59.29 F
Washington DC
April 21, 2021
Satenaw Ethiopian News/Breaking News
Amharic News

“መሪነት ለሴቶች የተለየ ጥበብ ነው” ወይዘሮ ንፁህ ሽፈራው

“መሪነት ለሴቶች የተለየ ጥበብ ነው” ወይዘሮ ንፁህ ሽፈራው

ባሕር ዳር፡ የካቲት 29/2013 ዓ.ም (አብመድ) ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን (ማርች 8) ዛሬ በዓለም ለ110ኛ፣ በኢትዮጵያ ደግሞ 45ኛ ጊዜ እየተከበረ ነው፡፡ ቀኑ ሲከበር በየአካባቢው የሚገኙ የጠንካራ ሴቶችን የሕይዎት ተሞክሮ ለሌሎች ማካፈል አንዱ ዓላማው ነው፡፡ አብመድ በአማራ ክልል አዊ ብሔረሰብ አስተዳደር የዳንግላ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ ከሆኑት ብርቱ ሴት ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡ ዋና አስተዳዳሪዋ ወይዘሮ ንፁሕ ሽፈራው ይባላሉ፡፡ ለ10 ዓመታት በተለያዩ የሥራ ኀላፊነት ቦታ ሠርተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅትም የዳንግላ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ በመሆን የተሰጣቸውን ኀላፊነት በአግባቡ በመወጣት ላይ ይገኛሉ፡፡

አስተያየት እንዲሰጡን የጠየቅናቸው ሰዎችም “ታታሪ፣ የሴቶች ተምሳሌት፣ የአንድነት ምሰሶ” ሲሉ ገልጸዋቸዋል፡፡ አቶ ያረጋል ፈንቴ በዳንግላ ወረዳ በወረዳ አስተዳዳሪነት ተመድበው የሠሩ ሦስት አስተዳዳሪዎችን አማክረዋል፡፡ በአሁኑ ወቅትም ወረዳውን እያስተዳደሩ የሚገኙትን ወይዘሮ ንፁህ ሽፈራውን በማማከር ላይ ይገኛሉ፡፡ “ወይዘሮ ንጹሕ እያንዳንዱን ሥራ ቆጥራ የምትሰጥ፣ ቆጥራ የምትረከብ በሳል የመሪነት ስዕብና ያላት ሴት” ሲሉ ገልጸዋል፡፡ በመሪነት ዘመናቸውም እያንዳንዱ አመራር ከጎጠኝነት በፀዳ መንገድ ሥራን መሠረት አድርጎ ሕዝብን ማገልገል እንዳለበት የሥራ መመሪያ በመስጠት ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ እየሠሩ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ “የሠራ ሰው በእሷ ዘንድ እውቅና ያገኛል” ያሉት አቶ ያረጋል አስተዳዳሪዋ የዳንግላ ወረዳን ግንባር ቀደም ለማድረግ ዓላማ አድርገው እየሠሩ እንደሆነ ነግረውናል፡፡

ወይዘሮ ንፁሕ ሽፈራው እንደነገሩን ተወልደው ያደጉት ዳንግላ ወረዳ ነው፡፡ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከጨረሱ በኋላም በሴቶች አደረጃጀት ውስጥ በመግባት መሪነትን ተለማምደዋል፡፡ ካለፉት 10 ዓመታት ጀምሮ በተለያዩ የሥራ ኀላፊነት ቦታዎች ተመድበው ሕዝብ እያገለገሉ እንደሚገኙ ነግረውናል፡፡ በአሁኑ ወቅትም የዳንግላ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ በመሆን ሕዝብና መንግሥት የሰጡትን ኀላፊነት በአግባቡ ለመወጣት ከሌሎች የሥራ መሪዎች ጋር በመሆን በትጋት እየሠሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡

“አመራርነት በተሰለፉበት የሥራ መስክ ሕዝብን ለማገልገል ቁርጠኛ አቋም መውሰድ፤ ለዚህም መስዋእትነት መክፈልና የሕዝብን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ነው” ብለዋል ወይዘሮ ንፁሕ፡፡ የመሪነት ተልዕኳቸውን በአግባቡ ለመወጣት የሥራ ሠዓት በአግባቡ ይጠቀማሉ፤አምሽተው ይሠራሉ፤ እሁድ፣ ቅዳሜና በበዓላት ቀናት ጭምር በሥራ ቦታ ይገኛሉ፡፡ በዚህ ወቅት የሥራ ጫናን የሚረዳና ከጎናቸው በመሆን ቤተሰብን የሚንከባከብ የትዳር አጋር እንዳላቸውም አስታውቀዋል።

