78.37 F
Washington DC
June 17, 2021
Satenaw Ethiopian News/Breaking News
Amharic News

ʺጎንደር ከግንቡ ላይ ያለው ነጭ አንበጣ ከምን ሊገባ ነው አሞራው ሲመጣ”
ʺጎንደር ከግንቡ ላይ ያለው ነጭ አንበጣ
ከምን ሊገባ ነው አሞራው ሲመጣ” (በድጋሜ የቀረበ)
ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 27/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ለበቀል የተደገሰ ድግሥ፣ ለጥፋት የተዘጋጄ ንግሥ፤ በዓድዋ ተራራ ላይ
የጨለመችው የሮም ፀሐይ ዳግም የምትበራበት ዘመን ይጠበቅ ነበር፡፡ የሮምን ፀሐይ አጥፍታ ከፍ ብላ የበራችው የኢትዮጵያ
ፀሐይ ለዘላለም ላትጠፋ ከፍ ብላ እያበራች ነው፡፡ እንገረስሳለን ሲሉ የተገረሰሱት፣ እናሸንፋለን ሲሉ የተሸነፉት፣ ከፍ እንላለን ሲሉ
የተንኮታኮቱት የሮም ነገሥታት ዓለም ስቆባቸዋልና ለ40 ዓመታት አንገታቸውን አላቃኑም፡፡ ያቺ ድንቅ የሆነች ሀገር የነካትን ሁሉ
እያቃጠለች፣ የገፋትን ሁሉ እየጣለች ትሄዳለችና በግርማ የመጣውን የሮም ሠራዊት በቁዛማ መልሰዋለች፡፡
ሮማውያን ኃያላን ነን ባዮች ብሥራት ያደርሰናል ያሉት ሠራዊት ሥብራት አደረሳቸውና አንገታቸውን አስደፋው፣ ወኔያቸውን
አጠፋው፡፡ ዓለም በኢትዮጵያዊያን ተደነቀች፣ በሮማውያን ተሳለቀች፣ አያድርስ ነው ስትል ፈራችም፡፡
ʺቆስቁሰው ቆስቁሰው ያቃጠሉት ክብር፣ ብቻውን አይነድም ራሱን ሳይጨምር” እንዳለ ጃሎ ባይ ሮም በነካችው እሳት ተቃጠለች፣
እከበራለሁ ስትል ተዋረደች፣ አፈረች፡፡ የሮማውያን በዓድዋ ጦራቸው፣ በሮም አደባባይ ወኔያቸው ተንኮታኮተ፤ የድል ዜና፣
የኢትዮጵያን ሐብትና ንበረት ይዘው ሊመለሱ የነበሩት መርከቦቿ ሀዘን ተሸክመው ውቅያኖሱን እየከፈሉ ወደ ሮም ተመለሱ፡፡
ወታደሮቻቸውን የኢትዮጵያ አርበኞች ሳንጃ ወጋቸው፣ አፈሙዝ በላቸው እና በየጥሻው ወድቀው ቀሩ፡፡ በዚህ ድል ለዘመናት
የካቡት ዝና በሰዓታት ተገርስሶ እንዳልነበር የሆነባቸው ሮማውያን ለዳግም በቀል 40 ዓመታት ደግሠው፣ ለበቀል ነግሠው
የማይደፈረውን ደፈሩ፡፡ በቀል የሻተው ሠራዊት የእነ አጅሮችን ሀገር ኢትዮጵያን ረገጠ፡፡
በዘመኑ ኃያሉን ዙፋን የተረከቡት ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ባለሙሉ ሥልጣን አልጋ ወራሽ በነበሩበት ጊዜ በተለያዩ የዓለም
ሀገራት ተዘዋውረው ያዩትን ስልጣኔ በሀገራቸው ለመተግበር ደፋ ቀና እያሉ ነበር፡፡ ያሰቡትን ያሳኩ ዘንድም ፍቅር ይሻሉና
