76.03 F
Washington DC
June 18, 2021
Satenaw Ethiopian News/Breaking News
Amharic News

ʺየደፈሩሽ ሁሉ ይዋረዳሉ፣ የናቁሽ ሁሉ ይወድቃሉ”

ʺየደፈሩሽ ሁሉ ይዋረዳሉ፣ የናቁሽ ሁሉ ይወድቃሉ”

ባሕር ዳር፡ መጋቢት 16/2013 ዓ.ም (አብመድ) ኢትዮጵያዊነት ኃይል ነው ይጋፋል፣ ቆራጥ ነው መከራን ያልፋል፣ ሰይፍ ነው ይቀስፋል፣ ብርሃን ነው እያበራ ይሰፋል፣ ኢትጵያዊነት ኩራት፣ ኢትዮጵያዊነት ፅናት፣ ኢትዮጵያዊነት አይሸነፌነት፣ ኢትዮጵያዊነት አንድነት፣ ኢትዮጵያዊነት ትግዕስት፣ ኢትዮጵያዊነት በረከት፣ ኢትዮጵያዊነት ረድኤት፣ ኢትዮጵያዊነት ነጻነት ነው፡፡ ሰዎች ሁሉ በኢትዮጵያ ይኮራሉ፤ መከራዎች ሁሉ በኢትዮጵያዊነት ይታለፋሉ፤ ብልጦች ሁሉ ኢትዮጵያን ይወዳሉ፤ ሞኞች ሁሉ ኢትዮጵያን ይጠላሉ፡፡ የጠሏት ይወድቃሉ፣ ያከበሯት ይከብራሉ፡፡

ኢትዮጵያ ዳሯ እሳት የነካትን የሚያቃጥል፣ መኋላ በረከት የሚያጠግብ፣ በስጋም በመንፈስም የሚመግብ ነው፡፡ የሚጠብቋት ጥንቁቆች፣ ረቂቆች፣ ኃያሎች፣ አስፈሪዎች፣ አይሸነፌዎች ናቸው፡፡ ሊቃውንት ለምድር የተሰጠው ሁሉ በኢትዮጵያ አለ፤ ኢትዮጵያ የተመረጠች፣ በጸጋ የተጠበቀች፣ በፈጣሪ የተባረከችና የተመረጠች ናት ይሏታል፡፡

በሌላው ዓለም ያለው በኢትዮጵያ አለ፤ በኢትዮጵያ ያለው ግን በሌላው ዓለም የለም፡፡ የሰማይ ፀጋ፣ የእግዚአብሔር ዋጋ በኢትዮጵያ ላይ አለና፡፡ ፈጣሪ የጠበቃትን ሰው ሊገፋት አይቻለውም፣ ፈጣሪ በሚስጥር ያስቀመጣት ሰው ተመራምሮ አይደርስባትም፤ ድብቅ ሚስጥር ልዩ ክብር ናትና፡፡

ጠላቶቿ በየዘመናቱ ተነሱ፤ ሁሉም እያፈሩ ተመለሱ፤ በውስጥ የሚነሱባት ጠላቶቿም እየተነሱ እየተቀሰፉ፣ በውርደት እያለፉ ዘመናትን አልፋለች፡፡ ኢትዮጵያን አክብሮ እንጂ አዋርዶ የከበረ አይገኝም፤ ኢትጵያዊያን ስለ ፍቅር እጅ ይነሳሉ፤ ስለ ጠብ ነፍጥ ያነሳሉ፤ በሀገራቸው ክብር አይደራደሩም፤ አይፈሩም፤ አይደፈሩም፡፡

ኢትዮጵያ በዚህ ዘመንም ፈታኞቿ አልተኙላትም፡፡ ከውጭ አንገታቸው የረዘመ፣ ከውስጥ እይታቸው የጨለመ ጠላቶቿ ኢትዮጵያን እየፈተኗት ነው፡፡ እርሷም ለዘመናት እየተፈተነች ያለፈችውን ፈተና አሁንም በፅናት እየተፈተነችው ነው፡፡ ተፈትና ታልፋለች፤ ከፍ ብላ ጠላቶቿን ዝቅ ታደርጋለች፣ እርሷ ኮርታ ጠላቶቿን ታሳፍራለች፡፡ የደፈሩሽ ሁሉ ይዋረዳሉ፣ የናቁሽ ሁሉ ይወድቃሉ፡፡

በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የሶሾሎጂ ትምህርት ክፍል መምህር ዶክተር ቡሻ ታኣ ኢትዮጵያዊያን በዓለም ላይ ሰው ባልበዛበት፣ ሀገራት ባልተቋቋሙበት ጊዜ ሀገርን አስፍተው፣ ዳርና ድንበሩን ጠብቀው ያስተዳድሩ ነበር፣ ኢትዮጵያዊነት በአንድነት፣ በእኩልነት፣ በመተሳሰብ፣ ዘርና ሃይማኖት ሳይቆጠር ለሁለንተናዊ እድገት የሚኖርበት ነው ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያዊያንም ይህንኑ ነው እያደረጉት የመጡት ነው ያሉት፡፡ በየጊዜው እያደገ የመጣው የዓለም ልዩነት ለኢትጵያዊያን እንደ ልዩነት አይታይም ነበር፤ ኢትዮጵያዊያን በአንድነት፣ በስምምነት፣ በመግባባት ስለሚሰሩ ከልዩነት ይልቅ አንድነት ይታይበታል ነበር ነው ያሉት፡፡

ʺኢትዮጵያ ማለት የታላቆች ሀገር፣ የብዙኃን ሀገር፣ ሰዎች ተደጋግፈው የሚኖሩባት፣ የሚተሳሰቡባት፣ ሁልጊዜም አብሮ መኖርን፣ ሁለንተናዊነትንና ክብርን ይዘው የሚራመዱባት፣ የሄዱባትና የኖሩባት ሀገር ናት” ሲሉም ኢትዮጵያን ይገልጿታል፡፡

ʺኢትዮጵያዊነት የቀደመውና የአሁኑ የሚባል የለም ኢትዮጵያዊነት አንድ ነው፤ በቀደመው ጊዜ ኢትዮጵያዊያን ጠንከር ብለው ስለሀገራቸው፣ ስለሕዝባቸው፣ ስለጎረቤታቸውና ስለዓለም በማሰብ ታላቅ ነገርን ያደርጉ ነበር፤ አሁን ላይ የዘር ፖለቲካ መምጣት አንድነትን የሚያናጉ ነገሮች ይታያሉ፣ ነገር ግን ይሄ ኢትዮጵያዊነትን ቀነሰ ማለት ሳይሆን ኢትዮያጵያዊነትን ለመቀነስ ያሰቡ የተቀነሱበት፣ የተዋረዱበት ጊዜ እንጂ ኢትጵያዊነት ምንግዜም በከፍታ ላይ ነው ያለው፤ ምንጊዜም ቢሆን ኢትዮያዊነት መውደቅ አይችልም፤ አይወድቅም ወደታችም አይሳብም፤ የሚጎትቱትን ይጥላቸዋል እንጂ በምንም ጊዜ በየትኛውም አቅጣጫ ቢሞክሩ ኢትዮጵያዊነትን መጣል፣ ማውደም አይችሉም፤ ኢትዮጵያዊነት ሀሳቡ ሁልጊዜ ታላቅ ስለሆነ ከጊዜ ወደጊዜ እያንኮታኮታቸው፤ ሁልጊዜም ከፍ እያለ ነው የሚሄደው” ነው ያሉኝ፡፡

አንዳንድ ሰዎች ስለ ኢትዮጵያና ስለ ኢትዮጵያዊነት ላይገባቸው ይችል ይሆናል እንጂ ኢትዮጵያዊነት ለሁሉም ኩራት ነውም ነው ያሉት ዶክተር ቡሻ፡፡ መዋደድ፣ መተሳሰብ፣ መፋቀር ማለት ኢትዮጵያዊነት ማለት ነው፤ ኢትዮጵያዊነት እንኳን ለኢትዮጵያዊያን ኢትዮጵያዊ ላልሆኑ ሰዎችም ኩራት ነውም ይላሉ፡፡

የአፍሪካ ሀገራት በኢትዮጵያ ይኮራሉ፤ ኢትዮጵያ ለጥቁሮች ምልክት ናት፣ ጥቁሮች ሁሉ ስለ ኢትዮጵያዊነት ጠንቅቀው ያውቃሉም ነው ያሉኝ፡፡ የኢትዮጵያዊነት ሀሳብ መጎዳት የለበትም፣ ኢትዮጵያዊነት ተወጋ ማለት የዓለም ጥቁር ሕዝብ ተዋጋ ማለት ነው፤ የኢትጵያዊነት ሀሳብ ከፍታ ነው፤ የፍትሕ ጉዳይ ነውም ብለዋል፡፡

ትንንሽ ሰዎች ኢትዮጵያን ቢነቁም፣ ተፈትኖ ተሞክሮ አልቻሉትም፤ ፈጣሪም አይረዳቸውም፤ ኢትዮጵያዊነትም መቸም ቢሆን አይሸነፍም ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያን አሁን ላይ ስለገጠማቸው ጉዳይ ሲያብራሩም- ከሚታየው ነገር አንጻር መስጋቱ አግባብ ነው፣ ሰው ካልሰጋ ምንም ላለማድረግ ፈቃደኛ ነው ማለት ነው፡፡ ነገር ግን ፈርጠም ብሎ ፈተናውን ማለፍና ሰይጣናዊ ተልዕኮ ያላቸውን ሰዎች ተባብሮ ቦታቸውን በመሥጠት፣ ችግሩን የምንጋፈጥበት ጊዜ ነውም ብለዋል፡፡