ወይዘሮ ንፁሕ እንደገለጹት እሳቸው አሁን ለደረሱበት የመሪነት ደረጃ እንዲደርሱም የባለቤታቸው እገዛ ከፍተኛ ሚና አለው፡፡ የተሠጣቸውን የሕዝብና የመንግሥት ኀላፊነት ለመወጣት ሲሉ በስራ ምክንያት ዘግይተው ወደ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው ልጆችን በመንከባከብና ቤቱን በማስተካከል በጥሩ ስሜት እንደሚቀበላቸውም ተናግረዋል፡፡

“መሪነት ለሴቶች የተለየ ጥበብ ነው” ብለዋል ወይዘሮ ንጹሕ፡፡ ሴቶች ከቤት ውስጥ ቤተሰብን ሲመሩ ያገኙትን ልምድ ወደ ውጭ በማውጣትና በሥራ ቦታም ባለሙያዎችና የሥራ ኀላፊዎችን አግባብቶ የመሥራት ክህሎታቸው ከፍ ያለ መሆኑን በማስረዳት፡፡ “ታታሪ ሴቶች ወደ መሪነት ሲመጡ ረጅም ጊዜ በሥራ ቦታ ያሳልፋሉ፤ በልዩ ልዩ ምክንያቶች ከሥራ ውጭ የሚባክን ጊዜ አይኖራቸውም፤ የተሰጠን ሥራ ግንባር ቀደም በመሆን ሠርተው ያሠራሉ” ሲሉ ነው የሴቶችን የኀላፊነት ብቃትን የገለጹት፡፡

ዋና አስተዳዳሪዋ ኀላፊነትን በአግባቡ አለመወጣት እነሱን ተከትለው ወደ ኀላፊነት የሚመጡ ሴቶችን እድል መዝጋት እንዳይሆን በጥንቃቄ መሥራት እንደሚገባ መልእክት አላቸው፡፡ ሴቶች ከየትኛውም ሥራ በበለጠ ልጆቻቸውን ተንከባክበው ጥሩ ደረጃ ላይ እንዲደርሱላቸው መፈለግ፣ በሥራ ኀላፊነት የሚገኙ ሴቶች ሥራቸውን በብቃት አከናውነው ሞዴል አለመሆን፣ አመራርነትን የማይረዳ ቤተሰብ መኖር፣ የቤት ውስጥ ጉድለቶችን ለመሸፈን መጣር፣ በልዩ ልዩ መድረኮች ስለሴቶች ተጠቃሚነት የሚደረጉ ንግግሮች ወደ ተግባር አለመቀየር እና መሰል ክፍተቶች ሴት መሪዎች ውጤታማ እንዳይሆኑ እንቅፋቶች ናቸው ብለዋል፡፡

ፈተናዎች ቢያጋጥሙ ችግሮችን ተቋቁሞ መሥራት የሴቶች ልዩ ብቃት ሊሆን ይገባል ነው ያሉት፡፡ እሳቸውም ወደ መሪነት ከመጡ በኋላ የነበሩ ክፍተቶችን በመለየትና የአሠራር ሥርዓትን በመዘርጋት በርካታ ጉዳዮችን ማስተካከል መቻላቸውን ተናግረዋል፡፡ በተለይም ያለአግባብ የተሠሩ ሥራዎችን በማጥናትና ኦዲት በማስደረግ እንዲታረሙ ተደርገዋል ነው ያሉት፡፡

ወይዘሮ ንፁሕ እንደተናገሩት በዳንግላ ወረዳ ከ156 ሺህ በላይ ሕዝብ ይገኛል፡፡ ወረዳው በርካታ የተፈጥሮና ሠው ሰራሽ ሀብት ባለቤት ነው፡፡ ይህንን ሀብት በአግባቡ በመጠቀም በልማት፣ በትምህርትና በጤናው ዘርፍ ልዩ ትኩረት ሰጥተው ለመሥራት እቅድ ይዘዋል፡፡ በመጨረሻም ሴቶች በመጪው ሀገራዊ ምርጫ በንቃት በመሳተፍ መብታቸውን ማረጋገጥ እንዳለባቸው መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ በክልልና በፌዴራል ደረጃ ሕዝብን የሚወክሉ ሴቶች የሴቶችን መብት ማስከበር የሚችሉ መሆን እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል፡፡

ዘጋቢ፡- አዳሙ ሽባባው፡፡

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡

Source link

Related posts

መቐለን ጨምሮ የብር ቅያሪ ከተጀመረ 14 ቀናት ባለፋቸው የትግራይ ከተሞች አገልግሎቱ መጠናቀቁ ተገለፀ

admin

“ዓድዋ የጥቁር ሕዝቦች መኩሪያ፣ የነጻነታችን ምልክት፣ የኢትዮጵያ ሕዝቦች የአንድነት ተምሳሌት፣ በኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ደም የተገነባ የድል ቀን ነው” ርእሰ መሥተዳድር አገኘሁ ተሻገር

admin

“መካሪ የሌለው ንጉስ ያለአንድ አመት አይነግስ” – ከወይራው እርገጤ | Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider

admin