76.95 F
Washington DC
May 18, 2021
Satenaw Ethiopian News/Breaking News
Amharic News

“ሕዝቡ ነፃ ወጥቷል ከዚህ በኋላ ወደባርነት አይመለስም” የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አቶ አገኘሁ ተሻገር

“ሕዝቡ ነፃ ወጥቷል ከዚህ በኋላ ወደባርነት አይመለስም” የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አቶ አገኘሁ ተሻገር

ከወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ተፈናቅለው በስደት የሚኖሩ ዜጎች ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱም ርእሰ መሥተዳድሩ ጥሪ አቅርበዋል።

ባሕር ዳር፡ የካቲት 11/2013 ዓ.ም (አብመድ) ትህነግ ትንኮሳ የጀመረበት ቀን ዝክረ ጥቅምት 24 በጠገዴ ቅራቅር ከተማ ታስቦ ውሏል።

በአማራ ሕዝብ ላይ ትንኮሳ የጀመረው ትህነግ በተመሰረተበት ቀን ድል ሆኖ ለዘመናት ታፍኖ የኖረው የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ድሉን አክብሮታል። በዝክረ በዓሉ ቀን የተገኙት የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አገኘሁ ተሻገር ፀረ ሕዝብና ፀረ አማራ የነበረው ትህነግ ተሸንፎ በመገናኘታችን እንኳን ደስ ያለን ብለዋል።

የወልቃይት ጠገዴና የራያ ጉዳይ የአማራን ሕዝብ መስበሪያ ተደርገው ሲቆጠሩ እንደቆዩ የተናገሩት ርእሰ መሥተዳድሩ የሕዝቦች ጥያቄ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ጥረት ቢደረግም የትህነግ ቡድን ሳይቀበለው መቅረቱን አስታውሰዋል። በሀሳብ ሲረቱ በእብሪት ይሄዱ እንደነበርም ተናግረዋል።

የአማራ ሕዝብና መንግሥት ገፍቶ ወደግጭት አለመግባቱን የተናገሩት አቶ አገኘሁ ከግጭቱ አስቀድሞ ክልሉ የተረጋጋ እንዳይሆን ትህነግ ሲሠራ መቆየቱንም ገልጸዋል። የክልሉ መንግሥትም ከሁሉም በማስቀደም የክልሉን ሰላም መመለስ፣ የፀጥታ መዋቅሩን ማጠናከርና ሕዝቡን የማንቃት ሥራ መስራቱን ነው ያስታወሱት። የማታ ማታ ትህነግ በአማራ ሕዝብና በአማራ ክልል መንግሥት ላይ ግልፅ የሆነ ጦርነት እንደሚያውጅ ያስታውቅ ነበርም ነው ያሉት። ክልሉ በተለይም በጠለምት፣ በጠገዴ፣ በአርማጭሆና በራያ በኩል ኃይሉን ማደራጀቱንም አስታውሰዋል።

የትህነግ ዓላማ የአማራን ሕዝብ ቅስም በመስበር ኢትዮጵያን ማፈራረስ እንደነበርም ተናግረዋል። ለአማራ ሕዝብ የነበረው ግምት አናሳ መሆኑ ለውድቀቱ ምክንያት መሆኑንም አንስተዋል።

“የክልሉ መንግሥት ትህነግ በራያ እንጂ በአማርማጭሆ በኩል ጦርነት እንደማይጀመር ገምቶ ነበር፤ በአርማጭሆ በኩል የተደራጀ ኃይል ስለነበር በዚያ ቢጀምር ራሱን እንደማጥፋት ይቆጠራል፤ በቅራቅር ጦርነቱን ጀመረ፡፡ የወያኔ ቅስም የተሰበረውም በቅራቅር በኩል ዘጠኝ ጊዜ የማጥቃት ሙከራ አድርጎ ሳይሳካለት ቀርቶ ማክሰኞ ገበያን ሲለቅ ነው” ብለዋል።

ትህነግ ውጊያ በከፈተበት ወቅት የጠገዴ፣ የአርማጭሆና የጠገዴ ሚሊሻ የፈፀመው ጀብዱ የማይረሳ መሆኑንም ተናግረዋል። ውጊያው በተቀናጄ አመራር እንደተመራም አስታውሰዋል። በዚያ ውጊያ የማይታመን ጀግንነት፣ ታይቶ የማይታወቅ ወንድነት የታዬበት ነበርም ብለዋል። ውጊያው አማራን ማንበርከክ እንደማይቻል ያሳዬንበት ነውም ነው ያሉት።

