍኝና የልጅነት ልምሻ በሽታ መከላከያ ክትባት ይሰጣል፤ ቀሪዎቹ ማክሰኞ፣ረቡዕና አርብ እንደሚሰጡ ነግረውናል፡፡ ከአዲስ ዓለም ሆስፒታል ጋርም በትብብር እንደሚሰሩ አስተባባሪው አብራርተዋል፡፡

በአማራ ክልል ጤና ጥበቃ ቢሮ የክትባት ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ ወርቅነህ ማሞ ክትባት በሀገርም ሆነ በክልል ደረጃ መስጠት ከተጀመረ ከ 40 ዓመት በላይ አስቆጥሯል ብለዋል፡፡

ክትባት በሀገር ደረጃ ሲጀመር ስድስት ያህል ተላላፊ በሽታዎችን ለመከላከል ቢጀመርም በአሁኑ ሰዓት የማህጸን በር ካንሰርን ጨምሮ 12 ያህል በሽታዎችን የሚከላከሉ ክትባቶች በሁሉም የጤና ተቋማትና በክትባት መስጫ ጣቢያዎች እየተሰጠ ነው ብለዋል፡፡

ሁሉም ክትባቶች አስከ አምስት ዓመት ድረስ ላሉ ሁሉም ሕጻናት ይሰጣል፤ የማህጸን በር ካንሰር ክትባት ደግሞ ከዘጠኝ ዓመት ጀምሮ ላሉ ልጃገረዶች ይሰጣል ብለዋል፡፡

መድኃኒቱን በአግባቡ ለማሰራጨት የመድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ በየወሩ ለወረዳዎች እንዲያደርስ ውል ወስዷል፤ ከወረዳ በታች ደግሞ ጤና ጥበቃ ጽሕፈት ቤት ተደራሽ ያደርጋል ብለዋል አቶ ወርቅነህ፡፡ ሀገር አቀፍ ችግር ካላጋጠመ በስተቀር እስካሁን የመድኃኒት እጥረት ገጥሞን አያውቅም ብለዋል፡፡

የማኅበረሰቡ የግንዛቤ ማነስ፣ ትኩረት አለመስጠት እንዲሁም የቦታ ርቀት መኖር በክትባት አሰጣጡ ላይ የሚያግጥሙ ችግሮች መሆናቸውን አንስተዋል፡፡ ህጻናትን በአግባቡ የማስከተብ ልምድ ማኅበረሰቡ ሊያዳብር ይገባልም ብለዋል፡፡

ክትባት ያልጀመሩና ጀምረው ያቋረጡ ህጻናትን የክትባት ተጠቃሚ ለማድረግም የአሠራር ስርዓት መዘርጋቱን ነግረውናል፡፡

ለህጻናት የሚሰተው ክትባት ከ12 ዓይነት በሽታ መከላከል ስለሚችል ወላጆች በአግባቡ ልጆቻቸውን ማስከተብ ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት፡፡

ከጥር 17 እስከ ጥር 22/2013 ዓ.ም ድረስ በሁሉም የጤና ተቋማትና በትምህርት ቤቶች ሁለተኛው ዙር የማህጸን በር ካንሰር መከላከያ ክትባት እድሜያቸው ከ14 ዓመት በላይ ላሉ ሴቶች እየተሰጠ እንደሚገኝ ከቢሮው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡

Source link

Related posts

የደቡብ ክልል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በሀዲያ ዞን ሻሾጎ ወረዳ ያልተጠናቀቁ ፕሮጀክቶችን ጎብኝተዋል

admin

የዜጎች ሞት፣ መፈናቀልና ንብረት መውደም ስለሚቆምበት ሁኔታ እና ተጎጂዎች በዘላቂነት እንዲቋቋሙ ለማድረግ የሚሰራ ቡድን እንዲቋቋም ውሳኔ ተላለፈ

admin

‹‹ እነሆ ወደ ዮርዳኖስ ወረደ የእዳ ደብዳቤውም ተቀደደ››

admin