70.74 F
Washington DC
May 14, 2021
Satenaw Ethiopian News/Breaking News
Amharic News

መንግሥትና ተግባሩ (ግዴታው) – አገሬ አዲስ | Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider

መንግሥትና ተግባሩ (ግዴታው) - አገሬ አዲስ 1መጋቢት 24 ቀን 2013 ዓም(02-04-2021)

የመንግሥትን ምንነት፣ተግባርና ግዴታ ከማንሳት በፊት ሁሉንም በሥልጣን ላይ ተቀምጦ አገራዊ አስተዳደር የያዘውን አካል ወይም ስብስብ መንግሥት በሚል ስያሜ መጥራቱ ትክክል እንዳልሆነ ማስረዳቱ ተገቢ ነው።የቅኝ ገዥዎች ፣የፈላጭ ቆራጭ ነገሥታት ፣የወታደርና የጎሳ አምባገነን ስርዓቶች የዘረጉትን፣ በጉልበትና በሃይል አገርና ሕዝብን ካለፈቃዱና ካለምርጫው ቀጥቅጠው የሚይዙትን ጨካኞች መንግሥት ከሚለው ይልቅ አምባገነን ገዢዎች ብሎ መሰዬሙ ትክክል ነው ብዬ አምናለሁ።ገዢ በሚገዛው ላይ የባለቤትነት መብትና ስሜት ስለሚያድርበት እንዳሻው ያደርገዋል።ሕዝብም ሆነ አገር፣በስሩ ያለ ሁሉ የሚንቀሳቀሰው፣የመኖርና ያለመኖር መብቱ የሚወሰነው በገዢው ትዕዛዝ፣ፍላጎትና ፈቃድ ነው።ሁሉም ለገዥው የተፈጠረ አገልጋይና ንብረት ሆኖ ከመታዬት በቀር የተፈጥሮ እኩልነቱም ሆነ መብቱ አይታሰብም። ያ እስከሆነ ድረስ አገርና ሕዝብ ጥቂቶች የሚያዙበት፣እንደፈለጉ የሚያደርጉት የግል ወይም የቡድን ይዞታ ነው ማለት ነው።ስለሆነም መንግሥት የሚለው ስያሜና አጠራር ለዚህ አይነቱ ስርዓትና መሪዎች የሚመጥንና ተገቢ አይሆንም እላለሁ።
በትክክለኛው የመንግሥት ስያሜ፣ምንነትና ተግባር ስንገባ እንደሚከተለው እንረዳለን።
መንግሥት በሕዝብ ወይም በሕብረተሰቡ ፈቃድና ፍላጎት በመሪነት ቦታ የተሰዬሙ ሰዎች የሚመሰርቱት የአስተዳደርና የሥልጣን መዋቅር ነው።መንግሥት የአንድን አገርና ሕዝብ እጣ ፈንታ ለመወሰን፣ወደ ተሻለ የእድገት አቅጣጫ እንዲመራ ታምኖበት ስልጣን በሕዝቡ የተቸረው ወኪልና አገልጋይ ነው።አንድ መንግሥት ዘለዓለማዊ ሳይሆን እንደ ሕዝቡ ፍላጎት በጊዜ ገደብ የሚቀዬር ወይም ኮንትራቱ የሚራዘምለት ነው።