

“መንግሥት በዜጎች ላይ የሚፈጸም ሽብርተኝነትን ለመከላከል ቁርጠኛ ከሆነ የተሰጠውን ሕገ መንግሥታዊ መብት በተግባር
ሊተረጉመው ይገባል” ደራሲ፣ ጠበቃና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች አለልኝ ምህረቱ
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 26/2013 ዓ.ም (አሚኮ) መጋቢት 21/2013 ዓ.ም በምዕራብ ወለጋ በባቦ ጋምቤል ወረዳ ከምሽቱ 3:00
ሰዓት ጀምሮ በዜጎች ላይ ማንነትን መሰረት ያደረገ የጭፍጨፋ ወንጀል መፈጸሙን የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄኔራል
አራርሳ መርዳሳ ለመገናኛ ብዙኀን በሰጡት መግለጫ ማሳወቃቸው ይታወሳል፡፡ ኮሚሽነሩ በኦነግ ሸኔ የተፈጸመው ጭፍጨፋ
ሽብር ነውም ብለውታል፡፡
በመተከል ዞን በቅርቡም ግድያ መፈጸሙ ይታወሳል።
የሰብዓዊ መብት ምሁራን እንደሚሉት ሽብርተኝነት ለፖለቲካ፣ ለሃይማኖት፣ለርዕዮተ ዓለም ወይም ለማህበራዊ ዓላማ ሲባል
የሚፈፀም የሕግ ጥሰት ወይም ያልተገባ ድርጊት ነው፡፡
አንድን የማኅበረሰብ ክፍል በሃይማኖቱ፣ በዘር፣ በፖለቲካ አመለካከቱ እና በመሳሰሉት በተቃራኒ ወገን የሚገኝ ቡድን ወይም
የመንግሥት አካል በማንኛውም ዘዴ ማስፈራራት፣ በነፃነት እንዳይኖር ማድረግ፣ የተደራጀ ጥቃት መፈፀም፣ ተጠቂው ዝም እንዲል
እና መብቱን እንዳይጠይቅ ማድረግ ሽብርተኝነት በሚል ዓለምአቀፍ ትርጉም ተሰጥቷቸዋል።
በኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት እየተፈጸመ ያለው ግድያ ከሽብርተኝነት ባህርያት የዓለምአቀፍ መርሆዎች አንጻር እንዴት ይመዘናል
ሲል አሚኮ የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ጉድለቶችና መንግሥታዊ አሸባሪነት በኢትዮጵያ ደራሲ፤ ጠበቃና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች
ለሆኑት አቶ አለልኝ ምህረቱ ጥያቄ አቅርቧል፡፡
በዓለምአቀፍ ሰብዓዊ መብት ሕግጋቶች መለኪያ መሠረት የሽብር ድርጊት በኢትዮጵያ እየተፈጸመ መሆኑን ማሳያዎችን በማንሳት
አቶ አለልኝ አብራርተዋል፡፡
የሕግ ምሁሩ በኢትዮጵያ “በሕግ ሽፋን በአንድ ማኀበረሰብ ላይ የመኖር መብትን ማሣጣት፣ በዜጎች ላይ ጥቃት ሲደረስ ጥቃት
አድራሹን መሸፈን እና በሕግ ተጠያቂ አለማድረግ፣ ለሚደረሰው ጥቃት ግድ አለመስጠት፣ የፍትሕ መብትን ማሣጣት፣ በሀሰት
ትርክት የሀሰት ማስረጃ በዜጎች ላይ የፍትሕ በደል ማድረስ እየታየ ነው” ብለዋል።
ከሰው ልጅ ተፈጥሮአዊ ባህሪ በወጣ እና ነውረኛ በሆነ መንገድ በዜጎች ላይ የሚፈጸመው ግድያ በዓይነቱ ዓለማቀፍ ሽብርተኝነት
ነው ያሉት የሕግና የሰብዓዊ መብት ምሁሩ አቶ አለልኝ የወንጀል አፈፃፀሙ የአንድን አካባቢ ሰዎች በዘር ለይቶ ማጥቃት፣ ዜጎችን
በአሰቃቂ አኳኋን የመግደልና የማፈናቀል ነውረኛ ተግባር እየተፈጸመ በመሆኑ ወንጀሉን ሽብር ያስብለዋል ብለዋል፡፡
የሽብርተኝነት ወንጀል በመንግሥት መዋቅር ውስጥና የመንግሥት ባለሥልጣን ባልሆኑ ፖለቲከኞች ሊፈፀም እንደሚችል ያወሱት
አቶ አለልኝ “መንግሥት በዜጎች ላይ የሚፈጸም ሽብርተኝነትን ለመከላከል ቁርጠኛ ከሆነ የተሰጠውን ሕገ መንግሥታዊ መብት
በተግባር ሊተረጉመው ይገባል” ብለዋል፡፡
ዘጋቢ:– ጋሻው ፈንታሁን–ከአዲስ አበባ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m