51.91 F
Washington DC
May 12, 2021
Satenaw Ethiopian News/Breaking News
Amharic News

ለሀገር አንድነትና ሉዓላዊነት ቅድሚያ በመስጠት ለስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን ተወዳዳሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተናገሩ፡፡

ለሀገር አንድነትና ሉዓላዊነት ቅድሚያ በመስጠት ለስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን ተወዳዳሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተናገሩ፡፡

ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 03/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ባለፉት አምስት ተከታታይ ሀገራዊ ምርጫዎች ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደ ልባቸው ተንቀሳቅሰው የምረጡኝ ቅስቀሳ ለማካሄድ ምቹ ሁኔታ እንዳልነበር አሚኮ ያነጋገራቸው ተወዳዳሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተናግረዋል፡፡ ዕጩ ተወዳዳሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችም የራሳቸው የሆነ ውስንነት እንደነበረባቸው ነው የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ያስረዱት፡፡

የእናት ፓርቲ የምክር ቤት አባል ታመነ ሀብቱ (ዶክተር) በኢትዮጵያ ባለፉት አምስት ሀገራዊ ምርጫዎች ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተገቢ ሚናቸውን እንዳይወጡ ሕጋዊ ሰውነት የተሰጠው ምርጫ ቦርድ ከገዢው ፓርቲ ነፃ በመሆን ፍትሐዊ አገልግሎት መስጠት አለመቻሉን አስታውሰዋል፡፡

የምርጫ ቦርድ አደረጃጀት ለስድሰተኛው ሀገራዊ ምርጫ ከዚህ በፊት ከነበረው የተሻለ ገለልተኛ መሆኑን ዶክተር ታመነ ተናግረዋል፡፡

ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ኃላፊነታቸውን በብቃት እንዲወጡ ምርጫ ቦርድ ለሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች በታማኝነት አገልግሎት መስጠት እንዳለበት ዶክተር ታመነ ጠይቀዋል፡፡ የሲቪል ማኅበራት ከፖለቲካ ወገኝተኝነት ገለልተኛ መሆን እንዳለባቸው ነው ዶክተሩ የገለጹት፡፡

ኢትዮጵያ ለምታካሂደው ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ይዘውት የቀረቡትን ፕሮግራም ለሕዝቡ በማስተዋወቅ በምርጫው በንቃት መሳተፍ ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት፡፡ በተለይም ውስጣዊ አንድነትን ያለማጠናከር፣ ዕጩ ተወዳዳሪዎችም ምርጫውን ሲያሸንፉ የሕዝብ አገልጋይ ከመሆን ይልቅ የሥልጣን ፍላጎትን አንግቦ የመነሳት እና መሰል ድክመቶች ይታዩባቸው እንደነበር ተናግረዋል፡፡

“በፉክክር ውስጥ ማሸነፍና መሸነፍ ያለ ነው” ያሉት ዶክተር ታመነ ለኢትዮጵያ የሚበጃት ሠላማዊ ምርጫ ማካሄድ ነው ብለዋል፡፡ ለዚህም ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች በመወያየት ጠንካራ የአደረጃጀት መዋቅር መፍጠር እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡ ዕጩ ተፎካካሪዎች የሚያቀርቧቸው ፕሮግራሞች ለይስሙላ ሳይሆን የኢትዮጵያ ሕዝቦችን ለመጥቀም መሆን እንዳለባቸውም ተናግረዋል፡፡

“ባለፉት አምስት ሀገራዊ ምርጫዎች ጠንካራ የፖሊሲ ክርክር አልተደረገም” የሚሉት ዶክተሩ በዚህ ዓመት ለሚካሄደው ምርጫ ደግሞ አብዛኞቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጠንካራ የምርጫ ቅስቀሳ ፕሮግራም ይዘው እየቀረቡ ናቸው ብለዋል፡፡ ይህ ደግሞ በባለፉት ጊዜያት ከተካሄዱ ምርጫዎች የተለየ ያደርገዋል ነው ያሉት፡፡ ዕጩ ተወዳዳሪዎች ለሕዝቡ የሚያስተዋውቋቸው ፖሊሲዎች ወደ ሕዝቡ ከመቅረባቸው በፊት የፖሊሲ አማራጮችን ከምሁራን ጋር መወያየትና መታረም ያለባቸው ጉዳዮችን ማስተካከል ይገባቸዋል ብለዋል፡፡