በአገራዊ ሕገመንግሥት ስር የሚንቀሳቀስ፣ የሕዝቡን አደራ የጠበቀ፣ አርዓያና ምልክት የሚሆን፣በስነምግባር ታንጾ የሚያንጽ፣ የሃይማኖትና የጎሳ ምርጫና አድልኦ የሌለው፣ ሁሉንም በእኩል ዓይን የሚያይ ከሁሉም ለሁሉም በሁሉም የሆነ፣ዕራእይ አንግቦ የሚሠራ አካል ነው።ትክክለኛ መንግሥት ማለት የተሰጠውን አደራ ዘንግቶ ለራሱ መጠቀሚያ የማያደርግ፣ በሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል በሚል መንፈስ የማይመራ፣ አገርንም ሕዝብንም ለድህነትና ለቀውስ የማይዳርግ ፣ሥልጣኑ ላይ ሙጭጭ ብሎ ለመቆዬት ሕዝብን ከፋፍሎ የማያባላ፣ከውስጥና ከውጭ ሃይሎች ጋር የማያብርና ሴራ የማይጎነጉን ግለሰብ ወይም ቡድን ያሻውን የማያደርግበት ከፍተኛ የሥልጣን እርከን እንጂ የሽፍቶችና የሌቦች ዋሻ አይደለም።መንግሥት ሥራውን በግልጽ እቅዶ የሚተገብር እንጂ በህዝብ ጀርባ የሚሸርብ አድማ መቺ አይደለም።ብሔራዊ ካዝና የሚያዳብርና ጠባቂ እንጂ በማን አለብኝነት የአገር ሃብት የሚያባክን፣ካዝና ሰባሪና ዘራፊም አይደለም።
ዋናዋናዎቹ የመንግሥት ተግባራት
1 ብሔራዊ መከላከያ ማደራጀት፣2 የፍትሕ ተቋም መዘርጋት፣ 3 ለማህበረሰቡ የሚጠቅሙ ተቋማትን መገንባት
መንግሥት ለህብረተሰቡ ወይም ለሕዝቡ በግለሰብ ደረጃ ሊሟሉ የማይችሉትን ተግባራት ማለትም የደህንነት፣የመከላከያ፣የፖሊስ፣የእሳት አደጋ መቆጣጠሪያ፣ የመገናኛ፣የሕክምና፣የትምህርት፣የከባቢ ደህንነትን በአጠቃላይ ማህበራዊ አገልግሎትን ለማቅረብ ሃላፊነት የተሰጠው አካል ነው። የሕዝቡን የእለት ተእለት ሁኔታና ኑሮ እዬተከታተለ ፍላጎትን የሚያሟላ፣ለምቾቱና ለሰላማዊ ኑሮው የሚጨነቅና በተግባርም የሚያሳይ አገርና ሕዝብን ከውጭና ከውስጥ ጠላትና ከተፈጥሮ አደጋ የሚከላከል መከታና መድህን ነው።
በተጨማሪም ለዜጎቹም ሆነ ለመላው የሰው ልጅ በህይወት የመኖርን ሰብአዊ መብት ማክበርና ማስከበር አንዱ የሚጠበቅበትና የሚለካበት ተግባሩ ነው።ከዚያም በተረፈ ማንኛውም ዜጋ በሃገሩ በነጻ ተንቀሳቅሶ የመኖር፣ንብረት የማፍራትና የመያዝ ነጻነቱን ያስከብራል።ከውስጥና ከውጭ ጠላት መከላከል፣የኤኮኖሚ ስርዓትን በወጉ መምራት፣የተፈጥሮ ሃብቶችንና ገቢዎችን ለሁሉም በማዳረስ ሁሉንም ተጠቃሚ ማድረግ ይጠበቅበታል።ከዚያም አልፎ ተርፎ ለውጭ ሃይሎች አጎብዳጅነትን ተጠይፎ ብሔራዊ ጥቅምን ማስከበር ከሚጠበቅበት ግዳጅ አንዱና ዋናው ነው።