ከሀገራት ጋር በፍቅር ለመኖር ይታትራሉ፡፡ የሀገራቸው ጠላቶች ግን በዙሪያ ገባው ከበው ሊውጧቸው እያሰፈሰፉ ነበር፡፡
በፍቅርና በምክክር ይፈታል እየተባለ የሄደው ጉዳይ እያደረ እየከረረ ሄደ፡፡ ፊት ለፊት ፍቅር ከኋላ ጦር የምታዘጋጄው ጣልያን
አሰፍስፋለች፡፡ የማይቀረው የጦርነት ጊዜ ደረሰ፡፡ ጣልያን ወረራውን ለኮሰች፡፡ አትንኩን ከነካችሁን አንምራችሁም የሚሉት
ኢትዮጵያውያን ወራሪን ለመመከት ተነቃነቁ፡፡ ኢትዮጵያዊያን ከ40 ዓመታት በፊት አባቶቻቸው የሠሩት ድል ወኔ ሆኗቸዋል፡፡
እነርሱም በሌላ ድል ስማቸው እስኪጠራ ድረስ ተቻኩለዋልና ሞት ወደሚደገስበት የጦርነት ግንባር ተመሙ፡፡
በመረባ የገባው የጣልያን ወታደር እየገፋ መጣ፡፡ ኢትዮጵያውያን ክንደቸውን ዘረጉ፡፡ አርባ ዓመታትን ከተዘጋጀው ወታደር ጋር
መተናነቅ ጀመሩ፡፡ እንደ ዓድዋ ሁሉ በአንድ ጀንበር ድል የሚገኝ አልነበረም፡፡ የአርበኝነቱ ሥራ ተቀጣጠለ፡፡ ጀግኖች አርበኞች ʺኧረ
ጥራኝ ጫካው ኧረ ጥራኝ ዱሩ፣ ለአንተም ይሻልሃል ብቻን ከማደሩ” እያሉ መኖሪያቸውን በዱር በገደሉ አደረጉ፡፡ ጥይት እንደ ቆሎ
ተቆላ፡፡ የፈሪ ልብ ተፈተነ፡፡ የጀግና ልብ ደነደነ፡፡
በዚያ ዘመን ለሀገራቸው ነጻነት ሲሉ የመረረውን ዘመን አሳልፈው የጣፈጠ ዘመን እንዲመጣ ካደረጉ አርበኞች የዚያኔው የሰሜን
በጌ ምድር አርበኞች ከግንባር ቀደሞቹ ናቸው፡፡ ቁጥራቸው ብዙ የሆኑ የሰሜን በጌ ምድር አርበኞች በየዱር ገደሉ እየተመላለሱ
የጣልያንን ሠራዊት ቁም ስቅል ያሳዩት ነበር፡፡ በዚያ ዘመን እልፍ ከነበሩት አርበኞች መካከል አንደኛውን ማስታወስ ፈለግን፡፡
የተወለዱበት ሀገር ስሙም ተፈጥሮውም ያስፈራል፡፡ በዚያ ቀዬ ተዘናግቶ የሚኖር ከቶም የለም፡፡ ከጠዋት ከማታ፣ ከቀን ከሌሊት
ሰው ሁሉ ጥንቁቅ ነው፡፡ ከመልካም ቤተሰብ የተወለዱ ናቸው፡፡ ጀግንነት የዘራቸው፣ የራሳቸው፣ ምግባራቸው ነው፡፡ የሰሜን
ቤጌምድር በረሃዎች ጀግንነትን፣ ዓልሞ ተኳሽነትን አጎልብተውላቸዋል፡፡ መልክዓ ምድሩ በአሻገር ሲታይ ልብን ያርዳል፤ የቆላ
ወገራ መረባ፣ የአርማጭሆ፣ የወልቃይት ጠገዴ በረሃ ጀግኖቹን በውስጡ ይዟልና፤ ያቺን ምድር ነጻነት የሚጋፋና ድንበር የሚገፋ
አርፎ አይቀመጥበትም በጥይት እሳት እየተቆላ እርር ብሎ ይቀራል እንጂ፡፡
አባታቸው ልጅ ተሰማ ጋረድ ይባላሉ፡፡ እናታቸው ደግሞ ደስታ ገብረሚካኤል ይባላሉ፡፡ ሁለቱም የሰሜን በጌ ምድር መኳንንትና
ወይዘሮ ናቸው፡፡ መኳንንቱና ወይዘሮይቱ ፈጣሪያቸውን የሚፈሩ፣ ሀገር ያከበራቸው ናቸው። በሰሜን በጌ ምድር ጠቅላይ ግዛት
