31.01 F
Washington DC
March 2, 2021
Satenaw Ethiopian News/Breaking News
Amharic News

ለዓመታት የጨለመች በወራት አበራች። | የአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት

ለዓመታት የጨለመች በወራት አበራች።

ባሕር ዳር ፡ የካቲት 13/2013 ዓ.ም (አብመድ) መሬትን ወዶ ሕዝብን መጥላት፣ ከአንድ እናት ልጆች ለአንደኛው ማዳላት፣ አንዱን ክሶ ሌላኛውን መጉዳት፣ አንዱን ጠብቆ ሌላኛውን ማጥፋት፣ በልቶ አለመጥገብ፣ ከልጅነት እስከ ሞት መስገብገብ መታወቂያው ነው ይሉታል ፖለቲከኞች። ኢትዮጵያን የሚወድ፣ በተለይም ከአማራ የሚወለድ ሁሉ ጠላቱ ነው። ለዓመታት በዘለቀው የሥልጣን ዘመኑ በአማራ ሕዝብ ላይ አያሌ ግፎችን አድርሷል።

ሲሻው ማፈናቀል፣ ሲሻው መግደል፣ እንዲያም ሲል ማሰር፣ ታሪኩን ማጠልሸት በሚወዳት ሀገሩ በሰላም እንዳይኖር ማሳደድ ተቀዳሚ ዓለማው ነበር። አማራ በሰፋች ሀገር አልጠብም፣ ዋጋ የተከፈለባትን ሀገር አላሳንም፣ በአባቶቼ አልወቀስም፣ ታሪክ አላረክስም ይላል። ኢትዮጵያን አብዝቶ ይወዳል። በሚወዳት ሀገሩ ተዘዋውሮ መሥራትን ይፈልጋል። በደል ሲመጣበት በቀላሉ አይገነፍልም። ስለሀገር፣ ስለፍቅር፣ ስለ ኢትዮጵያዊነት እና አንድነት ሲል አብዝቶ ይታገሳል። ጥላቻ ይቁም፣ ፍቅር ይቅደም ይላል።

አምርሮ ሲነሳ፣ ክብሩ ስትደፈር፣ ሀገሩ ስትነካ ግን ስለፍቅር ብሎ አይውጣ ያለውን ነፍጡን ያነሳል። በአነሳው ነፍጥ የሚወዳት ሀገሩ የኢትዮጵያን ጠላትና የሚያሳንሰውን ይቀጣበታል። ትህነግ የአማራን ርዕስቱንና ማንነቱን ነጥቆ በርስቱ እንዳይኖር፣ በየደረሰበት እንዳይከበር፣ ሠርቶ እንዳይከብር ሲያደርግ ኖሯል። ትህነግ በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ያልሰራው ግፍ የለም ይላሉ የግፉ ቀማሾች። ሺህዊችን ገድሏል፣ ሺህዎችን አስሯል፣ ሺህዎችን ከቤት ንብረታቸው አፈናቅሏል። ለምለም ነውና ምድሩን አብዝቶ ይወደዋል። ሠርተው ይከብራሉና የምድሩን ባላባቶች ደግሞ አብዝቶ ይጠላቸዋል።

የጠገዴዋ ማክሰኞ ገበያ ከተማ በትህነግ ዘመን በጨለማ ውስጥ እንድትኖር ከተፈረደባት ከተማ አንደኛዋ ናት። የከተማዋ ነዋሪዎች ዘመኑ ያዬውን መብራት ያዩ ዘንድ በተደጋጋሚ ጠይቀዋል። ጥያቄያቸው የተመለሰው ግን ከትህነግ መፈራረስ በኋላ ነው። በዚያ ዘመን በከተማዋ ከቀን ዘጠኝ ሠዓት እስከ ምሽት አምስት ሠዓት ድረስ በጄኔሬተር መብራት ይለቀቅ ነበር። ከዚያ ውጭ ባለው ጊዜ ግን መብራት ማግኜት ህልም ነው። የታፈነው ማንነታቸው የሚያንገበግባቸው የከተማዋ ነዋሪዎች በመሠረተ ልማት ሲቀጡም ቁጣቸው እያየለ ሄደ። ትህነግ ጥያቄውን መመለስ ግድ እየሆነበት መጣ። የመብራት ኃይል ማስተላለፊያ መሰሶዎችን መትከል ጀመረ። የተተከሉት መሰሶዎች መብራት ሳይተላለፍባቸው ትህነግ ራሱ ለኩሶ፣ ራሱ ተቃጥሎ ጠፋ።