“የተዋጋነው ራሳችንን ለመከላከል እና ለአርባ ዓመታት የተቀማነውን አማራነት ማንነታችን ለማስመለስ ነው” ብለዋል ርእሰ መሥተዳድሩ። በዘመቻው የአማራ ሕዝብ በአንድነት መሳተፉን የተናገሩት ርእሰ መስተዳድሩ የክልሉ ባለሀብቶች ያልተቆጠበ ድጋፍ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

“እኛ ቂመኞች አይደለንም ትህነግ የላከብንን ሠራዊት አሳክመን አብልተን ሸኝተናል”ነው ያሉት። በዘመቻው የነበረውን ትብብርና አንድነት በልማት ላይም መድገም እንደሚገባ ነው የተናገሩት።

ለወልቃይት ጠገዴና ሰቲት ሁመራ፣ ለራያ ሕዝብ አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግም ተናግረዋል።

“ሕዝቡ ነፃ ወጥቷል ከአሁን በኋላ ወደባርነት አይመለስም” ነው ያሉት።

የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ለአርባ ዓመታት ታግሏል፣ የትግሉ አላማ ተሳክቶለታልም ብለዋል። ባለፉት ዓመታት ተፈናቅሎ የሚኖረው የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ሀገሩ ነፃ ወጥቷል፣ የሰላም አየርም ነፍሷል ወደ ሀገራችሁ ተመለሱ ብለዋል ርእሰ መሥተዳድሩ።

የአማራና የትግራይን ሕዝብ አንድነት ለማስጠበቅ ሁሉም መሥራት አለበት ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ በተለያየ መንገድ የተለያየ አጀንዳ ለመስጠት የሚደረገው ጥረት ትክክል አይደለምም ብለዋል። ከዚህ በኋላ ሁለተኛ እንቅፋት አይመታንም ብለዋል ርእሰ መሥተዳድሩ በንግግራቸው።

“ዝክሩን ዛሬ የዘከርነው ቀን ጠፍቶ ሳይሆን ቀን መርጠን ነው ፣ ዝክሩ እጃችንን ለሰላም የምንዘረጋበት ነው” ብለዋል።

ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር በጋራ እንሠራለን ያሉት ርእሰ መሥተዳድር አገኘሁ አንድነታችንን የሚፈታተነውን መታገል አለብንም ብለዋል።

አማራ አንድ ነው፣ አንድነታችንን ለመከፋፈል ጥረት አድርገዋል ነገር ግን አልተሳከላቸውም፤ አንድነታችንን ማጠናከር አለብን ነው ያሉት።

“አማራን አሳንሶና ዝቅ አድርጎ የማዬት አጀንዳ ተዘግቷል፣ ከከፍታችን ከሚያወርዱንን አጀንዳዎች አንያዝ፣ በማንነታችን ለይተው የሚገድሉንን ለፍርድ እናቀርባቸዋለን፣ አማራን የሚያዋርድ እንቅስቃሴ የማታ ማታ መሸነፉ አይቀርም” ነው ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ።

የአካባቢው ማኅበረሰብ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ እንደሚመለሰም ርእሰ መሥተዳድሩ ተናግረዋል።

በትግሉ የተሰዉ ታጋዮችን ለመዘከር ያለመ የመንገድና የሙዚየም ግንባታ በርእሰ መሥተዳድሩና በሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በቅራቅር ከተማ ተቀምጧል።

በዝክረ ጥቅምት 24 መድረክ በዘመቻው አስተዋጽኦ ለነበራቸው ተቋማት፣ የፀጥታ አካላትና ግለሰቦች እውቅና ተሰጥቷቸዋል።

ዘጋቢ:-ታርቆ ክንዴ -ከቅራቅር

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡

Source link

Related posts

በመዲናዋ ለሚገኙ 828 አርሶ አደሮች እና የአርሶ አደር ልጆች የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ተሰጠ

admin

የጨቅላ ህጻናትን ሞት ለመቀነስ የሚሰራው ስራ ትኩረት እንዲሰጠው ተጠየቀ

admin

“ሳይደወል ቅዱስ …” መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ | Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider

admin