71.98 F
Washington DC
May 17, 2021
Satenaw Ethiopian News/Breaking News
Amharic News

ʺእነሆ የአላፊው ዓለም ጉዟቸውን ፈፀሙ”

ʺእነሆ የአላፊው ዓለም ጉዟቸውን ፈፀሙ”

ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 22/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ንቁ ደቀ መዝሙር፣ ብልህ መምህር፣ የሚስጥር መፍቻ፣ የሊቃውንት መፍለቂያ ምንጭ፣ የእግዚአብሔር መልካም አገልጋይ፣ የምዕመናን ትጉህ መሪ፣ መልካም ተናጋሪ፤ መጋቤ ሕይወት፣ መጋቤ ሃይማኖት፣ መጋቤ ሥርዓት፡፡ ብልሕ እረኛ፣ ጥንቁቅ መልክተኛ፣ እግዚአብሔር የመረጣቸው፣ መርጦ ያከበራቸው፣ ለቅድስና ለመልካምነት ያዘጋጃቸው ናቸው፡፡

ምድራዊያን አባታችን አጣን፤ መጠጊያ ዋርካችን ተቆረጠብን፣ ምርኩዛችን ተቀማን፣ መንገድ አመላካቻችን ጠፋብን ብለው ያለቅሳሉ፡፡ ምድር አለቀሰች፣ ሊቃውንቱ አዘኑ፣ ምዕመናኑ ደረታቸውን ደቁ። እንባቸውን አፈሰሱ፣ እረኛው በጎቻቸውን ጥለው ጠፍተዋልና በጎቹ ተረበሹ። ዋይታው ያሳዝናል፣ ሀዘኑ ልብን ያሰብራል። የሞት ጥላ ከባድ ነውና ገዳሙ ተረበሸ። በዋይታ ተሞላ።

ʺበእግዚአብሔር ፊት በሕያዋንና በሙታንም ሊፈርድ ባለው በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ፊት በመገለጡና በመንግሥቱም እመክርሃለሁ፤ ቃሉን ስበክ በጊዜውም ካለጊዜውም ጽና፤ ፈጽመህ እየታገስክና እያስተማርክ ዝለፍና ገሥጽ ምከርም። ሕይወት የሚገኝበትን ትምህርት የማይታገሡበት ዘመን ይመጣልና፤ ነገር ግን ጆሮቻቸውን የሚያሳክክ ስለሆነ እንደ ገዛ ምኞታቸው ለራሳቸው አስተማሪዎችን ያከማቻሉ። እውነትንም ከመስማት ጆሮቻቸውን ይመልሳሉ፡፡ ወደ ተረትም ፈቀቅ ይላሉ። አንተ ግን ነገርን ሁሉ በልክ አድርግ፡፡ መከራን ተቀበል፤ የወንጌል ሰባኪነትን ሥራ አድርግ፡፡ አገልግሎትህን ፈጽም። በመሥዋዕት እንደሚደረግ የእኔ ሕይወት ይሠዋልና፡፡ የምሄድበትም ጊዜ ደርሶአል። መልካሙን ገድል ተጋድዬአለሁ፣ ሩጫውን ጨርሼአለሁ፣ ሃይማኖትን ጠብቄአለሁ፣ ወደ ፊት የጽድቅ አክሊል ተዘጋጅቶልኛል፡፡ ይህንም ጽድቅ ፈራጅ የሆነው ጌታ ያን ቀን ለእኔ ያስረክባል፡፡ ደግሞም መገለጡን ለሚወዱት ሁሉ እንጂ ለእኔ ብቻ አይደለም። በቶሎ ወደ እኔ እንድትመጣ ትጋ” እንዳለ መጻሕፍ፡፡

