51.91 F
Washington DC
May 12, 2021
Satenaw Ethiopian News/Breaking News
Amharic News

“ሁለተኛው የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ ደብተር መሰጠት በአርሶ አደሮች መካከል ሊነሳ የሚችለውን የወሰን ግጭት በማስቀረት ልማትን ያፋጥናል” የአማራ ክልል ገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ቢሮ

“ሁለተኛው የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ ደብተር መሰጠት በአርሶ አደሮች መካከል ሊነሳ የሚችለውን የወሰን ግጭት በማስቀረት ልማትን ያፋጥናል” የአማራ ክልል ገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ቢሮ

ባሕር ዳር፡ ጥር 13/2013 ዓ.ም (አብመድ) የአማራ ክልል ገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ቢሮና የጀርመን ተራድኦ ድርጅት (ጂአይዜድ) አርሶ አደሩ መሬቱን በሚጠቀምበት ሁኔታ ላይ በባሕር ዳር ከተማ እየመከሩ ነው።

ወይዘሮ መሠረት አስቻለ በሰከላ ወረዳ የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ጽሕፈት ቤት ቀያሽ ባለሙያ ናቸው። በፊት የነበረው የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ ደብተር ችግር እንደነበረበት አስታውሰው ሁለተኛው የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ ግን ከወሰን ጋር ያለዉን ጠቅላላ ችግር እንደሚቀርፍ አስረድተዋል።

አቶ ዮሐንስን ጌታሁን በደብረ ኤልያስ ወረዳ የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ጽሕፈት ቤት የኢንቨስትመንት ባለሙያ ናቸው። በሁለተኛው የይዞታ ማረጋገጫ ደብተር የሚደረገው የቅየሳ ሥራ ባለ ሀብቱ ፍትሀዊ የሆነ አሠራር እንዲያከናውን ያደርጋል፤ ድሃ አርሶ አደር ሳይበዘበዝ የመሬቱ ተጠቃሚ እንዲሆን ያስችላል ብለዋል።

የአማራ ክልል ገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ቢሮ ከተለያዩ ግብረሰናይ ድርጅቶች ጋር በጋራ በመሥራት በክልሉ ለሚገኙ አርሶ አደሮች የሁለተኛ የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ ደብተር እየሰጠ ነው። የመጀመሪያው የይዞታ ማረጋገጫ ደብተር የአርሶ አደሩን የመሬት ወሰን በትክክል ሊያስቀምጥ ባለመቻሉ አርሶ አደሮች ጊዜያቸውን ለልማት ከማዋል ይልቅ በግጭትና ክስ በማሳለፋቸው ክልሉን ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት መሰናክል እንደነበሩ የአማራ ክልል ገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ቢሮ ምክትል ኀላፊ አቶ መለሠ ዳምጤ ተናግረዋል።

ሁለተኛው የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ ደብተር ግን በአርሶ አደሩ መካከል ሊነሳ የሚችለውን የወሰን ግጭት ምክንያት በማስቀረት አርሶ አደሮች ሙሉ አቅማቸውን በመጠቀም ፊታቸዉን ለልማት እንዲያዞሩ ያስችላል ነው ያሉት ምትክል ኀላፊው። አርሶ አደሮች መሬታቸውን በውል አውቀው የልማት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ቢሮው ከበርካታ ግብረሰናይ ድርጅቶች ጋር ሲሠራ የቆየ መሆኑን ያስረዱት አቶ መለሠ አሁን ደግሞ የጀርመን ተራድኦ ድርጅት ሥራቸውን የበለጠ ለማሳለጥ እንደሚረዳቸው ጠቁመዋል።

ድርጅቱ ለአርሶ አደሩ የመሬት ማረጋገጫ ቅየሳ እንዲረጋገጥ ካስቻለ በኋላ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስችል ሥልጠና፣ የግብአት አቅርቦት፣ የገበያ ትስስርን በመፍጠር አርሶ አደሮች የግብርና ሥራቸውን እንዲያዘምኑ እገዛ ያደርጋል ብለዋል።

በክልሉ ከሚገኙ 4 ሚሊዮን ባለይዞታዎች 1 ነጥብ 8 ሚሊዮን አባ ወራዎችና እማ ወራዎች ሁለተኛው የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ ተሰጥቷል ብለዋል። በሚቀጥሉት 3 ዓመታት ሁሉንም የክልሉ አርሶ አደሮች የሁለተኛዉ የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ ባለቤት ለማድረግ እየሠሩ እንደሆ አቶ መለሠ አስገንዝበዋል።

ምክትል ኀላፊው ባደረጉት ገለፃ ባለሀብቶችም ምርታቸውን ወደ አንድ ቦታ እንዲያሰባስቡና የምርታቸው ተጠቃሚ እንዲሆኑ ድርጅቱ እገዛ ያደርጋል። የጀርመን ተራድኦ ድርጅት የግብርና ኢቨስትምንትና የመሬት አስተዳደር ድጋፍ ማድረግ፣ የመንግሥትን መዋቅርና አሠራሮች እንዲሻሻሉ፣ የመሬት አስተዳደሩ ፖሊሲ እንዲሻሻል በጥናት የተደገፈ ምክረ ሀሳብ ለመንግሥት በማቅረብ የሕዝቡን የመሬት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንደሚሠራ ከድርጅቱ ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል።

ድርጅቱ በደብረ ኤልያስና፣ ሰከላና ወንበርማ ወረዳዎች የትግበራ ሥራዉን እንደሚጀምር ተጠቁሟል። ድርጅቱ በአማራ ክልል በመሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ዙሪያ ለመሥራት እ.ኤ.አ ከ2019 ጀምሮ የቅድመ ዝግጅት ሥራ ሲሠራ የቆየ ሲሆን በ2021 ደግሞ ወደ ትግበራ ሥራ ለመግባት ማቀዱን በውይይቱ ተገልጿል።

የጀርመን ተራድኦ ድርጅት 3 ነጥብ 9 ሚሊየን ብር ወጪ በማድረግ ለቅየሳ አገልግሎት የሚውሉ መሣሪያዎችንም ለአማራ ክልል ገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ቢሮ አስረክቧል።

ዘጋቢ:- ቡሩክ ተሾመ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡

Source link

Related posts

የድሮን ቴክኖሎጂን በትብብር በማልማት ለልዩ ልዩ አገልግሎቶች መጠቀም የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ

admin

ኢትዮጵያና ጃፓን የሀገራቱን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት በሚያጠናክሩ ጉዳዮች ዙሪያ መከሩ

admin

የብልጽግና ፓርቲ የሴቶች ሊግ ፕሬዚዳንት ወይዘሮ መሰረት መስቀሌ በሴቶች እየተሰሩ ያሉ ሥራዎች አመርቂ መሆናቸውን ገለጹ

admin