70.74 F
Washington DC
May 14, 2021
Satenaw Ethiopian News/Breaking News
Amharic News

ልደቱ ሳያመልጠን – ሰመረ አለሙ | Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider

የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች አንድም ሀገርን ለማገልገል በሌላዉ በኩል ደግሞ የፓርላማ ወምበር በመያዝ ጠቀም ያለ ገቢና በህዝብ ተወካይነታቸዉ የሚያገኙትን ጥቅማ ጥቅም በማስላት ወደ ምርጫዉ እየተንደረደሩ ነዉ። ዝግጅቱ መልካም ሁኖ መራጩ ህዝብ ተመራጮቹን እንዲያዉቃቸዉ የብቃት መለኪያ የሆኑ ጠንከር ያሉ ጥያቄዎችን በጋዜጠኞች አማካይነት ቢቀርብላቸዉ መራጩም ፕሮግራማቸዉን፤ልምዳቸዉን፤በችግር ጊዜ የመምራት አቅማቸዉን በመመዘን ድምጹን ለተመራጩ ፖለቲከኛ ይሰጣል  ተመራጮችም  ምርጫዉን ካሸነፉ የገቡትን ቃል ካልጠበቁ ወጥሮ የሚይዝበት የቃል መተማማኛ ይሆናል ማለት ነዉ።

ተፎካካሪዎች ለህዝብ በተደጋጋሚ ቀርበዉ እይታቸዉን ፕሮግራማቸዉን ሀገር አደጋ ላይ በወደቀችበት  ወቅት ድፍረታቸዉንና በችግር ጊዜ መላ ፈላጊነታቸዉ ከወዲሁ ይጤናል። ተፎካካሪዎችን ጠበቅ ባለ ጥያቄ  አቅም ባላቸዉ  ሀገር ወዳድ ጋዜጠኞች እንዲቀርብ ቢደረግ በቲፎዞና በያዙት ሚዲያ ሰማይ የተሰቀሉትን ፖለቲከኞች ምድር አዉርዶ ማንነታቸዉ እንዲጋለጥ ይረዳል።

እንግዲህ  ከላይ ባለዉ ሀሳብ ከተስማማን አእምሯችን ዉስጥ የሚጉላላዉ እንደ ታይሰንና ኢቫንደር ሆሊ ዉድ ግጥሚያ የተመለካቹን ቀልብ የሳበና በጉጉት የሚጠበቀዉ የሁለቱ ከባድ ሚዛን ተጋጣሚዎች የአቶ ልደቱ አያሌዉና የዶ/ር ብርሀኑ ነጋ ይሆናል ማለት ነዉ። እነዚህ ግለሰቦች ክልል ስለተባለዉ አጥር፤አለም አቀፍ ግንኙነትን፤የአዲስ አበባን ባለቤትነት፤ እየናረ ስለመጣዉ የኑሮ ዉድነት፤ዜጎች በየቦታዉ እንደ አዉሬ እየታደኑ ስለሚታረዱበት፤ መከላከያዉንና የዉጭ ጉዳይን ፖሊሲ፤  ሌሎችም ህዝባዊ ጉዳዮች ፕሮግራማቸዉ ይፈተሻል ። በዚህ አጥጋቢ መልስ ያገኘዉ መራጭ ይህንን ተንተርሶ ዉሳኔዉን ይሰጣል ኮሮጆ ካልተገለባበጠ።

ልደቱ አያሌዉና ዶር ብርሀኑ በጋራ  ለመራጩ ህዝብ በተለያዩ አገራዊ ጉዳዮች ምልከታቸዉን እንዲሰጡ ተደጋግሞ ቢጠይቅም ዶር ብርሀኑ የልደቱ ስም ሲነሳ ቱግ ግንፍል እያሉ ለገላጋይ ሲያስቸግሩ በቴሌቭዥን መስኮት ተመልተናቸዋል። በተመሳሳይ ሁኔታ የድርጅታቸዉ ሰዉ አቶ ግርማ ሰይፉ በቅርቡ የፓርቲ ተወካዮችን ሰብስቦ ላናገራቸዉ ጋዜጠኛ ለገላጋይ እስኪያቸግሩ መረን በለቀቀ መልኩ ጠያቂዉ ላይ ጫና ሲያሳድሩም ተስተዉሏል። እንዲህ አይነት ቦታ ሲጋበዙ ለተጠየቁት ጥያቄ መመልስ እንጂ እንካ ስላንትያ ባላስፈለገ ነበር።