መንግሥት የተሰጠውን አደራና ሃላፊነት በአግባቡ ካልተወጣ ከሥልጣኑ ሊወገድ ይችላል፣ይገባዋልም።ባለሥልጣናት በግል ወይም በቡድን ጥቅም ተጠምደው የፈጸሙት ወንጀል ካለ በአገሪቱ ሕግ መሠረት ከተጠያቂነትና ከቅጣት አያመልጡም።
የመንግሥቱን ወይም የባለሥልጣናቱን የእለት ተእለት ተግባር የሚከታተል፣የሕዝቡን መብትና ጥቅም የሚያስከብረው የሕዝብ ተወካዬች ምክር ቤት ለዚህ ዋና መሳሪያ ነው።ምክር ቤቱ ሕግ ከማውጣቱ ባሻገር ሕጉ በትክክል ተተርጉሞ በሥራ ላይ መዋሉን የሚከታተሉ ከመንግሥት ቁጥጥር ነጻ የሆኑ የፍትህና አስፈጻሚ አካላቶች ይኖሩታል። እነዚህ የፍትሕ ተቋማት በመንግሥት ወይም በፖለቲካ ድርጅት የሚወከሉ ወይም የሚሽከረከሩ ግለሰቦች የሚሰገሰጉበት ሳይሆን በዕውቀትና በምግባራቸው፣ለሕሊናቸው ያደሩ፣ ለአገርና ለሕዝቡ ጥቅም ቃልኪዳን የገቡ፣ለእውነት መስዋእት ለመሆን እንጂ እውነትን መስዋእት ለማድረግ የማይሞክሩ ሰዎች የሚሰለፉበት የአገር አስተዳደር ጠንካራ ዋልታዎች ናቸው።
ከዚህ በላይ የተሰጠውን የመንግሥትን ምንነትና ተግባራት እንዲሁም አጋር ተቋማትን ሚናና ድርሻ በጥቂቱም ቢሆን የሚያሳይ ማብራሪያ እንደ መስተዋት ወይም እንደሚዛን ተጠቅመን በአገራችን ያለውን መንግሥትና የፍትህ ተቋማት ለመፈተሽ እንሞክር።
መንግሥት የሕዝብ ይውንታን ያገኘና አደራ የተቀበለ፣ በሕዝብ ፍላጎት የተሰዬመ ነው ከተባለ እስከአሁን ድረስ የነበሩትና ያሉት የኢትዮጵያ ስርዓቶችና መሪዎች ግን በዚህ መንገድ ያላለፉ ናቸው።በጉልበት እዬተቀባበሉ የሥልጣኑ ባለቤት የሆኑ አምባገነኖች ነበሩ፣ናቸውም።የጥንቶቹን ትተን በተለይም ላለፉት ሃምሳ ዓመታት የሥልጣኑ ባለቤት የሆኑትን በተለይም ከሦስት ዓመት ወዲህ በሥልጣን ላይ ያለውን ስንመረምር መንግሥት ሳይሆን ገዢና አምባገነን በሚለው ስያሜ መጠራት ያለበት ሆኖ እናገኘዋለን።
መንግሥት የሕዝብንና የእያንዳንዱ ዜጋ ሰብአዊ መብት የማስከበር ግዴታ ያለበት ሲሆን ስልጣኑን የያዘው ቡድን ግን ይህን አላደረገም፤አልፎ ተርፎም ሰብአዊ መብት የሚጥሰው እራሱ “መንግሥት” ነኝ ባዩ ነው።