ትህነግ አካባቢውን ከለቀቀ በኋላ አካባቢውን ለማስተዳደር የተቋቋመው አስተዳደር የዘመናት ጥያቄያቸውን በወራት ፈታላቸው። ለዓመታት በጨለማ የኖረችው ከተማ በወራት አበራች። የዓመታት ጥያቄያቸው በወራት መመለስ ለከተማዋ ነዋሪዎች ደስታ ፈጥሯል።

የከተማዋ ነዋሪ ተስፋሁን ሙሉ “የመብራት ኃይል መሰሶዎች ተተክለው መብራት ከዛሬ ነገ ይመጣል እየተባልን አንድም ቀን መብራት አይተን አናውቁም” ነበር ያሉት። አሁን ላይ በወራት ልዩነት መብራት አግኝተናልም፣ ከጨለማም ተላቀናል ብለዋል። መብራት ከመጣላቸው ወዲህ ሕይወታቸውን በደስታ እየመሩ መሆናቸውንም ተናግረዋል። ከመብራት በፊት ማንነት ይጠይቁ እንደነበር የተናገሩት ተስፋሁን ለየትኛውም ጥያቄያችን ምላሽ አልነበረም ብለዋል።

ሌላኛዋ የከተማዋ ነዋሪ አበበች አደራጀው መብራት ይመጠላችኋል እየተባልን ሳናዬው ነበር የኖርነው ነው ያሉት። ሕይወታችን በጥቅሉ የተመቸ አልነበረም፣ አሁን ፀሐይ የወጣ ይመስላል፣ መልካም ተስፋም አይተናል ብለዋል።

በወልቃይት ጠገዴ ሲቲት ሑመራ ዞን የጠገዴ ወረዳ ጊዜያዊ አስተዳደር ጊዜያዊ አስተዳዳሪ ዋኘው ደሳለኝ አካባቢው ነፃ እንደወጣ ከተማዋ መብራት እንድታገኝ ጥያቄ ማቅረባቸውን ነው የተናገሩት። በቀረበው ጥያቄ መሠረትም በወራት ልዩነት ከቅራቅር መብራት በመሳብ ጥያቄውን መመለስ መቻሉን ነው የተናገሩት። አሁን ላይ ከተማዋን የ24 ሠዓት የመብራት ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን የተናገሩት አስተዳደሪው የከተማዋ ነዋሪዎች ደስተኞች መሆናቸውን እና ወጪ መቀነስ መቻሉን ተናግረዋል።

እስካሁን ባለው ሂደት የመብራት አገልግሎቱ ጥሩ መሆንም ተናግረዋል። በከተማዋ ቆጣሪ ያልደረሳቸው ነዋሪዎች መኖርና የማስፋፊያ ሥራዎች ገና አለመሰራታቸው ክፍተት መሆኑንም ነግረውናል። ክፍተቶቹ እንዲሞሉ ጥያቄ አቅርበው በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውንም ተናግረዋል። የቆጣሪ ከፍለው ቆጣሪ ያልመጣላቸውን ሰዎች በመለዬት እንዲመጣላቸው መላኩንም አስታውቀዋል።

ዘጋቢ:-ታርቆ ክንዴ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡

Source link

Related posts

‹‹የዓድዋ ድል በሰዎች መካከል ያለውን ልዩነት ደርምሶ ሰው ለሕግ እንዲገዛ ያደረገ ተገዳዳሪ የሌለው የድል ቀን ነው፡፡›› አቶ አብርሃም አለኸኝ

admin

ቀጣዩ የአሜሪካ አምባሳደር የኢትዮጵያና አሜሪካን ግንኙነት ለማጠናከር ይበልጥ መሥራት ይኖርበታል-አምባሳደር  ራይነር

admin

ፖለቲከኞች ከአድዋ ድል ሊማሩ ይገባል –  የፖለቲካ ሳይንስና አለም አቀፍ ግንኙነት ምሁራን

admin