“ነገሮች እንዳይጎዱን መጠንቀቅ ያስፈልጋል፤ ተሰባስበን እርምጃ የምንወስድበት ጊዜም ይኖራል፣ በመርገም ብቻ ጠላትን ማሸነፍ አይቻልም፤ አያገባኝም የሚል አመለካከት አያስፈልግም፤ የሁላችን ሀገር ናት ያገባናል፤ መከፈል ያለበት ነገር ካለም መክፈል አለብን” ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ አሁን ላይ እየተፈተነች ነው ያሉት ዶክተር ቡሻ በኢትዮጵያ ላለው ሞትና ኪሳራ መነሻው የፖለቲካ ስርዓቱ ብልሽት ነውም ብለዋል፡፡ ጠላቶች በየቀኑ አዲስ ነገር እያደረጉ ሊያስገርሙን አይገባም፣ ለኢትዮጵያ ሕዝብ በየቀኑ አዲስ ጥፋት እያመጡም ማዬት የለብንም፤ መቆጣጠር ይገባል ነው ያሉት፡፡

ኢትዮጵያ በዚህ ውጥንቅጥቅ መቀጠል ስለሌለባት የሕገ መንግሥት ጉዳይ መታዬት አለበትም ነው ያሉት ዶክተር ቡሻ፡፡ “ሰላም ነው የሚሻለው ወይስ ፌደራሊዝም ነው የሚሻለው?” የሚሉት ዶክተሩ የብሔረሰብ ፖለቲካ ስርዓት ለመጠበቅ ሲባል ሰው እንዲሞት መፍቀድ የለብንም ብለዋል፡፡ በኢትዮጵያ ስላለው ግጭት መረጃ ሊኖር ይገባል፤ በተለያዩ አካባቢዎች ጥቃት የሚያደርሱ ሰዎች በምን መንገድ ሄደው ጥቃት አደረሱ የሚለው መታዬት አለበት፡፡ የሄዱበት የትራንስፖርት ጉዳይም መጠየቅ አለበት፤ መንግሥት ሕዝብን መስማት አለበትም ብለዋል፡፡

እንደ ሀገር ከልዩነት ግድግዳዎች የበለጠ የአንድነት ድልድዮችን መሥራት ይገባናልም ነው ያሉት፡፡ በኢትዮጵያ ምድር ሁሉም ኢትዮጵያዊ ነው፤ የዚያኛው ዘር ነው መባል የለበትም፤ እያንዳንዱ የተወለደበትን የሚቀማው የለም፣ የሚያዋጣው ኢትዮጵያዊነት ነው ብለዋል፡፡

ʺመከፋፈሉ ቀርቶ አንድ ሀገር፣ አንድ ብሔራዊ መዝሙር፣ አንድ ሰንደቅ ዓላማ፣ አንድ ሕዝብ ነው ለእኛ የሚያስፈልገው” ሲሉም ያስረዳሉ፡፡

በየቀኑ ሴት ልጅ የምታለቅስበት ሥርዓት ለምን ኖረ? ብሎ መጠየቅና መንግሥትም ይሄን የሚያዳምጥ ጀሮ ሊኖረው ይገባል፡፡

ኢትጵያዊነት መኩሪያችንና መከበሪያችን ነውም ብለዋል ዶክተር ቡሻ፡፡ ኢትዮጵያን – እናት፣ አባቶች፣ አያቶችና ቅድመ አያቶች እንዳቆዩን ሁሉ በከፍታ ላይ የማቆዬት ግዴታ ስላለብን ኢትዮጵያዊ ሁሉ ለአንድነት፣ ለእድገትና ለፍቅር ራሱን መስዋዕት ለማድረግ ዝግጁ ማድረግ አለበትም ብለዋል፡፡

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡

Source link

Related posts

የሕግ ማሻሻያዎች ባለፉት ሦስት ዓመታት ለተሰሩት ሥራዎች ምሰሶዎች ናቸው – ጠ/ሚ ዐቢይ

admin

ለትምህርት ሚኒስቴር 500 ሺህ ማስክና 11 ሚሊየን ብር ግምት ያላቸው የሙቀት መለኪያ መሳሪያዎች ድጋፍ ተደረገ

admin

ለአዲሱ የሲዳማ ክልል መስተዳድር የተደረገው የክልሎች ድጋፍና አንደምታዎቹ | ዘ-ሐበሻ (ZeHabesha)

admin