መንግሥት ብሔራዊ ክብርን የሚያስከብር፣ከጠላት ጋር ያልወገነ፣የአገርን ብሔራዊ ክብር አሳልፎ የማይሰጥ መሆን ቢገባውም የኢትዮጵያ መሪዎች ነን ባዮች ግን ከራሳቸው ክብርና ሥልጣን በላይ የሚያስጨንቃቸውና የሚያሳስባቸው አይደሉም፣ለሥልጣናቸው ሲሉ ከባእዳን ጋር ይሞዳሞዳሉ፣ያገርን ጥቅም አሳልፈው ይሰጣሉ፤ከዚያም አልፎ ተርፎ የሚቃወማቸውን ይገላሉ፣ያስገድላሉ፣ያስራሉ፣ ያሳድዳሉ።
የሕዝብ ምክርቤትና የፍትሕ ተቋማት የሕዝቡን መብት ለማስከበር የሚቋቋሙ ናቸው ቢባልም በአገራችን ግን የስርዓቱ አገልጋይና የመጨቆኛ መሣሪያ በመሆን የሚያገለግሉ ናቸው።አባቱ ዳኛ ልጁ ቀማኛ እንደሚባለው አንዱ የሌላውን ወንጀል እዬሸፈነ፣ሌሎቹን ለማጥቃት የተሰለፈ የባለሥልጣናቱ ክብር ዘበኛ ሆኖ ያገለግላል።ለሆድ ያደሩ በጅምላ ተሰብስበው የሚወስኑበት፣መንግሥትን ወግነውና ደግፈው እጅ የሚያወጡበት እንጂ መንግሥት ጥፋት ሲያጠፋ የሚጠይቁና ወጥረው የሚይዙበት፣ደፋርና አገርወዳዶች የሚሟገቱበት መድረክ አይደለም።አባላቱ በመንግሥት ምስልና ቅርጽ የተሰሩ አሻንጉሊቶች ናቸው።የሚለያቸው ቢኖር ቅጥረኛ መሆናቸው ነው።ደመወዛቸውን ግን ከፋዩ የሚፈርዱበት ሕዝብ ነው።
መንግሥት ጎሳና ሃይማኖት ያለዬ፣ከሁሉም፣ለሁሉም፣በሁሉም የተቋቋመ ነው ቢባልም በአሁኗ ኢትዮጵያ ያለው መንግሥት ነኝ ባይ ግን በጎሳ ፖለቲካ የተካነ፣የጎሳ ማንነትን መጠቀሚያና መጉጃ ያደረገ፣ዜጋ በጎሳ ማንነቱና እምነቱ የሚገደልበት፣የሚፈናቀልበት ስርዓት የዘረጋ፣የሁሉም የሆነ አገር አፍርሶ የነጠላ ጎሳ አገር ለመገንባት ዓላማ ይዞ ደፋቀና የሚል፣ ቡድናዊነት የሚያጠቃው መሆኑ ይፋ ከወጣ ሰንብቷል። መሰሎቹን አዘጋጅቶና አስታጥቆ በተለያዩ ያገሪቱ አካባቢዎች አሰማርቶ ንጹሃን ዜጎች፣ በተለይም የአማራው ጎሳ ተወላጆች የሆኑ ሕጻናት፣አዛውንት፣ሴቶች እንዲጨፈጨፉ አድርጓል፤አሁንም እዬተጨፈጨፉ ነው።መልምለውና ባርከው ለሥልጣኑ ያበቁትን የህወሃት ወንጀለኞችን ጁንታ በሚል ስም ለማጥፋት በከፈተው ዘመቻ በትግራይ ንጹሃን ሕዝብ ላይ የፈጸመው እልቂትና የጦር ወንጀል ተጠያቂው በከይሲው አብይ አህመድ የሚመራው ሕገወጥ የማፊያ ስብስብ ነው።