71.98 F
Washington DC
May 17, 2021
Satenaw Ethiopian News/Breaking News
Amharic News

ሀገራቸውን በዓለም አደባባይ ከፍ ያደረጉ የኢትዮጵያውያን ባለዉለታው፣ የኮሪያው ዘማች አርበኛ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ፡፡

ሀገራቸውን በዓለም አደባባይ ከፍ ያደረጉ የኢትዮጵያውያን ባለዉለታው፣ የኮሪያው ዘማች አርበኛ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ፡፡

ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 21/2013 ዓ.ም (አሚኮ) አባቶቻችን የሀገራችንን ዳር ድንበር ከማስከበር ባሻገር ባሕርን በመሻገር ሀገራቸው የሰጠቻቸዉን ተልዕኮ ሲወጡ ቆይተዋል፡፡ ባሕር ማዶ በመሻገርም ወደ ኮንጎና ኮሪያ በመዝመት ሀገራቸው ሰላምን ከማስከበር አንፃር ያላትን ስም እና ዝና ከፍ አድርገዋል፡፡

የዓለም የሰላም አምባሳደር በኩረ ምዕመናን አራጋው መሰሉ በ1919 ዓ.ም በጎጃም ክፍለ ሀገር በባሕር ዳር አውራጃ በይልማና ዴንሳ ወረዳ ልዩ ስሙ ታላቁ ሸባ ጊዮርጊስ ከአባታቸው ቀኝ አዝማች መሰሉ ካሳ እና ከእናታቸው ከወይዘሮ በትሀ ወንዱ ተወለዱ፡፡

በ1940 ዓ.ም የቤተ-መንግሥት ሕግ አስከባሪ የክብር ዘበኛ ሠራዊት አባል ሆነው አገልግለዋል። የሚሰጠውን አጠቃላይ የወታደራዊ ስልጠና በመውሰድ አጠናቀው የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነትን ለማስከበር ግዴታቸዉን ሲወጡ ቆይተዋል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ጉባዔ በወሰነው መሰረት ኢትዮጵያ እንደ ሌሎች ሀገራት ሕግ አስከባሪ ሠራዊት ወደ ደቡብ ኮሪያ ለመላክ በመወሰኗ ከክብር ዘበኛ ሠራዊት አባላት መካከል በታማኝነታቸው እና በቁርጠኝነታቸው ተመርጠው በቃኘው ሻለቃ ሠራዊት አባልነት መዝመታቸዉን የሕይወት ታሪካቸው ያሳያል።

የዓለም ሰላም አምባሳደር በኩረ ምዕመናን አራጋው መሰሉ በደቡብ ኮሪያም ሆነ በተለያዩ ሀገራት የተሰጣቸዉን ግዴታ በብቃት ከተወጡ በኋላም በሀገር ውስጥ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊና በባሕላዊ ዘርፎች ትልቅ ተግባር ፈፅመዉ አልፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ባለውለታ የነበሩት የሰላም አምባሳደሩ ላበረከቱት የጀግንነት ታሪክ በርካታ ሽልማቶች ተበርክቶላቸዋል፡፡ የጦር ሜዳ ሜዳሊያዎች፣ ከተባበሩት መንግሥታት የጀግንነት የወርቅ ሜዳሊያ፣ የኮሪያ መንግሥት የታላቅ የጀግንነት ክብር የወርቅ ሜዳሊያ፣ ከግርማዊ ቀዳማዊ ኀይለ ሥላሴ መንግሥት የጀግና የወርቅ ሜዳሊያ፣ በኦጋዴን ሠላም ማስከበር የግርማዊ ቀዳማዊ ኀይለ ሥላሴ የብር ሜዳሊያ፣ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በኮሪያ ላበረከቱት ሥራ የኮሪያ የወርቅ ዘንባባ ሜዳሊያና የኮንጐ ኪንሻሳ የ1952 ዓ.ም የወርቅ ሜዳሊያ ሽልማቶች ይጠቀሳሉ፡፡

የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ የነበሩት የዓለም የሠላም አምባሳደር በኩረ ምዕመናን አራጋው መሰሉ ባጋጠማቸው ጽኑ ሕመም በህክምና ሲረዱ ቆይተው ሚያዝያ 20/2013 ዓ.ም በ95 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡ የዓለም የሰላም አምባሳደር በኩረ ምዕመናን አራጋው መሰሉ የ4 ወንዶችና የ6 ሴቶች አባት ነበሩ፡፡ በሕይወት እያሉ የአሁኑ ትውልድ ሀገሩንና ድንበሩን ጠንክሮ እንዲጠብቅ በፃፉት ደብዳቤ አደራቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የዓለም የሠላም አምባሳደር በኩረ ምዕመናን አራጋው መሰሉ ቤተሰቦቻቸው፣ ወዳጅና ዘመዶቻቸው በተገኙበት ሚያዝያ 21/2013 ዓ.ም በባሕር ዳር ከተማ ሰላም አርጊው ማርያም ገዳም የቀብር ሥነ ስርዓታቸው ተፈፅሟል።

ዘጋቢ፡- ቡሩክ ተሾመ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡

Source link

Related posts

ʺጎንደር ከግንቡ ላይ ያለው ነጭ አንበጣ ከምን ሊገባ ነው አሞራው ሲመጣ”

admin

በትግራይ የተረጋጋ ህዝባዊ ሰላምና አስተዳደርን ለማረጋገጥ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር አብርሃም በላይ ጥሪ አቀረቡ

admin

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ወለጋ ብርቅዬ የማይጠገብ የፍቅርና የልማት አካባቢ መሆኑን ገለጹ

admin