48.63 F
Washington DC
February 27, 2021
Satenaw Ethiopian News/Breaking News
Amharic News

“ሁለተኛዋ የመሬት ምልከታ ሳተላይት የሙከራ ሥራዎችን በተሳካ ሁኔታ እያከናወነች ነው” የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት

“ሁለተኛዋ የመሬት ምልከታ ሳተላይት የሙከራ ሥራዎችን በተሳካ ሁኔታ እያከናወነች ነው” የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት

ባሕር ዳር ፡ የካቲት 12/2013 ዓ.ም (አብመድ) ኢትዮጵያ ባለፈው ታኅሣሥ ወር ወደ ሕዋ የላከቻት ሁለተኛዋ የመሬት ምልከታ ሳተላይት (ET-SMART-RSS) የሙከራ ሥራዎችን በተሳካ ሁኔታ እያከናወነች መሆኑን የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ይሹሩን ዓለማየሁ በተለይ ለኢቢሲ እንደገለጹት ሳተላይቷ ደህንነቷን እና ወደ ሕዋ የተላከችበትን ዓላማዋን በተመለከተ የላከቻቸው የሙከራ መረጃዎች አመርቂ ናቸው።

ሳተላይቷ ምህዋር ላይ እያለች በትክክል ስለመሥራቷ እና ደህንነቷን ለማረጋገጥ እስከ ሁለት ወር ድረስ ሙከራ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑንም ነው የገለጹት።

በዚህም ET-SMART-RSS ደኀንነቷን በተመለከተ እና ከተቋሙ የተሰጧትን ትዕዛዞች ተቀብላ ጥራት ያላቸው መረጃዎችን መላክ ችላለች።

የሙከራ ሥራው ሲጠናቀቅ ሳተላይቷ ወደ መደበኛው መረጃ (ዳታ) የመስጠት ሥራ እንደምትገባ እና መረጃዎቹን የመጠቀም ሂደት እንደሚጀመርም ነው የተናገሩት።

ET-SMART-RSS ሳተላይት ወደ ሕዋ የተላከችበት ዓላማ የመሬት ምልከታ መሆኑን እና ከዚህም አንፃር በሙከራ ጊዜው ወቅት ኢንስቲትዩቱ በሚሰጣት አቅጣጫ መሠረት የሚፈለገውን መረጃ እየሰጠች እንደሆነም ዶክተር ይሹሩን ገልጸዋል።

ኢንስቲትዩቱ በአሁኑ ሰዓት የመሬት ምልከታ ሳተላይት ላይ ትኩረት አድርጎ እየሠራ የሚገኘው በአየር ፀባይ ለውጥ ምክንያት ድርቅ በተደጋጋሚ እያስቸገረ በመሆኑ ይህንኑ ለመቅረፍ እና ግብርናን ለማዘመን ተፈልጎ እንደሆነ አብራርተዋል።

ኢንስቲትዩቱ የET-SMART-RSS መረጃዎችን ከመጀመሪያዋ ETRSS-1 ሳተላይት ጋር በማጣመር እየተጠቀመ መሆኑን የገለጹት ዶክተር ይሹሩን፣ ከዚህ አንፃር መረጃ የመቀበል አቅምን ማሳደግ አስፈላጊ በመሆኑ በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑንም ገልጸዋል።

ከሳተላይቶቹ የሚመጡ መረጃዎችን መቀበል ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያውያን ሙያተኞች የመተንተን እና ለተጠቃሚ የማቅረብ አቅም ለማሳደግም እየተሠራ ነው ብለዋል።

የመጀመሪያዋን ETRSS-1 እና ሁለተኛዋን ET-SMART-RSS ወደ ሕዋ ለማምጠቅ 9 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር ወጪ መደረጉን ኢንስቲትዩቱ አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የኮሙዩኒኬሽን እና ብሮድካስቲግን ሳተላይትን ጨምሮ በሚቀጥሉት 10 ዓመታት ውስጥ ሦስት ሳተላይቶችን ወደ ሕዋ ለመላክ በመስራት ላይ እንደሚገኝ የዘገበው ኢብኮ ነው።

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡

Source link

Related posts

የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አደም ፋራህ ከቱርክ አምባሳደር ጋር ተወያዩ

admin

የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ጋር ተወያዩ

admin

“ከሱዳን ጋር ግጭት እንዲኖረን አድርገው የራሳቸውን ዓላማ ለማሳካት የሚፈልጉ ኀይሎች ገብተዋል” የኢፌዴሪ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል ዐቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ

admin