በወገራ አውራጃ መረባ አስተርዮ ሜዳ ማርያም ይኖሩ ነበር። እኒህ ፈጣሪያቸውን የሚያከብሩ ሰዎች መልካም ልጅ ተሰጣቸው።
ወንድ ልጅ ወለዱ። ከአብራካቸው የተገኙትን ልጅ ውብ ናቸውና ውብነህ ሲሉ ስም አወጡላቸው፡፡ በስም የወጣ ውብነህ።
የተወለዱበት ዘመንም 1889 ዓ.ም እንደነበር ልጆቻቸው ነግረውኛል። አንዳንድ ሰዎች 1881 ዓ.ም ተወለዱ የሚሉት ልክ
አለመሆኑንም ነው የሚናገሩት።
የመኳንንቱ ልጅ ውብነህ በግርማና በሞገስ አደጉ። በልጅነት እድሜያቸው የቤተ ክህነት ትምህርት ተማሩ። መልካም ምግባር
ያላቸው፣ አርቀው የሚያስቡ ነበሩና ያየ ሁሉ ይወዳቸዋል። ያደንቃቸዋልም። ውብነህ ቀልጣፋ፣ ጠንካራ የሰውነት አቋም ያላቸው፣
ከሮጡ የማይቀደሙ፣ ከተኮሱ የማይስቱ ናቸው። በልጅነታቸው በአደጉበት በረሃ አደን ያድኑ ነበር። በረሃ ወርደው ባዶ እጃቸውን
አይመለሱም። ያሻቸውን ግዳይ ጥለው ይመለሳሉ እንጂ። ከታላላቅ አባቶች ሥር እየተቀመጡ የሀገራቸውን ታሪክ አንድ በአንድ
ይማሩ ነበር። የሚሰሙት የሀገራቸው ፍቅር ልባቸውን በደስታ መላው።
ውብነህ አንድ ቀን ለአደን እንደወጡ ከዋሊ ዳባ ዋልድባ ገዳም ውስጥ ይደርሳሉ። በዚያም አንድ የበቁ ባሕታዊ ያገኟቸዋል።
ውበነህ አስቀድመው ለሀገራቸው የተጠሩ ነበሩና ባሕታዊው ሰው “ምነው ውብነህ ለምን አሁን ትተኩሳለህ ወደፊት ሀገርህን
ለመቀማት ከሚመጣው ጠላት አትተኩስም ወይ ?” አሏቸው። ብልሁ አዳኝ ውብነህም እባክዎ አባቴ ባዕትዎትን(የፀሎት ቤት)
ያሳዩኝ አሏቸው። ባሕታዊው ሰውም ውብነህን አስከትለው ወደ ባዕታቸው ሄዱ። ወደ ዋሻ ውስጥም አሰገቧቸው። ቀን ቀን
ገዳሙን እንዲያገለግሉ ማታ ማታ ደግሞ ከደጅ እንዲተኙ አዘዟቸው።
የተባሉትን በቅንነት ፈፀሙ። ሶስት ወራትም ሞላቸው። በዚያም ጊዜ ባሕታዊው ሰው “ልጄ ሆይ የእናትህን ለቅሶ ጌታ አይቷል።
ከነገርኩህ ነጭ ጠላት ኢትዮጵያን ነፃ እንድታወጣ ከእግዚአብሔር ስልጣን ተሰጥቶሃል። ንጉሡንም ከሥደት ትመልሰዋለህ።
ዋጋሕን አይከፍልም። ያንተን ዋጋ የሚከፍሉሕ ሥላሴ ናቸው።” ብለው መርቀው አሰናበቷቸው። ውብነህ አደን አቆሙ። አስቀድሞ
የተነገራቸው የመከራ ጊዜ ደረሰ። የሚወዷት ሀገራቸውን ጠላት ወረራት።
ልጅ ተሰማና ወይዘሮ ደስታ ደጅ አዝማች ሐጎስ የሚባሉ ልጅም ነበሯቸው። ጀግና መውለድ ያውቃሉና። በዚያ ዘመን ነዋሪነታቸው
በጎንደር የነበሩ ቆንስሎች በረሃውን አቋርጠው ሲያልፉ ወንበዴ ያሰቃያቸው ነበር። ውብነህ ከደረሱ በኋላ ግን ወንበዴውን
አጥፍተው፣ የሚያጠፋውን እየመከሩ፣ የተጣላውን እያስታረቁ ሰላም አደረጉት። የሀገሬው ሰውም በፍቅራቸው ተነደፈ። ውብነህ
ውብነህ ይል ጀመር።