ወደ ዋናዉ ጉዳይ ስንገባ ዶ/ር ብርሀኑና የድርጅታቸዉ መሪዎች ያልተገነዘቡት ነገር ፓርቲ መስርተዉ ለስልጣን ሲዉተረተሩ መሪዎቹ የግላቸዉ መሆናቸዉ ቀርቶ የህዝብ መሆናቸዉን አለመረዳታቸዉ ነዉ። እንዲህ አይነቱ ጥያቄ ስለ ሀገራችን በመሆኑ እመራችሗለሁ ብሎ የሚመጣ ፖለቲከኛን ፕሮግራሙን በአስጨናቂ ጥያቄ ሊጠይቅ ይገባል ይህም የመራጩ መብቱም ጭምር  ነዉ።  ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ ዶክተር ብርሀኑና አረጋዊ በርሄ ጥያቄ ሲጠየቁ ጥያቄዉ እንዲህ መሆን ነበረበት የሚል አባዜ አላቸዉ እራሳቸዉን ጠይቀዉ እራሳቸዉ ሲመልሱም ታዝበናል።

በሌላዉ ወገን ልደቱ አያሌዉ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ለጠላቶቹ አይቆረጠም የብረት ቆሎ ሁኖ ዛሬም ድረስ ተፈርቶ፤ ተጠልቶ፤ተደንቆ ይኖራል። ሰሞኑን እንኳን ልደቱ የታሰረበትን ሀሳብ በአቶ የሸዋስ የኢዜማ አመራር በደብዳቤ ለዶር አብይ ተልኮ አንብበናል። ብዙ ስለልደቱ ከተነገረዉ ተባራሪ ወሬ ይልቅ በቅርቡ ዶ/ር ሲሳይ መንግስቴ ልደቱን እንደገና ፈጥረዉታል በሚያስብል መልኩ በየኛ ቴሌቭዥን ቀርበዉ ምልከታቸዉን አካፍለዋል።

እንደ ዶ/ር ሲሳይ መንግስቴ ምስክርነት አልተማረም ለሚሉት የእዉቀት ክፍተቱን ተከታታይ ኮርሶችን በመዉሰድ እራሱን ከፍ ወዳለ ልቀት ወስዷል።

በምርጫ 97  የተጨበረበረዉን ድምጽ አስመልክቶ ወያኔ ሳይጠናከር በህዝባዊ ማእበል ይናጥ ብሎ ቢጠይቅም እነ ዶ/ር ብርሀኑ ነጋ ግን እስቲ ረጋ ብለን ፈረንጆቹ የሚሰጡትን ዉሳኔ  እንጠብቅ በማለታቸዉ ምርጫዉ በአዉሮፓ ታዛቢዎች ከጸደቀ በሗላ ሰልፍ  እንዉጣ ብለዉ ዳግም ቢጠይቁት አሁን ጊዜዉ አልፏል እልቂት እናመጣለን ማለቱን አያይዘዉ ነግረዉናል።

ልደቱ በዚህም ሳያበቃ ከ100 በላይ ያሸነፍንበትን  መቀመጫ እንደያዝን ወደ ፓርላማ እንግባ ብሎ በመጠየቁ ምን ያህል እንደተብጠለጠለ ይህን ጽሁፍ የሚያነብ  አንባቢ በሚገባ የሚያዉቀዉ ጉዳይ ሁኖ በወቅቱ ልደቱ እንዳለዉ ፓርላማ ቢገባ ኑሮ እንዲህ ያለ ቁጥር የመለስ ዜናዊን ብልግና ከማብረዱ ባሻገር ፓርላማዉ ከህወአትና ከህወአት ሰራሺ አባሎች ድኖ ቁም ነገር ያለዉ ስራ ይሰራበት ነበር።