ለሃያ ሰባት ዓመታት አብሮ የዘረፋትን አገርና ቀፍድዶ የያዘውን ሕዝብ ላለፉት ሶስት ዓመታት በተረኝነት መከራ የሚያሳዬው አብይና አጋሮቹ የያዙት የጎሳ አምባገነን ስርዓት ነው። ይህንን ሃቅ የማያዬውና የወንጀሉ ተባባሪ የሆነው በጥቅም ዓይኑ የተጋረደው ወይም የዓላማው ተሸካሚ የሆነው የጎሳው ተወላጅ ነው።እንደሱ የመከራ ቀንበር ተሸክሞ የኖረ ወገኑን፣በጎሳ ማንነቱና በሚከተለው ሃይማኖቱ ለይቶ የሚገለው በጥላቻና በውሸት ትርክት ተግቶ ያደገው የኦሮሞ ጎሳ ተወላጅና የሌላው በዝቅተኝነት መንፈስ የሰከረው ጎሳ ተወላጅ ነው።እዚህ ላይ ግን መታወቅ ያለበት ከደሙ ንጹህ የሆኑ፣የሌላው መጠቃት የሚሰማቸውና ከተጠቂው ጎን የተሰለፉ ኦሮሞና የሌላው ጎሳ ተወላጆች እንዳሉና የጥቃት ሰለባ እንደሆኑ መካድ አይገባም።
አንዳንዶቹም ተምራናል የሚሉ በአገር ውስጥና በውጭ አገራ የሚኖሩ ግለሰቦችና ስብስቦች በአገራችን የሚካሄደውን የዘር ማጥፋት ወንጀል በመሸፋፈን፣ሰላም የሰፈነባት አገር በማስመሰል ስለመዋእለ ሃብት(ኢንቨስትመንት)እና ልማት ያወራሉ። የአብይ አህመድን አመራር በማወደስ የብልጽግና ጎዳና ተከፍቷል ይላሉ።ስለሚጠፋው የሰው ህይወትና በመፍረስ ላይ ስላለችው አገር መጨነቅና ማውራት ለእነሱ የለውጥ እንቅፋት መሆን ነው።
መንግሥት ተጠያቂነት ያለው፣የሚሠራውና የሚያቅደው ግልጽ የሆነና ሕዝብ የሚያውቀው፣ከሕዝብ ጀርባ ሴራ የማይጎነጉን ነው ቢባልም በኢትዮጵያ ያለው ግን አንድ ግለሰብ ብቻውን የሚወስንበት፣ያሻውን የሚያደርግበት የግል ኩባንያ ነው።ያሻውን ይሾማል፣ያሻውን ይሽራል፤ያሻውን ይሰራል፣ ያሻውን ያፈርሳል።ያሻውን ያስራል፣ያሻውን ይፈታል።ይህንን ሁሉ ደባ ሲሰራ ምድራዊ ሰውነቱን ክዶ በአምላክ ቅብአት የተፈቀደለት ንጉሥ ለመሆን የሚዋትት ብቻ ሳይሆን እራሱን ከአማልእክት በላይ አድርጎ የሚያስብ ዳግማዊ እዬሱስ ለመሆን የሚቃጣውን ግለሰብ፣ዝናብ አወርዳለሁ መብረቅ እጥላለሁ የሚለውን አብይ አህመድን አድርባዮቹ እያጨበጨቡ ነብይና ሙሴ እያሉ የእብሪትና የእብደት ካባ እያለበሱት ማንነቱን እንዲስት አድርገውታል።ጨዋታን ጨዋታ ያነሰዋልና የዛሬ ሶስት ዓመት ወደ ሥልጣን ሲመጣ “እናቴ የሰባት ዓመት ልጅ ሆኜ ሰባተኛው ንጉሥ ትሆናለህ ብላኝ ነበር” ሲል “ አብይ አህመድ ቦካሳን ቦካሳን ሸተተኝ” በሚል ጽሁፍ የዛሬውን ማንነቱን ለማሳዬት ሞክሬ ነበር፤ግን ማን ሰምቶ!