ምርጫው በሠላም እንዲጠናቀቅ ፓርቲዎች ለሠላም ዘብ መቆም አለባቸው ያሉት ዶክተር ታመነ የጥላቻ ንግግሮች አላስፈላጊ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ “የእናት ፓርቲ ደጋፊዎች ምርጫውን በዴሞክራሲያዊ መንገድ ለማካሄድ መንገዱ እንኳን ቢጠባቸው በፓርቲው ምክንያት አንድም ደም መፍሰስ የለበትም” የሚል አቋም በመያዝ እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኙ ዶክተር ታመነ ተናግረዋል፡፡

የአማራ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ንቅናቄ (አዴኃን) ሊቀመንበር አቶ ተስፋሁን ዓለምነህ ባለፉት ጊዜያት በተካሄዱት አምስት ተከታታይ ምርጫዎች የ1997 ዓ.ም እንደ አብነት የሚጠቀስ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ እሱም ውጤታማ መሆን ያልቻለው በፖለቲካ ፓርቲዎች ጠንካራ ቅንጅታዊ አሠራር ባለመፈጠሩ ነው ብለዋል፡፡ ባለፉት ዓመታት አምስት ጊዜ በተካሄዱ ምርጫዎች የተሳተፉት ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የፖሊሲ አማራጮችን ከማቅረብ ይልቅ የፓርቲን ድክመት በመተችት ብዙ ጊዜያትን የማሳለፍ አዝማሚያ እንደታየባቸው አስታውሰዋል፡፡

ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ተዓማኒና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ማኅበረሰቡና መንግሥት የበኩላቸውን ኃላፊነት መወጣት እንደሚገባቸውም ገልጸዋል፡፡

“በምርጫ አሸናፊም ተሸናፊም ይኖራል” ያሉት አቶ ተስፋሁን አሸናፊ መሆን ያለበት ግን ዴሞክራሲ ነው ብለዋል፡፡ በዴሞክራሲ ሥርዓትም ለፖለቲካ ፓርቲዎች እኩል የሆነ መደላድል ሊኖር እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ ዕጩ ተወዳዳሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ለሀገር አንድነትና ሉዓላዊነት ቅድሚያ በመስጠት ለምርጫ መዘጋጀት እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡

ምርጫ ዴሞክራሲን በመጠቀም የሥልጣን ባለቤት የሚሆንበት አሠራር መሆኑን ነው አቶ ተስፋሁን የገለጹት፡፡ ፓርቲዎችም በምርጫ ፍላጎት ውስጥ ዜጎች ወደ ግጭት እንዳይገቡ የማስገንዘብ ሥራ መሥራት አለባቸው ብለዋል፡፡ ፓርቲያቸውም ይህን በመሥራት ላይ እንደሚገኝ አቶ ተስፋሁን አስረድተዋል፡፡

ዘጋቢ፡- አዳሙ ሽባባው

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡

Source link

Related posts

መንግስት በምርጫ ሂደቱ ሊከሰቱ የሚችሉ የጸጥታ ችግሮችን በመለየት እርምጃ እየወሰደ መሆኑ ተገለፀ

admin

የዩናይትድ ኪንግደም አስመጪዎች በኢትዮጵያ የቡና ኢንቨስትመንት ላይ እንዲሰማሩ ጥሪ ቀረበ፡፡

admin

አትሌት ሰምበሬ ተፈሪ በድሬዳዋ በተካሄደው 14ኛው የኢትዮጵያ ግማሽ ማራቶን ውድድር አሸነፈች

admin