87.71 F
Washington DC
June 14, 2021
Satenaw Ethiopian News/Breaking News
Amharic News

ሕዝቡ በበዓል ግብይት ጊዜ በሐሰተኛ ገንዘብ እንዳይታለል ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበት ተገለጸ፡፡

ሕዝቡ በበዓል ግብይት ጊዜ በሐሰተኛ ገንዘብ እንዳይታለል ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበት ተገለጸ፡፡

ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 20/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በበዓላት ወቅት ግብይት ይጨምራል፣ ኀብረተሰቡም ለበዓል የሚያስፈልጉ ነገሮችን ለመግዛት ወደ ግብይት ማዕከላት ይወጣል፣ በግብይት ቦታዎች መጨናነቆችም ይፈጠራሉ። ታዲያ በዚህ ጊዜ “የገብያ ግርግር” እንዲሉ ምቹ ሁኔታውን በመጠቀም የስርቆትና በሐሰተኛ ብር የማጭበርበር ተግባር የሚፈጽሙ አይጠፉም።

የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ አቶ እምወደው ገብሬ ሽንኩርት በጅምላ የሚያከፋፍሉ ነጋዴ ናቸው፡፡ በየቀኑ ከፍተኛ ሽያጭ ያከናውናሉ፤ የጥሬ ገንዘብ ልውውጡም በዚያው ልክ ነው፡፡ ይሁን እንጂ እስካሁን በነበራቸው የንግድ እንቅስቃሴ ትክክለኛውን የገንዘብ ኖት ከሐሰተኛው መለዬት ባለመቻላቸው “ምናልባትም ተቀብዬ ለሌላ ሰው አስተላልፌ ይሆናል” ብለዋል፡፡

አውቀውም ይሁን ሳያውቁ ሐሰተኛ የብር ኖት ይዘው ቢገኙ በወንጀል እንደሚጠየቁ ያውቃሉ፡፡ ነገር ግን ቀድመው መከላከል የሚያስችል ዕውቀት የላቸውም፡፡

አማራጭ የክፍያ መንገዶችን ተጠቅሞ ለመገበያዬትም የማንበብና የመጻፍ እውቀት የላቸውም፣ ቸርቻሪዎችም ያንን ማድረግ እንደማይችሉ ተናግረዋል፡፡

አዲሱ የብር ኖት ጥቅም ላይ ከዋለ ጊዜ ጀምሮ ሐሰተኛ ብር ለግብይት እየዋለ እንደሆነ ሪፖርቶች ያመላክታሉ፡፡ ጊዜው የበዓል ግብይት የሚከናወንበት በመሆኑ ማኅበረሰቡ በሐሰተኛ ገንዘብ እንዳይታለል ለማድረግ እየተሰሩ ያሉ ሥራዎችን በተመለከተ አሚኮ የሚመለከታቸውን አካላት ጠይቋል፡፡

በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የባሕር ዳር ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ ሞላ ምንውየለት እንዳሉት በሐሰተኛ ገንዘብ መታለልን ለማስቀረት በግብይት ጊዜ የጥሬ ገንዘብ ልውውጥን መቀነስ ይገባል፡፡ ለዚህም አማራጭ የክፍያ መንገዶችን መጠቀም እንደሚቻል መክረዋል፡፡ የተለያዩ የባንክ አገልግሎቶችን ማለትም እንደ ሞባይልና ኢንተርኔት ባንኪንግ አገልግሎት የመሳሰሉትን፣ ለትላልቅ ግብይቶች ደግሞ “ፖስ” ማሽንን በመጠቀም መክፈል ይመከራል፡፡ በአቅራቢያ ወደሚገኝ ባንክ በመሄድም ከሂሳብ ወደ ሂሳብ ማዘዋወር ይቻላል፡፡ ይሕም ኅብረተሰቡን ከጉዳት ይታደጋል ብለዋል፡፡

ከዚያ ውጪ በጥሬ ገንዘብ ግብይት በሚደረግበት ጊዜ የሚገበያዩበት ገንዘብ እጃቸው ላይ ካለ የብር ኖት በቀለም፣ በክብደትና በሌሎች መመዘኛዎች አይተው አጠራጣሪ ከኾነ ወደ ባንክ ሄደው ማረጋገጥ አለባቸው፡፡ ሐሰተኛ ኾኖ ከተገኘም ለፖሊስ እንዲያሳውቁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ሥራ አስኪያጁ እንዳሉት ማኅበረሰቡ በሐሰተኛ ገንዘብ አዘዋዋሪዎች እንዳይታለል በተለያዩ አማራጮች ግንዛቤ እየተፈጠረ ነው፡፡

የሐሰተኛ ብር ኖት ዝውውርን መከላከል አንድ ተግባር ቢሆንም ከምንጩ ማድረቅ ግን ከመንግሥት የሚጠበቅ ሥራ መሆኑን አንስተዋል፡፡

በበዓል ወቅት ሊከሰቱ ከሚችሉ የወንጀል አይነቶች አንዱ ሐሰተኛ የብር ኖትን ለግብይት ማዋል እንደሆነ የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ገልጿል፡፡

ሐሰተኛ የብር ኖት በሌሎች ጊዜያትም የሚስተዋል ወንጀል ቢሆንም በበዓላት የግብይት ጊዜ በስፋት ሊኖር ስለሚችል ጥንቃቄ እንዲደረግም አሳስቧል፡፡ ኮሚሽኑም ወንጀሉን ለመከላከል ዕቅድ በማዘጋጀት እየሠራ ነው ተብሏል፡፡

በኮሚሽኑ የማኅበረሰብ አቀፍ ወንጀል መከላከል መምሪያ ኀላፊ ኮማንደር ጀማል መኮንን እንዳሉት በተለይ በእንስሳት ግብይት ጊዜ ሐሰተኛ የብር ኖት ለአርሶ አደሮች የመክፍል ሁኔታ ይስተዋላል፤ ይህም አርሶ አደሮች የለፉበትን ከማሳጣት ባለፈ በሕግ ተጠያቂ እንደሚያደርጋቸው አስታውቀዋል፡፡

ለትንሣዔ በዓል በተለይ በእንስሳት ግብይት ወቅት ከፍተኛ የገንዘብ ልውውጥ ስለሚደረግ ከተቻለ ክፍያ በባንክ ቤት መፈጸም አለበለዚያም የሚያውቁ ሰዎችን ይዞ መገበያዬት ይገባል ብለዋል፡፡

የትንሣዔ በዓልን አስመልክቶ የሐሰተኛ ገንዘብ ግብይትን ለመከላከል በክልሉ የተዘጋጀው ዕቅድ ወደ ዞኖች ተልኳል፤ ዞኖችም ዕቅዱን ከልሰው በተዋረድ ተደራሽ እንደሚያደርጉ ነው

ኮማንደር ጀማል የተናገሩት፡፡

ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡

Source link

Related posts

የህዳሴው ግድብ ሁለተኛ ዙር ሙሊት በተያዘለት ጊዜ ይካሄዳል- አቶ ደመቀ

admin

ታክስ ማጭበርበር የግብር አሰባሰብ ሂደቱ ላይ ጫና እየፈጠረ መሆኑን የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ አስታወቀ፡፡

admin

“ከክልሉ ውጭ የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም የሚደረገው ጥረት ትርጉም ባለው መንገድ አልተሠራም” ኮሚሽነር ዘላለም ልጃለም

admin