66.11 F
Washington DC
June 22, 2021
Satenaw Ethiopian News/Breaking News
Amharic News

ʺአንተ በረሃ ሆይ የወገኖቻችንን ነብስ መልስ”ʺአንተ በረሃ ሆይ የወገኖቻችንን ነብስ መልስ”
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 05/2013 ዓ.ም (አብመድ) የምድር ጌጦች ያልተገባ ነገርን ያደርጋሉ። ምድርን ከፈጠራትና ከፈጠራቸው
በታች ሆነው እንዲገዟት የተመረጡት የሰው ልጆች ለፈጣሪያቸው የማይመች ነገርን ሠሩ። ምድርም አልተመቻቸውም፤ ቀደም
ሲል ከገነት የተባረረው የሰው ልጅ አሜካላ በበዛባት ምድር ይኖር ዘንድ ተፈረደበት። ከክብር መውረድ፣ በምድር እየተቅበዘበዙ
መሳደድ፣ በበረዶ መኮራተም፣ በበረሃ መንደድ ሆነ፡፡ ብዙ ተባዙ እንዳለ የሰው ልጅ ምድርን ይሞላት ጀመር።
ለሰው ልጅ መኖሪያነት በተሰጠችው ምድር አያሌ ነገሮች ተደርገዋል። በሕግና በትዕዛዝ የሚኖሩ ሰዎች ተወልደውባታል።
ከምድሩም ከሰማዩም ገዥ ሕግና ትዕዛዝ ያፈነገጡም መጥተውባታል። በምድር ያልሆነ ደግነት፣ ያልሆነስ ክፋት ምን አለና፤
ባየሁት ነገር ሁሉ አብዝቼ ደነገጥኩ፣ ልቤም በሀዘን ተመላች፤ ፈጣሪ ምድርን እያት አስባትም፣ በዱርና በገደል ሁሉ የሚቀሩትን
ሁሉ ተቀበላቸው፣ በረሃውን መልካም እያደረክ አሳልፋቸው፤ ቅድስት ሀገራቸውንም ባርክላቸው፣ ልባቸውንም በሀገራቸው ፍቅር
የተመላ አድርግላቸው አልኩ፡፡
ሰማይ በከዋክብት ተውቧል፣ ምድር ደግሞ በጨለማ ተከቧል፣ የሰው ልጅም በአርምሞ ተኝቷል፤ ሞቃታማዋ ድሬዳዋ ሲገርፋት
ከዋለው ወበቅ ያረፈች ትመስላች፡፡ እንደ እንፋሎት የሚጋረፈው ሙቀት ቀንሶ ቀዝቀዝ ያለ አየር ይነፍስ ጀምሯል፡፡ ሌሊቱ ሊነጋጋ
ተቃርቧል፡፡ አዕዋፋት የመንጋቱን ብስራት ለመናገር ይሁን ስለ ነጋላቸው ለማመስገን ዝማሬያቸውን ጀምረዋል፡፡ አንድ ቦታ እናይ
ዘንድ ጉዞ ተዘጋጅቶልናል፤ በረሃውን ለመቋቋም ጉዞው በጠዋት መሆን አለበት ስለተባለ በሌሊት ተነስቼ ካረፍኩባት ሆቴል በር ላይ
ቆሚያለሁ፡፡
በጠዋት የተነሱ ተሸከርካሪዎች በጎዳናው ሲያልፉ ይታያሉ፡፡ ቁጥራቸው ጥቂት ናቸው፡፡ እኔም ወደ ተባለው ሥፍራ የሚያደርሰኝን
መኪና ነበር የምጠብቀው፡፡ዓይኔ አካባቢውን ያማትራል፣ ቅርንጫፍና ቅርንጫፋቸው የገጠሙት የድሬዳዋ የመንገድ ዳር ዛፎች
ከመንገድ ዳር መብራቶች ጋር ተዳምረው ውበታቸው ልዩ ሆኗል፡፡ አዕዋፋት ዝማሬያቸውን ቀጥለዋል፡፡ እኔም መኪናውን
እየተጠባበኩ ነው፡፡
የጠበኩት መጣ፡፡ በመኪናው ውስጥ ሌሎች ተጓዦችም ነበሩበት፡፡ ሰላምታ ሰጥቻቸው ተቀላቀልኩ፡፡ በሌሊት ይሆናል የተባለው
ጉዞ በአንዳንድ ምክንያቶች ሌሊቱ እስኪነጋ ድረስ ከከተማው ሳንወጣ ቆየን፡፡ የጉዞው ዝግጅት ተጠናቆ በድሬዳዋ ሰሜን ምሥራቅ
አቅጣጫ ወጥተን ከነፍን፡፡ የበረሃዋን ንግሥት ወደኋላ ትተናት ወደፊት ገሰገስን፡፡
