70 F
Washington DC
April 10, 2021
Satenaw Ethiopian News/Breaking News
Amharic News

“መረባ” ብላለች ያቺ የራያ እናት ሠላም እንዲመጣ ክፉ እንዳያገኛት”

“መረባ” ብላለች ያቺ የራያ እናት

ሠላም እንዲመጣ ክፉ እንዳያገኛት”

ባሕር ዳር፡ ጥር 07/2013 ዓ.ም (አብመድ) የራያ እናት መልካም ትወዳለች፤ መልካም ታደርጋለች፤ ብርሌ አንገቷ፣ የሚጣፍጠው አንደበቷ፣ አንጀት የሚያላውሰው እናትነቷ እና ከልብ የሆነው መልካም ምኞቷ ተናፋቂዎች ናቸው፡፡

ራያን የማይናፍቃት፣ ሊያያት የማይመኛት፣ አይቶ የማይወዳት፣ በትዝታዋ የማይንከራተትላት ያለ አይመስልም፡፡ ራያዎች እንኳን ሰዎቹ ወንዙ፣ ጋራው ሸንተረሩ፣ አየርና ምድሩ ሁሉ ይናፍቃል፡፡

“ወለል ያለው ሜዳ ራያ ራዩማ

መሆኒ አላማጣ ዋጃ ጃሪጋማ፣

መገን የቆቦ ሰው ጎብየና ሮቢት አቤት ያለው ግርማ” እንዳለ ከያኒው ግርማ ሞገሳቸው አጀብ ያሰኛል፡፡ ራያ በሠላም ጊዜ አራሽ በክፉ ጊዜ ተኳሽ ነው፡፡

ወንዶቹ መውዜራቸውን እና በወገባቸው ዙር በተጠመጠመው ዝናር ይዘው ለሀገር ሠላም ሲቆሙ እናቶች ደግሞ አምላካቸውን እየለመኑ ሀገር ሠላም እንዲሆን፣ ፍቅር እንዲመጣ፣ ርሃብ፣ ድርቅ፣ ወረርሽኝና ቸነፈር እንዳይኖር “እርፎ መረባ” እያሉ ይለምናሉ፡፡

ፈጣሪም ይሰማቸዋል፡፡ የለመኑትን ሁሉ ያደርግላቸዋል፡፡ ኢትዮጵያ ሠላሟን የሚመኙላት፣ ፍቅሯን የሚፈልጉላት፣ አጥብቀው ፈጣሪን የሚማፀኑላት፣ ደግ እናቶች አሉላት፡፡ የደጎችን ልብ ፈጥኖ የሚመለከተው ፈጣሪም ኢትዮጵያ ሳትደፈር፣ እንደታፈረች፣ እንደተከበረች፣ እንደተወደደችና እንደተናፈቀች እንድትኖር አድርጓታል፡፡

የኢትዮጵያ ፅናት፣ ቀደምትነት፣ አይሸነፌነትና አይበገሬነት ሚስጥሩ ብዙ ነው፡፡ የራያ እናቶች የጭንቅ ቀን ሲመጣ፣ መከራ ሲጋረጥ ለፈጣሪያቸው ምልጃና ልምና የሚያቀርቡበት የራሳቸው ሥርዓት አላቸው፤ “እርፎ መረባ” ይሉታል፡፡ በሀገር ጭንቅና መከራ ሲመጣ እርፎ መረባ የሚሉ እናቶች ከቤት ወጥተው በአንድ ላይ ተሰባስበው “እርፎ መረባ ሠላም ይግባ” እያሉ ይለምናሉ፡፡

ልመናውን የሚከውኑት እናቶች “ዱበርቲዎች” ይሏቸዋል፡፡ እኒህ ሠላምና ፍቅር ወዳድ የራያ እናቶች ነብሰ ጡር ሴት የመውለጃዋ ጊዜ ሲዳረስ፣ የተጋደለ ሰው ሲኖር እርቅ እንዲወርድ፣ ዝናብ ሲቀር፣ ወረርሽኝ ሲመጣ፣ ጦርነት ሲከሰት “መረባ” ለማለት ከቤት ይወጣሉ፡፡

የለመኑት ሁሉ ሳይሳካ “እርፎ መረባው” አይቋረጥም፡፡ አንበጣ ሲወርና በሌሎችም ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ እናቶች “እርፎ መረባው” ብለዋል፡፡ በመረባቸውም ፈጣሪ ክፉን እንዳራቀ ነው የነገሩን፡፡ ለሠላም፣ ለፍቅር፣ ለአንድነትና ለአብሮነት ፀሐይና ብርድ ሳይበግራቸው “መረባ” እያሉ ይለምናሉ፡፡

“ገዥ ከገዥ ይስማማ፣ ሞት ይብቃ፣ ሰላም ይምጣ፣ እናት አታልቅስ፣ አንድነት ይጠንክር፣ ኢትዮጵያን ክፉ አይንካት፣ ለኢትዮጵያ የማይበጅ ገለል ይበል፣ ለልጆች የማይበጅ ይጥፋ” ይላሉ፡፡

መረባ የሚያስብሉትን እናት “ምሰሶአችን፣ መሪያችን፣ አለቃችን” ይሏቸዋል፡፡ “እርፎ መረባው” ሲባል ቡና ይፈላል፣ ቄጠማ ይጎዘጎዛል፣ ስጦታ ይቀርባል፣ መረባው ይባላል፡፡ መረባው ሲደረግ ከፈጣሪ ደጅ ይደርሳል፣ ፈጣሪም ይቅር እንደሚል ይታመናል፡፡

