73.2 F
Washington DC
June 14, 2021
Satenaw Ethiopian News/Breaking News
Amharic News

“ለሌላው መኖር ለምን ተሳነን” | አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን

“ለሌላው መኖር ለምን ተሳነን”

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 03/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ተዘዋዋሪ ብድር የወሰዱ ወጣቶች ሌሎችም የእነሱን ዕድል እንዲያገኙ በማሰብ በወቅቱ መመለስ እንደሚገባቸው የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ቴክኒክና ሙያ ኢንተርፕራይዞች ልማት መምሪያ ገልጿል፡፡

ተዘዋዋሪ ብድር ወጣቶች ሠርተው እንዲጠቀሙና በወቅቱ እንዲመልሱ በማስብ ለሥራ ዕድል ፈጠራ በመንግሥት ከተመደበው ተቀንሶ የሚሰጥ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ብድሩን የወሰዱ አንዳንድ ወጣቶች በአግባቡ ሠርተው በወቅቱ በመመለስ ላይ ይገኛሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ በወቅቱ መክፈል ተስኗቸው የሌሎችን ሥራ የመፍጠር ዕድል እየዘጉ ነው፡፡

በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ለወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ 194 ሚሊዮን ብር ተዘዋዋሪ ብድር ተሰጥቶ ወጣቶች በተለያዩ የሥራ መስኮች ተሰማርተው ይገኛሉ፡፡ ለሥራ ዕድል ፈጠራ ከተሰጠው 194 ሚሊዮን ብር 97 በመቶ ካልተመለሰ ለሌሎች ወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ ማዋል አይቻልም፡፡

ከዚህ መመሪያ ጋር ተያይዞ ቀድመው ብድር የወሰዱ ወጣቶች ቶሎ ሠርተው ያለመመለስ ችግር፣ የተሰጠው ብድር መንግሥት በነፃ እንደሰጣቸው አድርገው የመመልከትና ያለመመለስ አዝማሚያዎች በአንዳንድ ወጣቶች ሲንፀባረቅ ተስተውሏል፡፡

በብሔረሰብ አሥተዳደሩ በየዓመቱ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የሚመረቁ በርካታ ወጣቶች በገንዘብ እጥረት ከሥራ ውጪ ሲሆኑ ይታያል፡፡ “ተዘዋዋሪ ብድር ይሰጣችኋል” በማለት የተለያዩ የሙያ ሥልጠና የወሰዱ ወጣቶችም ያሰቡት ስላልተሳካላቸው ጊዜአቸውን በአላስፈላጊ ሁኔታ እንዲያባክኑ አስገድዷቸዋል፡፡

ወጣት ዓለምቀረ አለሙና ጓደኞቹ በዳንግላ ወረዳ መንግሥት ያመቻቸላቸውን ተዘዋዋሪ ብድር ወስደው በብሎኬት ማምረት ሥራ ተሰማርተዋል፡፡ በሥራቸው ግን ውጤታማ መሆን አለመቻላቸውን ተናግረዋል፡፡ ለኪሳራ የዳረጋቸው ዋነኛው ጉዳይም ጥናት ሳይደረግበት ወደ ሥራ መግባታቸውን ጠቅሰዋል፡፡ በተሰማሩበት የሥራ ዘርፍም የሥራ መሥሪያ ጥሬ ዕቃ እጥረት እንዳጋጠማቸውም ተናግረዋል፡፡

ሥራ ከጀመሩ በኋላም ሥራ የጀመሩበት አካባቢ ውኃ የሌለው መሆኑ ለብሎኬት ማምረት ሥራ አመቺ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡ ተደራጅተው ወደ ሥራ ከገቡ ወጣቶች መካከል ሥራውን ጥለው የወጡ እንዳሉም አንስተዋል፡፡ ይህ በመሆኑም የተበደሩትን ገንዘብ በተያዘለት ጊዜ መመለስ እንዳልቻሉ ተናግረዋል፡፡ ያም ሆኖ የመንግሥት ዕዳ ይዞ መኖር ሥለማይቻል በአሁኑ ወቅት የጉልበት ሥራ በመሥራት በየሦስት ወሩ 18 ሺህ ብር ብድር እየመለሱ እንደሆነ ነግረውናል፡፡

ጌትነት ታያቸው በዳንግላ ወረዳ በማድለብ ሥራ ለመሠማራት ከወረዳው ቴክኒክና ሙያ ልማት ኢንተርፕራይዝ ጽሕፈት ቤት ስልጠና ከወሰዱ ወጣቶች መካከል አንዱ ነው፡፡ ሥራ ለመግባት ተደራጅተው መጠባበቅ ከጀመሩም ሁለት ዓመታት ማለፉን ተናግሯል፡፡ ይህ በመሆኑ ተስፋ በመቁረጥና ቤተሰቦቻቸዉን በማስቸገር በ160 ሺህ ብር ባጃጅ ገዝቶ ወደ ሌላ ሥራ መሰማራቱን ገልጾልናል፡፡ ይህም ቀድመው ብድር የወሰዱ ወጣቶች በወቅቱ ያለመመለስ ችግር ነው ብሏል፡፡