በተለይም ፊደል ቆጥረናል የሚሉ በውጭም በውስጥም ያሉ ምሁራን ነን ባዮች የስርዓቱ ሰለባ በሆኑት ንጹሃን ዜጎች፣ህጻናት፣አዛውንት፣እርጉዝ ሴቶችና እናቶች ሞት፣ስቃይና መፈናቀል ሲዛበቱና ድርጊቱን አይቶ እንዳላዬ፣ሰምቶ እንዳልሰማ ሆነው ሲክዱ ማዬት የበለጠ ያማል።ለነሱ ለውጥ ማለት አገር እዬፈረሰ የህንጻ መቆም፣እርሃብና በሽታ ሕዝብ ሲጨርስ በከተማ የሚሰሩ የመዝናኛ፣ ቦታዎችና ሆቴሎች መስፋፋት ነው።የህጻናት መደፈርና በድህነት ምክንያት ለፍትወት ገበያ መጋለጣቸው የቅንጦትና የቅብጠት ተግባር ሆኖ ይታያቸዋል። የሥልጣን ወይም የጥቅም ፍርፋሪ ካገኙ ለሌላው ደንታ የላቸውም።ቤተእምነቶች በእሳት ሲጋዩና ምእመናን ሲታረዱ፣ለለውጥ የሚከፈል ዋጋ አድርገው ይቆጥሩታል እንጂ ሃዘን አይሰማቸውም።አብይ አህመድም ከብርሃን በፊት የሚከሰት ጨለማ፣ከመውለድ በፊት የሚከሰት የምጥ ስቃይ ነው፤ስለዚህ ቻሉት እያለ በፓስተር ስብከቱ ሊያደነዝዝ ይሞክራል። ይባስ ብለውም የእምነት አባቶች ሳይቀሩ የመከራው ቁንጮ የሆነውን መሪ የሶስት ዓመት የስልጣን ዘመን እንደ ትንሳኤ ቆጥረው ለማመስገንና ለዘለዓለሙ ያንግሥህ! ለማለት የድጋፍ ሰልፍ ለመውጣት ያሰቡት ሽር ጉድ በተቃውሞ ድምጾች ለጊዜው ለማስቆም የተቻለ ቢሆንም በዬሆቴሉ አዳራሽ ክብረውዳሴው የስርዓቱ ቁንጮዎችና አጃቢዎቻቸው በተገኙበት ተካሄዷል።ያለፉት ሶስት ዓመታት ግን የግፍ ዋንጫው ሞልቶ የፈሰሰበት ፣ ዜጎች በዬቀኑ የሚጨፈጨፉበት፣አስከሬናቸው በየጫካው ተጥሎ ለአውሬ የተጋለጠበት፣ ጭካኔና መከራ በታሪካችን እንደዚህ ያልታዬበት፣የኑሮ ውድነት፣ስራአጥነት፣ፍርሃትና ስጋት የሰፈነበት፣መተማመን የጠፋበት፣ኢትዮጵያውያን የተጋለጥንበትና የምናፍርበት ወቅት ነው።
አድርባዮቹ ወንጀልና መከራውን የሚቃወሙትንና የሚያጋልጡትን ሃቀኞች ጸረ ለውጥ በማለት ይኮንናሉ፣ያወግዛሉ። የጊዜ ጉዳይ ነው ሁሉም በሰፈረው ቁና መሰፈሩ አይቀርም።እነዚሁ ይሉኝታ ቢሶች ባለተረኛ ሲመጣ ደግሞ መስሎ ለማደር የሚቀድማቸው የለም፤ የሚያግዳቸው የሞራል ግንብ አልፈጠረባቸውም። የሰውነት ሳይሆን የእስስትነት ጸባይ ስለተሸከሙ ይሉኝታ ቢሶች ናቸው።የሚገርመው ነገር አድርባይነትን የጥበብና የችሎታ መመዘኛ አድርገው የሚያዩ መኖራቸው ነው። ከመጣው ጋር አለማጨብጨብን፣ለፍትሕ መቆምን እንደ ጅልነት ይቆጥሩታል።ለእነዚህና ለጎሰኞቹ አገር ወዳድነት ተስፋፊነት ነው።ለነሱ አንድነትና አብሮነት ወራሪነት ነው።በአንድ መግባቢያ ቋንቋ እንናገር፣ በአንድ ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ ስር እንሰለፍ ማለት ለእነሱ የሌላውን እኩልነትና መብት መንፈግና መግፈፍ ማለት ነው።