71.98 F
Washington DC
May 17, 2021
Satenaw Ethiopian News/Breaking News
Amharic News

መንግሥት ከስድስት ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር በመተባበር በትግራይ ክልል ለተፈናቃዮች እና ድጋፍ ለሚሹ ዜጎች የሚሰጠው ሁሉአቀፍ ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠሉ ተገለጸ፡፡

መንግሥት ከስድስት ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር በመተባበር በትግራይ ክልል ለተፈናቃዮች እና ድጋፍ ለሚሹ ዜጎች የሚሰጠው ሁሉአቀፍ ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠሉ ተገለጸ፡፡

ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 21/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ቻታም ሀውስ የተባለ በዩናይትድ ኪንግደም በዓለምአቀፍ የፖሊሲ ጥናትና ምርምር የሚሠራ ተቋም ከለንደን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጋር በመተባበር ባዘጋጀው የበይነ መረብ ውይይት ላይ የሰብዓዊ ድጋፍ ሰጪ ድርጅቶች ሥራ አስፈጻሚዎች፣ የሰብዓዊ መብት ዓለምአቀፍ ተቋማት፣ በዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት አፍሪካ ተኮር የልማት ድርጅት ኀላፊዎች ፣ ዓለምአቀፍ የመገናኛ ብዙኃን ፣ ዓለም አቀፍ የግጭትና ቀውስ ትንተና ባለሙያዎች እና አፍሪካ ላይ ትኩረት አድርገው የሚሠሩ ተቋማትን ጨምሮ ሌሎች ተሳታፊዎች ተገኝተዋል፡፡

በውይይቱ ላይ የብሔራዊ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ምትኩ ካሳ በሰጡት ማብራሪያ በትግራይ ክልል የሕግ ማስከበር እርምጃ መጠናቀቅን ተከትሎ በተደረገው የመጀመሪያ ዙር ለ 4 ነጥብ 5 ሚሊየን ዜጎች የምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ድጋፍ ተደርጓል፤ በሁለተኛው ዙር ለ 2 ነጥብ 7 ሚሊየን ዜጎች በተመሳሳይ ድጋፉ መቀጠሉን ገልጸዋል፡፡

ለሰብዓዊ ድጋፍ መንግሥት ከ 3 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ማውጣቱን ተናግረዋል፡፡ ከዚህ ድጋፍ ውስጥ 70 ከመቶው ከመንግሥት ፤ ቀሪው 30 በመቶው በዓለምአቀፍ ድርጅቶች የተሸፈነ ነው፡፡

በአሁኑ ወቅት በትግራይ ክልል ድጋፍ ከሚደረግላቸው 92 ወረዳዎች ውስጥ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች 86 ከመቶውን ወረዳዎች በራሳቸው እየተንቀሳቀሱ ሽፋን መስጠት መቀጠላቸውን አመላክተዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በመቀሌ ከተማ ማእከል በማቋቋም ማንኛውም እርዳታ በቅርበት ለወረዳዎች እንዲዳረስ እየተደረገ መሆኑን ያመለከቱት ኮሚሽነር ምትኩ በጤና ሚኒስቴር በእርዳታ የተሰጡ የህክምና መሳሪያዎች፣ መድኃኒቶች እና አምቡላንሶች ከክልሉ ጤና ቢሮ ጋር በመተባበር በየወረዳው የተንቀሳቀሽ ህክምና ማእከል አቋቁመው አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረጉ ነው ብለዋል፡፡

መንግሥትና ዓለም አቀፍ እርዳታ ሰጪ ድርጅቶች በገቡት የማስተባበርና የሰብዓዊ እርዳታን የማቅረብ ውል መሰረት ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጥ የሚገባቸው ከ 5 ዓመት በታች ለሆኑ ሕጻናት እና ለነፍሰ ጡር ሴቶች የሚደረገው የአልሚ ምግብ ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀርብ ለእርዳታ ሰጪዎች ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የትምህርት ሚኒሰቴር ለሕጻናት ከ 1 ሚሊዮን በላይ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ እና የኮሮናቫይረስ ንጽህና መጠበቂያዎችን ማቅረቡን ኮሚሽነሩ ገልጸዋል፡፡

ለአርሶ አደሮችም የሚያስፈልጉ መሰረታዊ የግብርና ግብዓቶች ለማቅረብ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የተፈናቀሉ ዜጎችንም ዓለም አቀፍ መርሑ በሚጠይቀው መሰረት መልሶ የማቋቋም ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡

በሕወሐት የወደሙ የኢኮኖሚና የማኅበራዊ መሰረተ ልማቶች ከዓለም ባንክ ፣ ከገንዘብ ሚኒሰቴር፣ ከሰላም ሚኒሰቴር ጋር በመተባበር ጥናት እየተደረገ መሆኑን አስረድተው ትግራይን መልሶ የመገንባት ሥራም እንደሚጀመር አመላክተዋል፡፡

ለሰብዓዊ እርዳታ የሚሆኑ አማራጮችን በሙሉ መንግሥት ክፍት አድርጎ ዓለም አቀፍ ተራድኦ ድርጅቶችንም እያስተናገደ እንደሚገኝ ያስረዱት ኮሚሽነር ምትኩ የመከላከያ ሰራዊትም የተሽከርካሪ እጀባ እና የጸጥታ ጥበቃ በማድረግ ለሰብአዊ ድጋፍ አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ተቀማጭነታቸው በኢትዮጵያ የሆኑት የተመድ ቋሚ ተጠሪና የሰብዓዊ ድጋፍ አስተባባሪ ካትሪን ቦሴ በበኩላቸው ያጋጠሙት ችግሮች ፈታኝ ቢሆኑም ከመንግሥት ጋር ተባብሮ በመሥራት ፈተናዎቹን ማለፍ እንደሚቻል አስረድተዋል፡፡

የድንበር የለሽ ሃኪሞች ዳይሬክተር ጀነራል ኦሊቨር በህን በበኩላቸው ችግሮች ቢኖሩም መንግሥት ለዓለም አቀፍ ተራድኦ ድርጅቶች ወደ ክልሉ በፈለጉት ጊዜ እንዲገቡ የፈቀደ መሆኑ ሊመሰገን እንደሚገባው ገልጸዋል፡፡ የእርዳታ አቅርቦቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የበኩላቸውን ጥሪ ማቅረባቸውን ከለንደን የኢትዮጵያ ኤምባሲ የተገኘ መረጃ ያመላክታል፡፡

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡

Source link

Related posts

ከ3 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር በላይ የሚገመቱ ለአርሶ አደሮች ያልተሰራጬ የእርሻ መሳሪያ ክምችት በኢንዱስትሪው ይገኛሉ-ቋሚ ኮሚቴው

admin

አቶ ደመቀ ሩስያ ለወሰደችው መርህን መሰረት ያደረገ አቋም ምስጋና አቀረቡ

admin

በሰሜን ሸዋ ዞን የተከሰተውን የጸጥታ ችግር ለመቆጣጠር በቅንጅት እየተሠራ መሆኑን የዞኑ ፖሊስ መምሪያ አስታወቀ፡፡

admin