ባሁኑ ጊዜ ልደቱ አያለዉ ፖለቲካ ትርፍ ስላላመጣለት ይሁን ወይ በግል ምክንያቱ ፖለቲካን በትዝብት ለማየት ዳር ዳር እያለ በመሆኑና እንደ ሌሎቹ ፖለቲከኞች ቲፎዞም ሆነ የመገናኛ ሺፋን በብቃት  ስለማይሰጠዉ ለማን ብዬ ነዉ  በሚል እሳቤ የህይወት ጉዞዉን ለመቀየር ያሰበ ይመስላል።

በተመሳሳይ ሁኔታ ዶር ብርሀኑ ነጋ ምንም እንኳን ከአካዳሚክሱ አለም እየተፋቱ ቢመጡም በተለያዩ የፖለቲካ ድርጂቶችና ጊዜ እራሳቸዉን በማስተካከል ወደ ሀገር ቤት ገብተዉ የኢዜማ ሊቀመንበር ሁነዋል። ፓርቲያቸዉ በለስ ከቀናዉ ጠ/ሚኒስተርም ሊሆኑ ይችላሉ።እዚህ ላይ ከትህነግ ጋር ጉሮሮ ለጉሮሮ ተናንቀዉ የቆዩ የሀገር ቤት ታጋዮች እያሉ እመራሩን እንዴት  እንደያዙት የቅርብ ጓደኛቸዉ አቶ አንዳርጋቸዉ ጽጌ ምልከታቸዉን ቢያጋሩን መልካም ይሆናል።

ዶር ብርሀኑ ለንግግር ወደ መድረክ ብቅ ሲሉ ጥንቃቄ አያደርጉም ይህ የሚመጣዉ ወይ ህዝብን ማስተዋል አይችልም ከሚል ንቀት ሲሆን በሌላ በኩል የሳቸዉ የሀሳብ ጥራት ለቦታዉ ባለመመጠኑ ነዉ። ወደኛ የሚደርሰዉ ንግግራቸዉ ብዙ ግድፈት ይሰተዋልበታል ለምሳሌ ደጋግመዉ ዶር አብይና ታከለ ኡማ ያሻግሩናል ከማለት አልፈዉ ይህ ባልደራስ የምትሉት ይህ አማራ የምትሉት  በማለት እንደሳቸዉ ፓርቲ ሁሉ እዉቅና የተሰጣቸዉን ፓርቲዎችም ሲተቹ ተሰምተዋል።

ዶክተሩ በብልጽግና ላይ እንዲህ ያለ ጠንካራ እምነት ካላቸዉ ለምን ተዋህደዉ አይሰሩም የሚሉ ጠያቂዎች ብዙ ናቸዉ። በስሜነህ ባይፈርስ ቃለ መጠይቅም ያቃቃራቸዉ አንዱ ጥያቄ ይህ ይመስላል። እንግዲህ ልደቱ ለህወአት ቅርብነቱን በወሬ ካልሆነ በስተቀር በተጨባጭ የምናዉቀዉ ነገር የለም ዶ/ር ብርሀኑ ግን የዩኒቭረስቲ አስተማሪዎች ሲባረሩ ተክተዉ መስራታቸዉን መለስ ዜናዊና ታምራት ላይኔ ቢሮ ወጣ ገባ ይሉ እንደነበር በፎቶግራፍ ከዚህ ቀደም ተመልክተናል ሳይቀያየሙ በፊት ማለት ነዉ።ዶክተሩ እጣ ፋንታቸዉ ሁኖ  ነገር ይከተላቸዋል መሰል ከግብጽም፤ ከጠላት አገርም አዛምደዉ የሚተቿቸዉ ቀላል አይደሉም።   ከወደ ግብጽ ለኢሳት ብር እንደተሰጠ አንድ ሰሞን ሲናፈስ ነበር ጠያቂ ባለመኖሩ በዚህም ነገር በቂ ምላሻቸዉን አልሰጡም የዉሾን ነገር ያነሳ ዉሻ ይሁን ተብለዉ ታልፈዋል።