ሩጫቸውን ጨርሰዋል፡፡ ሃይማኖታቸውን ጠብቀዋል፡፡ ታሪክ አስቀምጠዋል፡፡ ስማቸውን በነጠረ ቀለም ጽፈዋል፡፡ ከዘመናቸው ያበከኗት ጊዜ አልነበረችም፡፡ ያለ ቁምነገር ያለፈች አንዲትም ሰዓት አላስተረፉም፡፡ የተሰጣቸውን ጊዜ፤ ለሰጣቸው ኖሩለት፣ እነሆ የአላፊውን ዓለም ጉዟቸውን ፈፀሙ፡፡ ወደ ማያልፈው ዓለም ገሰገሱ፡፡

በበዓለ መስቀል ተወለዱ። በበዓለ ስቅለትም ዘመናቸውን ፈፀሙ። አኗኗራቸው ግሩም ነውና ያያቸው ሁሉ ግሩም ይላል። ጌታ የእናታቸውን ማሕፀን አስቀድሞ ባረከው። ቅዱስ ልጅ ይወለድበት ዘንድም አዘጋጀው። የተባለው ቀን ደረሰ። ጌታ በባረከው ማሕፀን የሚወለደው መልካም ፅንስ የመወለጃ ጊዜው ደረሰ። በሰሜን በጌምድር ጠቅላይ ግዛት በደብረታቦር አውራጃ በደራ ወረዳ አባ ታዬ ውቤና እማሆይ የሺሐረግ በለጠ የሚባሉ ደጋግ ሰዎች ነበሩ። ጌታን የሚፈሩ፣ በምግባር የፀኑ ነበሩ። መልካሟ እናት እማሆይ የሺሐረግ በደግነት ይኖሩ ነበርና አንድ ቀን ስውር ባሕታዊ ያይዋቸዋል። እኒያ ስውር ባሕታዊውም ከተደበቁበት ተገልጠው “እማ ሆይ ደግ ልጅ ትወልጃለሽ ስሙንም ጥበቡ ብለሽ ጥሪው” ብለዋቸው ተሰወሩ። በልባቸው አሰቡት። በደግነትም ጠበቁት። እኒያ ደጋግ ባልና ሚስቶች በንጽሕና ተዋወቁ። የተባረከ ፍሬም ተሰጣቸው።

የተባለው ደግ ፍሬ በተባረከ ማሕፀን ተገኘ። ቀኑ መስከረም 17/1922 ዓ.ም ነበር። በዚህም ቀን የመስቀል በዓል ይከበራል። አስቀድሞ የተነገረላቸው ልጅም በበዓለ መስቀል ተወለዱ። ስማቸውም አስቀድሞ ወጥቶላቸዋልና ጥበቡ አሏቸው። የጥበብ አባት። እኒህ ሰው የተወለዱበት ሥፍራ በደራ ወረዳ “ቁላላ መስቀለ ኢየሱስ ዘሴ” የተባለ ቦታ ነበር። በጥበብ አደጉ። በመንፈስም ተጠበቁ። በምግባርም ኖሩ፤ ለትምህርትም ደረሱ። የፊደል መቁጠሪያ ዘመናቸው ሲደርስም በእናታቸው የትውልድ ሥፍራ በደብረ ምሕረት ዛራ ቅዱስ ሚካኤል ገዳም ከመምህር አባ ታምራት ብሩ ፊደል መቁጠር ጀመሩ። ጉልበታቸው ሳይጠና ልጅነታቸውን ሳያሳልፉ አባታቸውን ሞት ነጠቃቸው። ሐዘን ገባቸው። ልባቸው ተረበሸ። እናታቸውም ወደ ፈለገ ሕይወት ጎሐ ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን ይዘዋቸው ሄዱ።

