76.62 F
Washington DC
June 15, 2021
Satenaw Ethiopian News/Breaking News
Amharic News

“መከራውን ያልተካፈሉ ግን ትንሣኤውን አያዩም፡፡” ሊቀ መዘምራን ጌታቸው

“መከራውን ያልተካፈሉ ግን ትንሣኤውን አያዩም፡፡” ሊቀ መዘምራን ጌታቸው

ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 20/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ከዕለተ ሆሣዕና እስከ ትንሣኤው ሌሊት ያሉትን ቀናት ያመላክታል – ሰሞነ ሕማማት፡፡ ሰሞነ ሕማማት ክርስቲያኖች የክርስቶስን ውለታ እያሰቡ እጅግ የሚያዝኑበት፣ የሚያለቅሱበት፣ የሚሰግዱበት፣ ፈጣሪያቸውን የሚማጸኑበት እና ጧት ማታ ደጅ የሚጠኑበት በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ የሚገኝ ሳምንት ነው፡፡

በዚህ ሳምንት ክርስቲያኖች ከመራብ እስከ መጠማት፣ ከመውጣት እስከ መውረድ፣ ከመስገድ እስከ መፀለይ፣ ከመፆም እስከ ትህትና ያሉትን በጎ ክርስቲያናዊ ተግባራት በመፈፀም የኢየሱስ ክርስቶስን መከራ እና ስቃይ በማሰብ ያሳልፋሉ፡፡ በሰሞነ ሕማማት ክርስቶስ ኢየሱስ ስለሰው ልጅ ሃጢያት ሲል በፈቃዱ ያሳለፋቸውን መከራ፣ ሕማማት፣ ድካሙን እና እንግልቱን የሚያስታውሱ ከኢሳይያስ እስከ ኤርምያስ፤ ከመዝሙረ ዳዊት እስከ ግብረ ሕማማት ቅዱሳት መጻሕፍት በየሰዓቱ በቤተ ክርስቲያናት ይነበባሉ፡፡

ሰሞነ ሕማማት ለክርስቲያኖች ከሞት ወደ ሕይወት የተሸጋገሩበት እና ከጨለማ ወደ ብርሃን የተጓዙበት የመሸጋገሪያ ወቅት ምሳሌ ተደርጎም ይወሰዳል፡፡ በዚህ ሳምንት ታላላቅ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ከደቀ መዝሙራቸው ኢየሱስ ክርስቶስ የወረሱትን ትህትና እያወሱ ዝቅ ብለው የታናናሾቻቸውን እና ጓደኞቻቸውን እግር ያጥባሉ፡፡

ከስግደት፣ ከመጽሐፍት ንባብ እና ጥሞና በተረፋቸው ጊዜም እንደ ትንሳዔው ባይደምቅ እንኳን ስለመበደላቸው ንስሃ እየገቡ በገናን ይደረድራሉ፡፡

በባሕር ዳር ከተማ የቅዱስ ያሬድ መንፈሳዊ በገና ማሰልጠኛ ተቋም መስራች እና መምህር ሊቀ መዘምራን ጌታቸው ብርሃኑ ጋር ቆይታ አድርገናል፡፡ ሰሞነ ሕማማት የፅሞና እና የአርምሞ ሳምንት ናት ብለዋል ሊቀ መዘምራን ጌታቸው፡፡

በዚህ ሳምንት ክርስቲያኖች የሚያደርጉትን ሃይማኖታዊ ተጋድሎ ሲያመሰጥሩም “መከራውን ያልተካፈሉ ግን ትንሣኤውን አያዩም” ይላሉ፡፡ በሰሞነ ሕማማት በተለይም ሁለት ቀናት የተለየ ስያሜ እና ግብር እንዳላቸው ሊቀ መዘምራን ጌታቸው አስረድተዋል፡፡ እነርሱም ፀሎተ ሐሙስ እና ቅዳሜ ስዑር ይባላሉ፡፡