ለነሱ እኩልነት ማለት ተበታትኖ፣ሁሉም የዬራሱን ባንዲራ ሰፍቶ፣ መሬት ከልሎ፣የቀበሮ ጉድጓድ ቆፍሮና አድፍጦ እየተላለቀ መኖር ማለት ነው።ይህንን የሚያራምድ መንግሥት ነኝ ባይ የጥፋት ሃይል ነው የሚያደንቁትና የሚያጨበጭቡለት። በውጭ አገር የሚኖሩት ደጋፊዎቹ ከሚኖሩበት አገር የዴሞክራሲና ፖለቲካ ባህል ቅንጣትም አልተማሩም። ለእነሱ እውቀት ማለት ገንዘብ መሰብሰብ ነው።በምንም መንገድ ይሁን በምንም ገንዘብ ካገኙ ዓይናቸውን አያሹም።እንኳንስ ያገርና የወገን ክብር እራሳቸውንም ይሸጣሉ።
ከዚህ አይነቱ የመከራ ጊዜና ሕዝብ ካልመረጠው አገር አጥፊ የጎሰኞች ስርዓት እንዴት መገላገል ይቻላል? ለዚህ ጥያቄ መልሱ አጭርና አንድ ብቻ ነው
በስልጣን ላይ ያለውን ጎሰኛ ቡድንና ስርዓቱን ታግሎ ማሶገድ ነው።ለዘለቄታውም ሰላምና አንድነት በጎሳና በሃይማኖት የፖለቲካ ድርጅት እንዳይኖር የሚከለክል፣ ያለውን የጥፋት መመሪያ የሆነ ሰነድ በማገድ በሕዝቡ ተሳትፎና ተቀባይነት ያለው ሕገመንግሥት እንዲረቅ ማድረግ ነው።
ይህስ በማን ሊሠራ ይችላል? ለሚለው ጥያቄ ደግሞ መልሱ አገር ወዳዱ ሃይል በግንባር ተሰባስቦ ወይም ችሎታ ያላቸው ባለሙያዎች(ቴክኖክራትስ) የሽግግር መንግሥት ያቋቁሙ የሚል ሲሆን ለመፍጠር የሚቻልበትን መንገድ ነገ ዛሬ ሳይባል ምክክሩ መጀመር አለበት።በተለይም ወጣቱ ትውልድ ለዚህ ብሔራዊ ግዳጅ እንዲሰለፍ እድልና ቦታውን መስጠት የግድ ይላል።
ይህ የሽግግር አካል ፣እግረመንገዱንም አገር የሚያምሱትንም የጥፋት ሃይሎች ለመመከትና ለማሶገድ የሚችል ሕዝባዊ ሃይል ማዘጋጀትና ለጥቃት የተጋለጡትን ማስታጠቅ አንዱ ተግባሩ ይሆናል።የኢትዮጵያን አንድነት የሚሻው ጥቂት እንዳልሆነ መተማመን ያሻል።ብዙሃኑ ከተደራጀ ደግሞ የጥፋት ሃይሎቹ ዕድሜ በጣም አጭር ይሆናል።ወሳኙ የሕዝቡ ቁርጠኝነት ነው።ከሁሉም በላይ ግን በስሙ ወንጀል የሚፈጸምበት ማህበረሰብና ጎሳ በተለይም ኦሮሞው ስልጣኑን ይዞ አገር ለመበታተን ሲል የእርስ በርስ ግጭት እንዲነሳ ንጹሃን ዜጎችን የሚጨፈጭፈውን ቤተመንግሥትና ጫካ ውስጥ የሰፈረ ወንጀለኛ ቡድን የእኔ ጎሳ ተወላጅ ነው ሳይል ከእኩይ ምግባሩ እንዲታቀብ እርምጃ ሊወስድበትና ለፍርድም አሳልፎ ሊሰጠው ይገባል።የወንጀለኞች ዋሻ አለመሆኑን በተግባር ሊያሳይ ይገባዋል።