ጣልያን ማሰፍስፍ ጀምራ ነበር። የውብነህን ጀግንነት አስቀድመው የሰሙት ጣልያኖች ሊያታልሏቸው ፈለጉ። እሳቸቸው ግን
እንኳን ሀገራቸውን ነፃ ያወጡ ዘንድ ከፈጣሪያቸው ስልጣን ሲሰጣቸው ወትሮውንም የሀገር ፍቅር አለባቸውና ለጣልያን ጀሮ
አልሰጡም። ይልቁንስ ጣልያን መውረሩ እንደማይቀር ከንጉሡ የይለፍ ቃል ይዘው በአስመራ፣ ምፅዋ አልፈው ሲሄዱ ተረድተዋል።
ልጆቻቸው ወይዘሮ ገዳሪፍና ወይዘሮ ኢትዮጵያ እንደነገሩኝ በዚያም ዘመን የንጉሡ በዓለ ሲመት ነበርና በአስመራና ምፅዋ አልፈው
የጅቡቲ ቆንስል ከነበረው ራስ አንዳርጌ ጋር አክብረው በባቡር አዲስ አበባ ገቡ። በአስመራ ሲያልፉ ያዩትን የጣልያን ዝግጅት
ስለተመለከቱ ከንጉሡ ቀርበው ንጉሥ ሆይ ጣልያን ሀገራችን ለመውረር ቁርጥ አድርጋለችና የሀማሴን ወንድሞችን ይዤ መረባን
ሳይሻገር እንደወጋው የመሣሪያ ድጋፍ ይደረግልኝ ብለው ጠየቁ። ንጉሱ ግን ግድ የለም ይቆይ በፍቅር ይፈታል አሏቸው። በዚህም
ጊዜ ውብነህ በየገዳማቱ እየተዘዋወሩ ፈጣሪ ሀገራቸውን ከጠላት እጅ እንዳይጥላት ይማፀኑ ነበር ይባላል። ዓመታት አልፈው
ከአራት ዓመታት በኋላ ውብነህ ያሉት ነገር ደረሰ። ጣልያን መረባን ተሻገረች።
ንጉሡም “እንዳልከው ሰላም አልሆነም ጣልያን ሀገራችን ገብቷል። ዓድዋም ደርሷል። የሰሜኑን ሀገር ይዘህ ዝመት” ሲሉ
መልዕክት ላኩባቸው። ውብነህም “ለእኔ የሰሜኑን ግዛት ቢሰጡኝ ሹማምንቱ ተቆጥተው ለጠላት ይገባሉና። ባሉበት ይቆዩ ለእኔ
የጦር አበጋዝነቴ ይበቃኛል ባይሆን ሀገራችን ነፃ ስትሆን ያሉኝን ይሰጡኛል። ብከዳ ፈጣሪ ይክዳኝ” ብለው ላኩ። ውበነህ
የሀገራቸውን ጀግኖች አስከትለው ለሀገር ነፃነት መዋጋት ጀመሩ።
“ከሀገሬና ከሃይማኖቴ የሚበልጥብኝ ነገር የለም” የሚሉት ቆራጡ አርበኛ ጠመንጃቸውን ወልውለው፣ ልባቸውን አደላድለው፣
ተከታዮቻቸውን ይዘው የሮምን ሠራዊት ቁም ስቅል ያሳዩት ጀመር፡፡ የሮም ሠራዊት በጥይት ተቆላ፡፡ መውጫ መግቢያ ጨነቀው፡፡
ጠላት በወልቃይት ጠገዴ ሲመጣ እየመቱ ፣ በቋራ ሲወርድ በጥይት እየቆሉ ፣ በወገራ ሲወጣ እየተከተሉ፣ በአርማጭሆ ብቅ ሲል
አንገቱን በጥይት እየቀሉ፣ ወደ በለሳም ሲወርድ እየተከተሉ መድረሻ አሳጡት፡፡ ስመ ገናናው አርበኛ ውብነህ ጠላትን በደረሰበት
እንደ ስጦ ሲያሰጡት፡፡ ጠላት መላው ጠፋው፡፡ ምድር ጠበበችው፡፡ ጀግና ነው የተባለው የሮም ሠራዊት እየተመረጠ መጣ፡፡
አንደኛውም ከውብነህ ፊት አልቆም አለ፡፡ የውብነህ ጥይት መሬት ላይ አልወድቅ አለች፡፡ በዚህ የተጨነቀው የጣልያን ሠራዊት
ለውብነህ “ምግብ አቀብላችኋል” እያለ ንጹኃንን ያንገላታ እንደነበር ገሪማ ታፈረ ጎንደሬ በጋሻው በሚለው መጻሕፋቸው