“ፀሎተ ሐሙስ” ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ዕለት ፍፁም ሰው ፍፁም አምላክ መሆኑን የገለጠበት ነው፡፡ ለአርአያነትም ጸሐፍት ፈሪሳውያን የአይሁድ ካህናት መጥተው እስኪይዙት ድረስ ሲፀልይ በማደሩ ምክንያት “ፀሎተ ሐሙስ” ትባላለች ነው ያሉት፡፡

ከዓመት አንድ ቀን ብቻ የምትፆመው ቅዳሜ ደግሞ “ቅዳሜ ስዑር” ይሏታል፡፡ “ቅዳሜ ስዑር” የመባሏን ምክንያት ሊቀ መዘምራን ጌታቸው ሲናገሩም እናቱ ማርያም እና ወዳጆቹ ቅዱሳን ሐዋርያት ኢየሱስ ለአይሁድ ካህናት ተላልፎ ከተሰጠበት ዕለት አንስተው በብርሃነ ትንሣኤው እስኪገለጥ ድረስ ምንም አልቀመሱም ነበር ይላሉ፡፡

ዛሬም ክርስቲያኖች ሐዋሪያትን መስለው ጭንቃቸውን እያሰቡ የላመ እና የጣመ ሳይቀምሱ “ቅዳሜ ስዑርን” ያሳልፋሉ ብለዋል፡፡ ሊቀ መዘምራን ጌታቸው እንዳሉን በሰሞነ ሕማማት ክርስቲያኖች የደቀ መዝሙራቸውን የኢየሱስ ክርስቶስን 13ቱን ሕማማተ መስቀል እያስታወሱ “እንዲህ አንገላቱህ” እያሉም የንስሃ በገናን ይደረድራሉ፡፡

መዝሙረኛው ዳዊት በትንቢት መነፀሩ በገና እየደረደረ እንግልቱን፣ ግርፋቱን፣ ሞቱን፣ ስቅለቱን እና ልብሶቹን እኳን አይሁድ ፈሪሳዊያን እንዴት በእጣ እንደሚካፈሉት ይናገራል ብለዋል፡፡ ሊቀ መዘምራን የትንሣኤው ቀንን ጨምሮ በገና እንደሚዘወተር ገልጸው በሰሞነ ሕማማት ለንስሃ ዝማሬዎች በገና ይደረደራል ብለውናል፡፡

በሰሞነ ሕማማት ከስሜት እስከ አልባሳት፤ ከሰላምታ እስከ አንድምታ በአርምሞ የሚያሳልፉት ክርስቲያኖችም በገናን በንስሐ ቃኝተው እየደረደሩ ያሳልፋሉ፡፡ ከኦሪት ዘፍጥረት ጀምሮ በገና በእለተ ሰንበት ከተፈጠሩት ስምንት ፍጥረታት መካከል ሰባተኞቹ ፍጥረታት ከሆኑት መላዕክት ጋር እንደነበረ መጽሐፍ ቅዱስ ይነገረናል ብለዋል፡፡

ሊቀ መዘምራን ጌታቸው ይህንን ጥንታዊ የቤተ ክርስቲያን የምሥጋና መሳሪያ ጥንታዊነቱን ጠብቆ እንዲዘልቅ እና እንዳይዘነጋ ለማድረግ ጥረቶች እንዳሉም ነግረውናል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡

Source link

Related posts

ዓለምአቀፉ አሸባሪ ትክክለኛ ስሙን አገኘ

admin

በቻይና  በውድድር ወቅት  በተከሰተ ከባድ የአየር ሁኔታ የ21 ሯጮች ህይወት አለፈ

admin

በጄኔራል ብርሃኑ ጁላ የተመራ የመከላከያ ሚኒስቴር ከፍተኛ የልኡካን ቡድን በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ጉብኝት እያደረገ ይገኛል

admin