የትግራይ ተወላጆችም እንዲሁ አሁን ላሉበት ስቃይና መከራ የዳረጋቸውን፣ለሃያ ሰባት ዓመታት በስማቸው ሲነግድባቸው የኖረውን ህወሃትና መሪዎቹን ወግዱ ሊላቸውና ለፍርድ አሳልፎ ሊሰጣቸው ይገባል።ህወሃት በታሪክ፣በባህል፣በስነልቦናና ማህበራዊ ድር ተሳስረው፣ሌላውንም አስተባብረው ለኢትዮጵያ ስርዎመንግሥት ትልቅ ድርሻ ያበረከቱትን የትግራይንና የአማራውን ማህበረሰብ ደም አቃብቶ በጋራ እንዳይቆሙ አድርጓቸዋል።የአሁኑም ኦሮሞ መራሹ ቡድን ያንኑ የወያኔ ዱካ ተከትሎ እርስበርስ እንዲጋጩ፣በጠላትነት እንዲቆሙ አድርጓል።ለሁለቱም ሆነ ለሌሎቹ የኢትዮጵያ ማህበረሰቦች የሚበጀው በመካከላቸው ያለውን አለመገባባትና ወያኔ/ኦነግ/ብልጽግና ፈጠር ችግሮችና ልዩነቶች አሶግደው በጋራ መቆምና ለተተኪው ትውልድ የጋራ አገር ማስረከብ ነው።በደምና በአጥንታቸው የመሰረቷትን ኢትዮጵያን ከውድቀት ማዳን ነው።መከፋፈሉና እርስ በርስ መፋጠጡ ለነአብይ ኦነግና ለውጭ ጠላቶች አመቺ ሁኔታን ከመፍጠር ባለፈ የሚያገኙት ጥቅም አይኖርም።ትርፉ ተራ በተራ ወይም ተያይዞ ማለቅ ይሆናል።የግብጽና የሱዳን ድፍረትና ወረራም በስርዓቱ ምክንያት የተፈጠረውን በሕዝቡ መካከል ያለውን ክፍተት ተከትሎ የመጣ መሆኑን ማጤን ይገባል።ስለሆነም ለውጩም ሆነ ለውስጡ ችግር መወገድና ኢትዮጵያ እንደ አገር ለመቀጠሏ ወሳኙ የሕዝቡ አንድነትና በጋራ መቆም ነው። ጊዜው የውጭውን አድኑን እያሉ ከመማጸን ይልቅ በእራስ ተማምኖ የሚቆሙበት እና ለመዳን የሚሰለፉበት እንጂ የስርዓቱን ዕድሜ ለማርዘም ለምርጫ የሚዘጋጁበት አይደለም።
አሁን በታቀደው መንገድ ምርጫ እንዲካሄድ መፍቀድ ማለት ያለው ሕገወጥ ጎሰኛ ስርዓት በሕጋዊነት እንዲቀጥል መፍቀድ ነው።በቀጣይነት ሕዝብ እዬተገደለና እዬተፈናቀለ ይኑር ብሎ መፍቀድ ማለት ነው።ለመሆኑ ለምርጫ እራሳቸውን ያዘጋጁት ቡድኖች ዓላማቸውን ለሕዝቡ ለማቅረብና ለመወያዬት የሚችሉበት ዕድልና ሁኔታ ሳይኖር፣ሰላምና መረጋጋት በሌለበትስ አገር ምን አይነት ምርጫ ተካሂዶ እንመረጣለን ብለው ያስባሉ?በገሃድ ሲታይ በአገራችን ሰማይ ላይ የተንጠለጠለው ደመና ዝናብ ሳይሆን ደም ያረገዘ ይመስላል።ያንን የደም ደመና አውሎ ነፋስ ሆኖ መበተንና ማክሸፍ የሚችለው ህዝባዊ ሃይል ነው።ይቻላል! ከመምሸቱ በፊት አሁኑኑ ብልሃት ይፈለግለት።
አገሬ አዲስ

Source link

Related posts

ሃገር አቀፍ የትምህርት ብርሃን ምዘና መርሀ-ግብር ተጀመረ

admin

በኢትዮጵያ ስልጣን መያዣ መንገድ ዴሞክራሲያዊ እና ሰላማዊ የምርጫ ስልት ብቻ ነው –  ጠ/ሚ ዐቢይ

admin

በጋምቤላ ክልል በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች የህዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት እንዲሰሩ ተጠየቀ

admin