አስፍረዋል፡፡
የጠላት ሠራዊት በየደረሰበት ሁሉ እየደረሱ የሚዋጉት ጀግናው አርበኛ ሀገሬውን ጉድ አስባሉት። ጣልያንም “በየሄድንበት ሁሉ
የምናገኘው ይሄስ ሠውም አይደል አሞራ ነው” በማለት ስም አወጣላቸው ይላሉ ልጆቻቸው። ከዚያ ወዲህም ከጠላት
በተሰጣቸው ስም አሞራው ውበነህ ይባሉ ጀመር። በፈጸሙት ጀግንነት የራስ ማዕረግ ስለተሰጣቸውም ራስ አሞራው ውብነህ
ይባላሉ።
ጣልያንን ቁም ስቅሉን ሲያሳዩት የሀገሬው ሰው እንዲህ ሲል ተቀኘላቸው
“ንጉሡ ተሰደው ያልሆነላቸውን
ራስ ደጅአዝማቹ ያልሆነላቸውን
ይነዳው ያጉዘው ጀመረ አሞራው ብቻውን”
አሞራው በዚያ በጭንቅ ዘመን በሰሜን በጌምድር አውራጃዎች እየተመላለሱ ኃያሌ ጀብዱዎችን ፈፅመዋል። ጠላት እጅ ሲሰጥ
እንኳን ለአሞራው ነው የምሰጥ የሚልላቸው አስፈሪ ሰው እንደነበሩ ይነገርላቸዋል።
አሞራው በጀግንነት በሚዋጉበት ግንባር ሁሉ ዘመናዊ መሳሪያ ከጠላት እጅ እየነጠቁ መልሰው ያቅሙት ነበር፡፡ በአሞራው
ጀግንነት የተበሳጩት ጣልያኖች በአውሮፕላን በመረባ አስተርዮ፣ በአርማጭሆና በሌሎች አካባቢዎች እየተዘዋወሩ ሰላማዊውን
ሰው መፍጀት ጀመሩ። ጠላት በጥር ወር 1930 ዓ.ም በሺህ የሚቆጠር ጦሩን አሰልፎ ወደ ጃኖራ አምርቶ ቀንጣ ከሚባለው ቦታ
ሲደርስ አሞራው ውብነህ “ያገሬ ልጅ አይዞህ በርታ ፣ ስላገርህ ለኢትዮዽያ ስትል በክብር ሙትላት፣ ነፃነቷን በደምህና በአጥንትህ
አስከብርላት”
ብለው ወኔ በመሰነቅ የጠላትን ጦር እንዳልነበር አደረጉት።
በዚህ ከባድ ጦርነት የጠላት ሠራዊቱ ግማሽ ያህሉ ሲያልቅ ቀሪው መሳሪያና ሠራዊት በአርበኞች እጅ ወደቀ። በዚያ ዘመን
የጠላትን ስንቅና ትጥቅ የያዘ አርባ መኪና ወደ ጎንደር ለማለፍ ዳባት ላይ መድረሱን አሞራው ሰሙ። በጠፍ ጨረቃ ገስግሰው
አምባ ጊዮርጊስ ላይ አርበኞችን አስደፍጠው መንገድ ላይ ተጠባበቁ። የጣልያን መኪና ሲደርስ የደፈጣ ተኩስ ከፍተው አርባውን
መኪና ማረኩ ይባላል።
በሌላ ጊዜ ደግሞ የጠላት ጦር ጎንደር ተነስቶ በለሳ ደረሰ። የአሞራው ውብነህ ጦር ከሌሎች አርበኞች ጋር አጣጥ መጠበቂያ
ከተባለው ተራራ አካባቢ ገጠመው። የፋሽስት ጣልያን ጦር ተደምስሶ የጦር አዛዣቻቸው ከጥቂት ወታደሮች ጋር በመሆን እግሬ
አውጭኝ ብሎ ፈረጠጠ፡፡ በዚህም ጊዜ እንዲህ ሲሉ ተቀኙላቸው፡፡
ʺየሰማዉን እንጃ ሮም ገስገሰ፣
የጦሩ መድሃኒት አሞራው ደረሰ።
ያየህም ተናገር የሰማህም አውራ፣
ተገናኝቶ ዋለ አሞራው ካሞራ።
ጎንደር ከግንቡ ላይ ያለው ነጭ አንበጣ
ከምን ሊገባ ነው አሞራው ሲመጣ፡፡”
