82.62 F
Washington DC
June 21, 2021
Satenaw Ethiopian News/Breaking News
Amharic News

ለሁለንተናዊ ዕድገት አስተዋፅዖ ለሚያበረክት ባለ ሀብት መሠረተ ልማት ሊሟላለት እንደሚገባ የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት አሳሰበ፡፡

ለሁለንተናዊ ዕድገት አስተዋፅዖ ለሚያበረክት ባለ ሀብት መሠረተ ልማት ሊሟላለት እንደሚገባ የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት አሳሰበ፡፡

ባሕር ዳር፡ መጋቢት 17/2013 ዓ.ም (አብመድ) የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት የኢኮኖሚ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በከተማዋ በመዘዋወር የተለያዩ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ሁኔታ ተመልክቷል። የቋሚ ኮሚቴው መዳረሻ መካከል አንዱ የሽመላ ሎጅ ነበር፡፡

በከተማው በርካታ ባለሀብቶች መዋዕል ንዋያቸውን አፍስሰው ወደ ሥራ ቢገቡም ለፕሮጀክታቸው የተለያዩ መሠረተ ልማት ባለመሟላታቸው ለኪሳራ የተጋለጡ አሉ። ኪሳራ ካጋጠማቸው ፕሮጀክቶች ውስጥ ሽመላ ሎጅ አንዱ ነው፡፡

ሽመላ ሎጅ ከተመሠረተ ዓመታትን አስቆጥሯል። ሎጅው በተለይ ለተሽከርካሪም ሆነ ለእግረኛ አመቺ የሆነ መንገድ ባለመኖሩ ችግር ውስጥ ገብቷል። በርካታ ደንበኞች ወደ መዝናኛው ለማቅናት ቢፈልጉም የመንገድ ምቾት ስለሌለው እንደሚቀሩ የሎጅው ባለቤት አቶ ሙላት ባሳዝነው ተናግረዋል።

“ሽመላ ሎጅን ለመመሥረት 30 ሚሊዮን ብር ወጪ አድርገንበታል። ለዓመታት ለከተማ አስተዳደሩ ብናሳዉቅም መንገዱን ለመገንባት ወሰኑ እንጂ ተግባራዊ ሊያደርጉት አልቻሉም። ሎጅው ለ57 ዜጎች የሥራ ዕድል ፈጥሯል፤ ነገር ግን እነዚህን ሠራተኞች ልናስቀጥል ቀርቶ ፕሮጀክቱን ልንዘጋው ተቃርበናል” ብለዋል።

ባለሃብቶች ለከተማዋ እድገት እስከሠሩ ድረስ እንዲሁም የሚጠበቅባቸውን ግብር እስከከፈሉ ድረስ መሠረተ ልማት ሊሟላላቸው ይገባል ነው ያሉት።

የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር የመንገድ ባለሥልጣን ጽሕፈት ቤት ምክትል ሥራ አስኪያጅ አብቧል ሙላት ለባለ ሀብቶች የመንገድ ግንባታ ለማከናወን የመሳሪያ አቅርቦት እንዳልነበራቸው ተናግረዋል፡፡ አሁን ግን ጽሕፈት ቤታቸው 16 የግንባታ መሳሪያዎች(ማሽኖች) በመግዛት ባለሀብቶች ከመጠየቃቸው በፊት የመንገድ ግንባታ እያከናወኑ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ ሆኖም ግን በከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ የግንባታ ግብዓት ችግር ስላጋጠማቸው ግንባታ ለማጠናቀቅ አስቸጋሪ እንደሆነባቸው ገልጸዋል፡፡

የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ምክርቤት የኢኮኖሚ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ስማቸው ንጋቱ በሰጡት አስተያየት “ባለ ሀብቱን ለመሳብ ሁሉንም መሠረተ ልማት እናሟላለን ብለን ቃል እንገባለን፡፡ ሀብት ንብረቱን ይዞ ከመጣ በኋላ ግን የሚጠይቀውን አይሟላለትም፡፡ ለምሳሌ ሽመላ ሎጅ 30 ሚሊዮን ብር ወጪ በማድረግ ከተመሠረተ ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ ግን የመንገድ ችግሩን መፍታት አልተቻለም” ብለዋል፡፡

ለከተማዋ ሁለንተናዊ ዕድገት አስተዋፅዖ ለሚያበረክቱ ባለ ሀብቶች መሠረተ ልማት ሊሟላ ይገባል ያሉት አቶ ስማቸው በከተማ አስተዳደሩ የሚገኙ የሚመለከታቸው ተቋማትም የሚስተዋሉ ችግሮችን መቅረፍ እንደሚገባቸው ተናግረዋል፡፡ ምክር ቤቱም በዘርፉ ያሉ ጉዳዮችን ቀጣይነት ባለው መልኩ ክትትል እንደሚያርግም ጠቁመዋል፡፡

“ቢያንስ በትንሽ ጉልበትና ወጪ ሊቀረፉ የሚችሉ ችግሮች በባለ ሀብቱ ላይ እንግልት ሊያደርሱ አይገባም” ብለዋል፡፡

የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት የኢኮኖሚ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባደረገው የመስክ ምልከታም ባለሀብቶች የተሟላ የመሠረተ ልማት አገልግሎት እንዲያገኙም አቅጣጫ አስቀምጧል።

ዘጋቢ፡- ብሩክ ተሾመ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡

Source link

Related posts

አቶ ደመቀ መኮንን አሁን ያለውን የኮቪድ 19 ስርጭት ለመግታት ሁሉን አቀፍ ምላሽ ማጠናከር አስፈላጊ መሆኑን ገለፁ

admin

ብሔራዊ የአየር ጠባይ አገልግሎት ማዕቀፍ ስምምነት ተፈረመ

admin

“የራሴ ጥረት፣ የመምህራንና የወላጆቸ ድጋፍ ውጤታማ አድርጎኛል” በእንጅባራ ዩኒቨርስቲ የከፍተኛ ማዕረግ ተመራቂ

admin