ትምህርታቸውን እየተማሩ ለእናታቸው ከብቶችን ያግዱ ነበር። አንድ ቀንም ቤተ ክርስቲያን ይሳለሙ ዘንድ ሄዱ። በምስራቅ ንፍቅም ቆሙ። አንድ ቅዱስ ባሕታዊም አስቀድመው ወደ ተመረጡት ብላቴና መጡ። “ልጄ ሆይ የአንተ ሥራ ከብት ጥበቃ አይደለም። ወደ ደብረ ምሕረት ዛራ ቅዱስ ሚካኤል ገዳም ሂድና ትምህርትህን ተማር የብዙ ሊቃውንት አባት ትሆናለህና” ብለዋቸው ተሰወሩ። እኒያ ብላቴና መልካሙን መንገድ ተመለከቱ። በሰሙት ነገር ተገረሙ። ወደ ተባሉበት ሥፍራ ተመለሱ። ትምህርታቸውንም ቀጠሉ። ዳዊት ደገሙ፣ ውዳሴ ማርያም ዘለቁ፣ ወደ ወንጨት ቅዱስ ሚካኤል ገዳም ሄዱ። ከመምህር ቃለ ወንጌል መስተጋብዕ አርባዕት ተማሩ።

ወደ አፈሯ እናት ማኅደረ ስብሐት ሽሜ ማርያም ሄዱ። በዚያም ፆመ ድጓና ምዕራፍን ተማሩ። ወደ ጎጃም ክፍለ ሀገርም ሄዱ። በአዴት ቅድስተ ሐና የሰምና የወርቅ ቅኔን ተማሩ። ወደ ሰሜን በጌምድር ጠቅላይ ግዛት ተመልሰው ወደ አለፋ ጣቁሳ መኮንታ ኢየሱስ ሄዱ፤ በዚያም የሰምና የወርቅ ቅኔን ከእነ አገባቡ አዋጁ፣ ከእነ ዕርባ ቅምሩ አጠናቀቁ። በኮረብታ ማርያምም አዕማደ ሚስጥር፣ ውዳሴ ማርያምና ቅዳሴ ማርያም ትርጓሜ ተምረው አጠናቀቁ።

ወደ ናበጋ ቅድስት ማርያምና ቅዱስ ሚካኤል ሄደው መፅሐፍተ ብሉያትን፣ ሐዲሳትን፣ ፍትሐ ነገሥትንና ሌሎችንም የትርጓሜ መፃሕፍትን አጠናቀቁ። በመምህርነትም ተመረቁ። ወደገዳም ገብተው መኖርንም መረጡ። መምህራቸው የነበሩ አክሊሉ ወርቅነህ ግን ጉባኤ ከፍተው እንዲያስተምሩ ነገሯቸው። ወደ ደንቢያ ወጄት ቅድስት ማርያምና አርባያ ቅዱስ መድኃኔዓለም ጉባኤ ተክለው እንዲያስተምሩ ላኳቸው። ወደ መና መቀጠዋ አጃ ፋሲለደስም ሄደው አስተማሩ። በስማዳ ቅድስት ኪዳነ ምህረት ደብርም አስተማሩ።

በስማዳ በነበሩበት ጊዜ ለክብረ በዓል ወደ ገዳመ ወንያት አቡነ ሐራ ድንግል አንድነት ገዳም ይሄዱም ነበር። በዚያም በዑራ ኢየሱስ ገዳም ይኖሩ ከነበሩ አባ ገብረ ማርያም ከተባሉ ባሕታዊ ጋር ተገናኙ። እኒያ ባሕታዊም “ፊደል ወደጀመርክበት ወደ ደብረ ምሕረት ዛራ ቅዱስ ሚካኤል ገዳም ሂድና አስተምር“ ብለው አመጧቸው። በዚያ ሥፍራም ሊቃውንትን እንደሚያፈሩ ነገሯቸው። በዚያውም የተባሉትን አደረጉ።

ወላዴ አዕላፍ መልአከ ምሕረት የኔታ ጥበቡ ታዬ የሊቃውንት መፍለቂያ፣ የእውቀት ባሕር፣ የፍቅር ተክሊል፣ የትህትና ቀንዲል፣ የመልካም ምግባር አባት፤ ማዕረገ ዲቁናቸውን በጎንደር ደብረ ብርሃን ቅድስት ስላሴ ቤተ ክርስቲያን ከብፁዕ አቡነ ይስሐቅ ተቀበሉ፡፡ በጎንደር አቡን ቤት ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ከአቡነ እንድሪያስ ቀዳማዊ ማዕረገ ቅስና እና ማዕረገ ቁምስና ተቀበሉ። በጎንድ ተክለሃይማኖት አንድነት ገዳምም ሥርዓተ ምንኩስናን ፈፀሙ።