በየደረሱበት ሁሉ ጠላት የሚበረግግላቸው፣ እንደ መንጋ የሚነዳላቸው፣ ዓልሞ የማይስተው ዓይናቸው፣ የማይደፈረው ክንዳቸው፣
ሰው ሆነው ሳለ እንደ አሞራ የሚያደርጋቸው፣ በጠላት አናት ላይ እንደ አሻቸው የሚከንፉት፣ ጀግንነታቸው ሀገሬውን አጀብ
አስባለው፡፡
ʺእንኳን ኢትዮጵያ ባለቤትዬው
ጣልያንም ቀና አንድ ቀን ባዬው” እንዳለ አርበኛው የአሞራው ጀግንነት ለወዳጅ ብቻ ሳይሆን ለጠላት ገረመው፡፡ አሞራው
በየደረሱበት ጠላትን ድባቅ እየመቱ የአካባቢውን አስተዳደር እያጠናከሩ አያሌ ጀብዱዎችን ይፈጸሙም ነበር ፡፡
የአርበኞች ሥራ አይሎ ጣልያን ወደ ሀገሩ መኮብለል ሲጀምር ጎንደርን ለማስለቀቅ የደብረታቦር፣ የእብናት፣ የበለሳ፣ የቋራ የወገራ
በአጠቃላይ የሰሜን በጌ ምድር አርበኞች ከጣልያን ፋሽስት ጦር ጋር ጦርነት ተደረገ። ጀግኖች አርበኞች በወገራ አምባጊዮርጊስ
የነበረውን የጣልያን ጦር እየደመሰሱ ወደ ጎንደር እንዲዘልቁ የቀሩት ደግሞ በቁልቋል በርና ጭልጋ ቆላድባ የሚገኘውን ጠላት
እየመቱ ወደ ጎንደር እንዲዘልቁ ተደረገ። የአርማጭሆና የጠገዴ አርበኞችም ራስ አሞራው ውብነህና ጀግኖች አርበኞች የጎንደርን
ጦር ከብበው ጣሊያንን አርመጠመጧት፡፡ በዚህም ጊዜ
ʺበአርማጭሆ መንገድ፣ በወገራ መንገድ፣
በስሜንም መንገድ፣ በመረባም መንገድ፣
በበለሳም መንገድ አይተላለፉ፣
አሞራው አርበኛ ይማታል በክንፉ።
የሮማ ነጭ በሬ ተከቧል በብረት ፣
ሊበላው ነው አሉ አሞራው ዞረበት፡፡” ተብሎላቸዋል፡፡
ገና በልጅነት እድሜያቸው የጀግንነት ሥራ እንደጀመሩ የሚነገርላቸው ታላቁ የጦር መሪ አሞራው ውብነህ ወደ ጦርነት
ከመግባታቸው በፊት ጸሎት ያደርሱ እንደነበር ይነገርላቸዋል፡፡ ታምራት ወርቁ የመማፀኛዋ ከተማ በሚለው መጻሕፋቸው
ʺአሞራው ሲፀልዩ መሬቱን እስከ ወገባቸው ድረስ ቆፍረው በመግባት ነበር” ብለዋል፡፡ ከጦርነት በፊት፣ ጸሎት ያደርሳሉ፡፡ ስልትም
ይነድፋሉ ይባላል፡፡ የምድር አርበኛ ብቻ አይደሉም የሰማይም አርበኛ ናቸው ራስ አሞራው ውብነህ፡፡
ራስ አሞራው ውብነህ ከነፃነት በኋላ ከራስ እመሩ ጋር የአካባቢውን ሰላም በማስከበር ጀብዱ ፈፅመዋል። ልጆቻቸው ወይዘሮ
ገዳሪፍና ወይዘሮ ኢትዮጵያ እንደነገሩኝ የዘውድ አማካሪ በነበሩበት ዘመንም ኢትዮጵያ ከሱዳን ጋር በሚያዋስናት ጠረፍ አንድ
ስንዝር መሬት
እንዳይሄድባት አድርገዋል። ድንበሯንም አስጠብቀዋል። ራስ አሞራው ጠላት የማይደርስባቸው፣ጥበበኛ፣ ቅን፣ አርቆ አሳቢ፣
መካሪ፣ የገንዘብ ፍቅር የሌለባቸው ጀግና ሰውም ነበሩ።
ባለቤታቸው ዘነበች መሸሻም እንደ አሞራው ሁሉ ደፋር እርበኛ እንደነበሩ ነው የሚነገርላቸው፡፡ ʺባልና ሚስት ከአንድ ወንዝ