ዳግም ወደ ጉዳዬ ስመለስ ዶር ብርሀኑና ልደቱ አያሌዉ የግል ጠብ የላቸዉም ዶ/ር ብርሀኑ ወያኔ ሳይሆኑ ልደቱ ብቻ ወያኔ መሆኑ ብዙም አመንክዮ የለዉም። ስለዚህ ይህን አጋጣሚ ተጠቅመዉ ልምዳቸዉን፤ የሀሳባቸዉን ጥልቀት፤ በስነ ስርአት ለኢትዮጵያ ያላቸዉን ህልም አብረዉ በሚዲያ ቀርበዉ በጋዜጠኞች  አማካይነት  እንዲያስረዱን ቢደረግ ቢያንስ ለሚቀጥለዉ ምርጫችን ጥሩ መደላደል ይፈጥራል እንደትምህርትም ይወሰዳል የሚል እምነት አለኝ። እንደዉም ይህ አሰራር ከተለመደ ወደፊት በደቦ፤ በሚዲያ ሺፋን፤ በገንዘብ ለዚህ ቦታ እራሱን እጩ ያደረገ ወይ እራሱን ያስተካክላል ወይ ቦታዉን ብቁ ለሆኑ ዜጎች ይለቃል ማለት ነዉ።  በተገቢዉ ቦታም ተገቢዉ ሰዉ ይቀመጣል ማለት ነዉ።

ባጠቃላይ ምንም እንኳን የዶር ብርሀኑና የልደቱ አያሌዉ ዉይይት ተጠባቂና ተናፋቂ ቢሆንም በተመሳሳይ ሁኔታ ከንግግሩ ልንጨብጠዉ ያልቻልነዉና የሁለት ሰዎች አባል ፓርቲ መሪ የሆነዉ አረጋዊ በርሄን ከኢንጂነር ይልቃል ጌትነት፤ ሺመልስ አብዲሳን/ታየ ደንዳን ከዶ/ር ሲሳይ መንግስቴ፤ ታከለ ኡማን ከተፈታ ከእስክንድር ነጋ ጋር ሊያሸንፍ ይችላል ተብሎ ከእስር ካልተፈታም በቪዲዮ ግንኙነት ካለበት ቦታ ወይም ደግሞ ካልታሰሩት የባልደራስ አባላቶች ጋር፤ ጣሂር መሀመድ ከመራራ ጉዲና፤ ዶር ደሳለኝ ጫኔ ከዳዉድ ኢብሳ፤አባዱላ ገመዳ ሰዉ ተፈልጎለት እንደአቅማቸዉ (እንደክብደታቸዉ) እየተጣመሩ ካለፈዉ ድርጊታቸዉ ወንጀላቸዉ ጋር እየተነጻጸረ ጥያቄና ምርመራ ቢደረግባቸዉ ጥሬዉን ከብስሉ የዋሁን ከቀበሮዉ ከመለየቱም በላይ ካሁን በሗላ ምርጫ በሀሳብ ልቀት፤በእዉቀትና በሀገር መዉደድ ስሜት ላይ ብቻ ያተኮረ ይሆናል ብለን እናምናለን።

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር   ሰመረ አለሙ semere.alemu@yahoo.com

Source link

Related posts

የእንስሳት ሃብትን ለማዘመን መንግሥት የመሬት፣ የብድር አቅርቦት እና የግል ባለሃብቱን ማሳተፍ እንደሚገባው የአማራ ምሁራን መማክርት ገለጸ፡፡

admin

71 ሚሊየን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው መድኃኒቶችና የህክምና ግብዐቶች ወደ ትግራይ ተልከው እየተሰራጩ ነው

admin

አደዋ –   ማላጂ

admin