ፊደል በጀመሩበት በዛራ ቅዱስ ሚካኤል ገዳምም ጉባኤ ከፈቱ። ዕልፍ የሆነ ደቀ መዛሙርትን አፈሩ። ለ57 ዓመታት በዛራ ቅዱስ ሚካኤል ገዳም ተትክሎ ባልተነቀለው ጉባዔያቸው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስን፣ ብፁዕ አቡነ እንድሪያስ ካልዕን፣ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስን፣ ብፁዕ አቡነ ሚካኤልን፣ ብፁዕ አቡነ በርናባስ ካልዕ የተባሉትን ጳጳሳት አስተምረዋል። የአራቱ ጉባያት መምህር ሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ ሀዲስን፣ ባሕታዊ ነብዬ ልዑልን፣ መምሕር ዶክተር ሐዲስ ትኩነህን፣ መጋቤ ሐዲስ ስቡህ አዳምጤን፣ መጋቤ ምሥጢር ፍሬ ስብሐት ዱባለንና ሌሎች ዕልፍ የሆኑ ሊቃውንትን አፍርተዋል። ለዚያም ነው ወላዴ አዕላፍ የተባሉት።

ጉባኤ ቤታቸውን የማያስታጉሉት ታላቁ ሊቅ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለሃይማኖትን ጨምሮ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ጉባኤ ቤታቸውን ይጎበኙ እንደነበር ይነገራል። ረዳት የሌላቸውን ደቀ መዛሙርቶቻቸውን ድጋፍ እያደረጉ ያስተምሩ እንደነበርም ይነገርላቸዋል። አስታራቂ፣ መካሪና ዘካሪም ናቸው። በዛራ ቅዱስ ሚካኤል ገዳም ውስጥ የቅዱስ ዑራኤል ቤተክርስቲያን አሠርተዋል። ይህ ቤተ ክርስቲያን ከመሠራቱ በፊት በዚያ ሥፍራ የታላቁ ሊቅ መስቀል ጠፋች። ቆይታም ተገኘች። ስትገኝም የሚያንፀባርቅ ብርሃን ነበራት። መስቀሏ የተገኘችበትም የዑራኤል ክብረ በዓል የሚከበርባት ቀን ነበረች። ምልክት ነበርና ደብሩን አነፁ።

እኝህ አባት ገድለ ፃዲቁ አቡ ሐራ ድንግልን፣ የጎንድ ተክለሃይማኖት ፃዲቁ ዮሐንስን ገድል፣ የጣራ ገዳም አቡነ ኤዎስጣቴዎስን ገድል፣ የዋሻ እንድሪያስ የፃዲቁ አቡነ እንድሪያስን ገድል ከግዕዝ ወደ አማርኛ ተርጉመዋል። ለ68 ዓመታት አስተምረዋል።

የማለፍ ዘመን መጣ። የስጋ ሞትን መቅመስ ግድ ሆነ። ፈጣሪ የምድር ቆይታቸውን አጠናቀዋል አላቸው። ወደ እርሱም ይሄዱ ዘንድ ፈቀደ። የስጋ ዘመናቸው ተፈፀመ። ታላቁ ሊቅ በሚያዚያ 20/2013 ዓ.ም አለፉ። በሚያዝያ 22/2013 ዓ.ም በጌታቸው በኢየሱስ ክርስቶስ ስቅለት ቀን ግብዓተ መሬታቸው ተፈፀመ። ለ57 ዓመታት ጉባዔ ቤት ከፍተው ባስተማሩበት ፊደልም በጀመሩበት በዛራ ቅዱስ ሚካኤል ገዳም ሥርዓተ ቀብራቸው ሲፈፀም ተገኝቼ ነበር።