ይቀዳሉ” እንዲሉ ጀግናው ጀግናዋን አግብተው ኖረዋል፡፡ ሳይሰለቹ እየተኮሱ፣ እንዲቀናቸው ኪዳን እያደረሱ፣ ቆመው እያስቀደሱ
ጠላትን ደምስሰው የነጻነት ዘመንን አመጡ፡፡ ባለቤታው ዘነበች መሸሻ ለጀግንነታቸው የአርበኝነት ኒሻን ባለ አምስት ዘንባባ፣ የድል
ኮኮብ ሜዳሊያ፣ የእንግሊዝ መንግሥት የአፍሪካ ኮኮብ፣ ከአንግሊዝ መንግሥት የድል ኮኮብ ኒሻን ተሸልመዋል። ጀግነዋ ሴት
ጦር ፣እየመሩና እያደራጁ ሀገርን ነፃ አድርገዋል።
በጀግንነት የተዋደቁት፣ የጨለማውን ዘመን አስቀርተው፣ የብርሃን ዘመን ያመጡ የብርሃን ሰው ናቸው። እኒህ ጀግና ከነጻነት በኋላ
በጎንደር አደባባይ ለኢትዮጵያ ጦር ድጋፍ ያደረገው የእንግሊዝ ባንዴራ ከኢትዮጵያ ሰንደቅ ጋር ሊወለበለብ ሲል አሻፈረኝ ብለው
የሀገራቸውን ሠንደቅ ብቻ እንዲውለበለብ ያደረጉ መሆናቸውም ይነገርላቸዋል፡፡ በአንድ ሀገር አንድ ሠንደቅ እንጂ ሁለት
አይፈቀድም፣ የሚፈቀደውም አርንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀዩ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ነው ያሉ ሰው ናቸው።
በእሳት ውስጥ ተፈትነው ሀገራቸውን ከጅብ አፍ ያተረፉት ራስ አሞራው መስከረም 6 ቀን 1975 ዓ.ም ነበር ሕይወታቸው
ያለፈው፡፡ በእሳት የተፈተነ ዘመን አልፈው ያልተደፈረች ሀገር፣ ያልተቀናነሰ ክብር፣ ያልደበዘዘ የሀገር ፍቅር፣ በፈተና የማይናወጥ
የጀግንነት ሚስጥር አውርሰዋልና ስምዎ ከፍ እንዳለ ይኖራል።
በታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች
ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m


Previous article“ያልተዘመረላቸው ኢትዮጵያዊ ሌተናል ጀነራል”
Next articleኮሚሽነር አበረ አዳሙ የአማራ ፖሊስ ዘመናዊ አሠራር እንዲከተልና ብቁ ተቋም እንዲሆን ከፍተኛ ጥረት ያደረጉ እንደነበሩ የሥራ ባልደረቦቻቸው ተናገሩ፡፡


Source link

Related posts

ʺአንተ በረሃ ሆይ የወገኖቻችንን ነብስ መልስ”

admin

ለቴክኖሎጂ ቅጂና ፈጠራ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሠራ የአማራ ክልል ቴክኒክ፣ ሙያና ኢንተርፕራይዞች ልማት ቢሮ አስታወቀ፡፡

admin

ሀገራቸውን በዓለም አደባባይ ከፍ ያደረጉ የኢትዮጵያውያን ባለዉለታው፣ የኮሪያው ዘማች አርበኛ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ፡፡

admin