አንዲት እናት “እርፎ መረባ” ሲሉ ሌሎች “መረባ” እያሉ ይቀበላሉ፡፡ መረባ የራያ እናቶች የቀደመ የፀሎት ሥርዓት ነው፡፡ “እርፎ መረባ ወደ ሀገራችን ሠላም ይግባ፣ ሠላም ስጠን፤ እርፎ መረባ ፍቅር ስጠን፤ እርፎ መረባ ጭንቅ ይራቅ፤ እርፎ መረባ ገበያው ጥጋብ ይሁን፤ እርፎ መረባ ሕዝቡ ይዋደድ፤ እርፎ መረባ ዓለሙና ደስታው ለእኛ ይሁን፤ እርፎ መረባ ሀገራችን ፍቅር ይግዛት፤ እርፎ መረባ በአንድነት ወስኮ እንጠመድ፤ እርፎ መረባ የሰው መውደዱን የቀና መንገዱን ይስጠን፤ እርፎ መረባ የሀዘን ቀን ይለፍ፤ እርፎ መረባ የታሰረ ይፈታ፤ እርፎ መረባ የሞተ ገነት ይግባ፤ እርፎ መረባ …” እያሉ ይማፀናሉ፡፡

በእርፎ መረባ ፈጣሪን መለመን ብቻ ሳይሆን፣ ጥበብ፣ ዜማ፣ መልካም ተስፋ፣ ብሩህ ሀሳብ አለ፡፡ ለኢትዮጵያ አንድነት ይለመናል፡፡ በዚያ ሥርዓት ውስጥ ሀገርና ሕዝብ ሠላም እንዲሆን በተደጋጋሚ ይጠራል፡፡

“እርፎ መረባ” የሚሉትን የራያ እናቶችን ያዬ ሁሉ የጨለመ የሚመስለው ጊዜ፣ የከፋ የሚመስለው ወራት፣ የማያልፍ የሚመስለው ችግር ሁሉ ሲቀለው ይታየዋል፡፡ በመልካም ልብ ሲማፀኑ ያያልና፤ የራያ እናቶች ዘመንን አሳልፈው የተቀበሉት፣ ዘመንን አሳልፈው የሚሰጡት፣ በጭንቅ ቀን የሚማፀኑበት፣ ተስፋና የጸሎታቸውን ፍሬ የሚያገኙበት መልካም ሥርዓት ነው ይሉታል፡፡

ልመናው ፈጣሪን ነውና እኔ በራያ እናቶች ፀሎት ተደምሜያለሁ፤ በፍቅራቸው ረክቻለሁ፤ ላልረሳቸውም በፍቅራቸው ትዝታ ተነድፌያለሁ፤ ስለፍቅር የሚጮህ አንደበት፣ ስለ ሠላም የሚሰራ ጉልበት፣ ከልብ የሚያዝን አንጀት፣ ሁሉን በአንድ የሚያይ ሥርዓት፣ ፍሬው ያማረ፣ መንገዱ የሰመረ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ዥንጉርጉር ናት፤ ደስ የሚል ቀለም የሞሸራት፤ ፍቅርና አንድነት ያጣበቃት፤ ታሪክ ያደመቃት፤ ጀግንነት ያረቀቃት፤ ዓለም የሚናፍቃት፡፡ ከሰሜን እስከ ደቡብ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ድረስ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ባሕል፣ ወግ፣ ሥርዓትና እሴት ቢመረምሩት እፁብ ይላሉ፡፡

ኢትዮጵያዊት እናት ጀግና ትወልዳለች፣ ጀግና ታሳድጋለች፣ ጀግናም ነች፣ ራያ ውብ ባሕል ያደመቃት፣ ውበት እንደዥረት የፈሰሰባት፣ ፍቅር እንደ ሸማ የሚለበስባት፣ ጀግኖች የሚወለዱባት ድንቅ ሞሰበ ወርቅ ናት፡፡

በሞሰበ ወርቁ ውስጥ ያልታየ፣ ያልተመረመረ፣ ያልተዘከረ፣ ያልተነገረ፣ ውብ ሕብስት አለ፡፡ ሂዱ ሞሰበወርቋን ቃኟት ሕብስቷን ትገልጥላችኋለች፡፡

“ሀገሯ ራያ የማር ወተት ሀገር፣

ከእርሷ ተለይቼ እንዴት ብዬ ልደር፣ ደብዳቤ ላኪልኝ ሁለት ወረቀት፣

አንዱን የሠላምታ አንዱን የናፍቆት” ተብሎም ይቀኙአል፡፡

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡

Source link

Related posts

የሱዳን ጦር የሦስተኛ ወገን ፍላጎት ለማሳካት እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ እንዲያቆም የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አሳሰበ፡፡

admin

ግድቡ በመጪው ሐምሌና ነሃሴ ወራት ሁለተኛውን ዙር ውኃ የማይዝበት ምንም ምክንያት እንደሌለ የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ገለጸ።

admin

የነዳጅ እጥረትን ለመፍታት የነዳጅ አቅርቦትን መጨመርና ሕገ ወጥነትን መቆጣጠር እንደሚገባ በዘርፉ የተሰማሩ ባለሀብቶች ገለጹ፡፡

admin