ግርማው የሚያስፈራው ገዳም በሰው ተጨናንቋል። የሚያዝነው በዝቷል። መካሪያችን፣ አባታችን፣አልባሻችን፣ አጉራሻችን አስታራቂያችን ጥለውን ጠፉ እያለ የሚያዝነው ብዙ ነው። የከፋ ዘመን ነውና ጸሎታችሁ ያስፈልገናል። የመከራውን ዘመን አሳልፉን ይላሉ። እንባቸውን ያፈሳሉ። ደረታቸውን ይደቃሉ። ጸሐይም ጨልማለች እኛም ጌታችንን አጥተናል ወዮልን ወዮታ አለብን ይላሉ። ሊቃውንቱ ለእኛ ቀረብን እንጂ እርስዎስ ከአድካሚው ዘመን አረፉ። ወዮልን ለኛ። የጥበብ መፍቻው ቁልፍ ለጠፋብን እያሉ ያዝናሉ።

እርሳቸው ረጅም ዘመን በቆዬው ዘመናቸው ብዙ ሊቃውንትን አፍርተው ነው ያለፉት። አቤቱ ጥላችን ነጠከን፣ መጠጊያችን አሳታጣኸን፣ በዚህ ቀን ክርስቶስ ሞትን ገደለ። እሳቸውም በጸሎታቸው በተጋድሏቸው ሞት በሞተበት ቀን አረፉ። ሞትንም ገደሉት ይላሉ ሊቃውንት። ሊቁ በዓለም የሞቱ ናቸው። ዓለምም በሊቁ ዘንድ የሞተች ናት – አይተዋወቁምና ይላሉ ደቀ መዛሙርቶቻቸው። በረከት ራቀን፣ ዋርካችን ተቆረጠ የሚሉት ምዕመናን ግን በቶሎ የሚፅናኑ አይመስለኝም ልባቸው ተጎድቷልና። ያለ እረኛ ቀርተዋልና። የምታስተውን ዓለም አያውቋትም። የምታስተው ዓለምም አታውቃቸውም። የማወቅ አቅምም የላትም። እሳቸው ምድራዊ ሳሉ ሰማያዊ የሆኑ ቅዱስ ናቸውና። ባየሁት ሁሉ ተደነቅኩ። አብዝቸም ተገረምኩ። መልካም ያደረገ ሲኖር ብቻ ሳይሆን ሲሞትም በግርማ ይሸኛል። አቤቱ ኢትዮጵያ ትልቅ ሰው እንዳታጣ አንተው ጠብቃት። ዋርካዎች ወድቀው ቁጥቋጦዎች ብቻቸውን እንዳይቀሩ ጠብቃቸው። የዋርካዎችን እድሜ አርዝም። ቁጥቋጦዎችንም ዋርካ አድርግ።

የድካሙን ዓለም መጠናቀቂያ ዘመናቸው ሲደርስ ለ57 ዓመታት በኖሩባት ባዕታቸው “ይህች የዘላለም ማረፊያዬ ናት” አሉ። በዚያውም አረፉ። በምድር የቆዩበት ዘመንም 91 ዓመታት ነው፡፡መልካም እረፍት ይሁንልዎ።

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡

Source link

Related posts

ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ ለትንሣኤ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

admin

በጄኔራል ብርሃኑ ጁላ የተመራ የመከላከያ ሚኒስቴር ከፍተኛ የልኡካን ቡድን በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ጉብኝት እያደረገ ይገኛል

admin

“ዓድዋ ኢትዮጵያውያን ልዩነታቸውን ሁሉ ትተው በአንድነት ሀገራቸውን ከወረራ ያዳኑበት አኩሪ ታሪክ በመሆኑ ትምህርት ልንወስድበት ይገባል” አምባሳደር ታየ አፅቀስላሴ

admin