የዳንግላ ወረዳ ዋና አሥተዳዳሪ ወይዘሮ ንፁሕ ሽፈራው በወረዳው ለወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ ልዩ ትኩረት ከተሰጣቸው ዘርፎች አንዱ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በዘርፉ ግን የመሥሪያ ቦታ ችግርና የተሰጠው ብድር 97 በመቶ ሳይመለስ ሌላ ብድር መስጠት ባለመቻሉ በሚፈለገው ልክ የሥራ ዕድል ለመፍጠር እንቅፋት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ከዚህ በፊት በነበረው ብድር አሰጣጥ ላይ ሠርተው ራሳቸውን ሊቀይሩ የሚችሉ ወጣቶችን የመመልመል ችግር ለዚህ ድርጊት መዳረጉን ጠቁመዋል፡፡

ተዘዋዋሪ ብድር የወሰዱ ወጣቶች “ሰርቼ እለወጣለሁ” ከሚል አስተሳሰብ ይልቅ ሌሎች የሥራ አማራጮችን ሲያገኙ ሥራውን አቋርጠው ወደ ሌላ ሥራ መዞርና የመበታተን አዝማሚያም እንዳለም ተናግረዋል፡፡

በወረዳው የሚገኙ አራት ኢንተፕራይዞች ግን በበቂ የሥራ ቁሳቁስ እጥረት ምክንያት የሚፈልጉትን ሥራ መሥራት አንዳልቻሉ ወይዘሮ ንፁህ ገልጸዋል፡፡ ለሥራ መሥሪያ የተገዛ የጠጠር መፍጫ ማሽን (ክሬሸር) ለመሸጥ ጨረታ እንደወጣም ተናግረዋል፡፡ ማሽኑ ሲሸጥም የተሰጠውን ተዘዋዋሪ ብድር 97 በመቶ መሙላት እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡ በዚህ ዓመት ለ5 ሺህ 300 ወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ እስከ አሁን ለ3 ሺህ 300 ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉን ተናግረዋል፡፡

የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ቴክኒክና ሙያ ኢንተርፕራይዞች ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ነጋ መከት በዞኑ በግብርና፣ በእንስሳት ሀብት፣ በኮንስትራክሽን፣ በማንፋክቸሪንግ፣ በአግልግሎት ዘርፍ፣ በፕሮጀክቶች ሥራ እና በሌሎች የሥራ ዘርፎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡ እስከ መጋቢት 30/2013 የበጀት ዓመት ለ70 ሺህ 26 ወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ ለ43 ሺህ 667 ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠር እንደተቻለ ተናግረዋል፡፡ አፈጻጸሙም 62 ነጥብ 4 በመቶ መሆኑን ነው ያስረዱት፡፡

ከዚህ በፊት የተሰጠው 194 ሚሊዮን ተዘዋዋሪ ፈንድ ሙሉ በሙሉ ያለመመለሱ ደግሞ ዞኑ በሚፈልገው ልክ የሥራ ዕድል እንዳይፈጥር ማድረጉን ተናግረዋል፡፡ ወጣቶች የወሰዱትን ቶሎ የመመለስ ችግር እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡

በአመለካከት ላይ ብዙ ሥራ ሳይሠራ ብድር መስጠት ተገቢ አለመሆኑንም አስረድተዋል፡፡ “ወጣቶች ብድሩን መንግሥት በነጻ እንደሰጣቸው አድርጎ የመመልከት፤ ድርሻችን ነው የማለት፤ አቅም ፈጥረው መመለስ እየቻሉም የማጓተት ችግር እንዳለባቸው በግልፅ ታይቷል” ብለዋል፡፡ ተዘዋዋሪ ብድርን የወሰዱ ወጣቶች “ለሌላው መኖርን” በማሰብ በወቅቱ መመለስ እንደሚገባቸው ኃላፊው አሳስበዋል፡፡ ብድሩን በወቅቱ የማይመልሱ ወጣቶችን በተመለከተ ጉዳዩን ወደ ሕግ ለማቅረብ የዞኑ የሥራ ዕድል ፈጠራ ግብረ ኀይል በቅርቡ ውይይት ማድረጉን ተናግረዋል፡፡

ዘጋቢ፡- አዳሙ ሽባባው

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡

Source link

Related posts

በምርጫ ወቅት ፓርቲዎች ሊያከብሯቸው የሚገቡ የሰብአዊ መብት አጀንዳዎች ይፋ ሆኑ

admin

በካናዳ ለህዳሴ ግድብ ግንባታ ከ140 ሺህ የካናዳ ዶላር በላይ ተሰበሰበ

admin

ድምጻችን ለነጻነታችን” በሚል መሪ ቃል በተለያዩ አካባቢዎች ሰልፍ ተካሄደ

admin