ጀንበር ልትወጣ ተቃርባለች፡፡ በምሥራቅ የሚታየው ሰማይ ማብረቅረቅ ጀምሯል፤ ሁሉም በአግራሞት ያለ ይመስላል፡፡ በተመስጦ
አካባቢውን ያማትራልና፤ ከድሬዳዋ ብዙም ሳንርቅ ጀንበር ፈገግ ማለት ጀመረች፡፡ እርጥበት የተጠማው መሬት ያስፈራል፡፡
የጀንበር በምሥራቅ አዘላለቅ አስገረመኝ፡፡ በምሥራቅ ጋራ አይታይምና ጀንበር ከሰማይ ሳይሆን ከምድር የምትወጣ ትመስላለች፡፡
ጨረሯ በዓይኔ ውኃ እስኪሞላብኝ ድረስ በአግራሞት ተመለከትኳት፡፡ እንዲህም አለ ለካ አልኩ በልቤ፡፡ ጉዟችን በሱማሌ ክልል
ደወሌ ጠረፍን እያቋረጡ ወደ ጅቡቲ የሚሄዱ ኢትዮጵያውያን መውጫና መግቢያ ለማየት ነበር፡፡ በረሃ በጠናበት መንገድ በፍተሻ
ሥራ የተሠማሩ የአካባቢው ሚሊሻዎች በየመንገዱ ያስቆሙናል፤ የጉዞ ዓላማችን ስንነግራቸው መልካሙን ሁሉ ተመኝተው
ይሸኙናል፡፡
ጉዟችን ቀጥሏል፡፡ በበረሃው መካከል በሸራ የተሠሩ ቤቶች ይታያሉ፤ በቤቶቹ አቅራቢያ ደግሞ ላታቸው የረዘመ በጎችና ግመሎች
ይታያሉ፡፡ በርካታ መንደሮችን እያለፍን ወደፊት ገሰገስን፡፡ አራዋ፣ ሚሎ፣ አንዶቤድ፣ አዲጋላ፣ ማሊክ፣ ላሳራትና ሌሎችን የመንድ
ዳር የበረሃ መንደሮች ተጉዘን አይሻ ደርሰን፡፡ አይሻ ታሪካዊት ከተማ ናት፡፡ የኢሳ ጎሳ ንጉሥ ኦጋዝ ጀግና ልጅ ነበረቻቸው። እርሷም
አይሻ ትባላለች፡፡ ጀብዶችን ፈፅማለች፡፡ ለጀግንነቷ መታሰቢያ ይሆን ዘንድም በስሟ ከተማ ተመሰረተላት፡፡ ከተማዋም አይሻ
ትሰኛለች፡፡ አንዳንዶች ደግሞ አይሻ ማለት በሱማሊኛ ቋንቋ ጥጋብ ማለት ነው፤ አካባቢውም መልካምና ጥጋብ ስለሆነ አይሻ
ተባለች ይላሉ፡፡ ከተማዋ ላይ ወረድን፡፡
ከአይሻ ወረዳ የሥራ ኃላፊዎች ይጠብቁን ነበርና አገኘናቸው፡፡ አይሻን እያለፉ ስለሚጓዙ ኢትዮጵያውያን ይነግሩን ዘንድ ነበር
ልናገኛቸው የወደድነው፡፡ ቁጥራቸው ብዙ የሆኑ ኢትዮጵያውያን ቀያቸውን እየለቀቁ በድሬዳዋ ይሰባሰባሉ፡፡ ከድሬዳዋ በኋላ
ስለሚገጥማቸው ነገር እምብዛም አያውቁም፡፡ ጓዛቸውን እየጠቀለሉ በእግራቸው በረሃውን ያቆራርጣሉ፡፡
በበረሃው የሚቀመስ ጉርስ፣ ጉሮሮ የሚያርስ ውኃ አይገኝም፡፡ በላይ የፀሐይ ሀሩር፣ በምድር ደግሞ የጋለ መሬት ያቃጥላቸዋል፡፡
እድል ከእነርሱ ጋር የሆነች ሁሉ በረሃውን አልፈው፣ ባሕሩን ተሻግረው ልባቸው ወደ ከጀለው ይደርሳሉ፡፡ እድል ከእነርሱ ጋር
ያልሆነችው ደግሞ ውኃ ጠምቷቸው፣ እንጀራ እርቧቸው፣ ሐሩር አንድዷቸው፣ የበረሃ አውሬ በልቷቸው መንገድ ላይ ይቀራሉ፡፡
የበረሃ ሲሳይ ሆነው የቀሩት የትየለሌ ናቸው፡፡ ልጇን የናፈቀች እናት ከዛሬ ነገ ይመጣል ስትል የአብራኳ ክፋይ የውኃ ሽታ ሆኖ
ይቀራል፡፡ ሞተልሽ ተብላ እርሟን አታወጣም፣ መጣልሽ ተብላ ደስ ብሏት ነጭ ለብሳ አትወጣም፡፡ እንደተብከነከነች የእርሷ እጣ
ይደርሳል፡፡ ደስታ እንደራቃት ታልፋለች፡፡
በሱማሌ ክልል የሽልሌ ዞን የአይሻ ወረዳ የሥራ ኃላፊዎች የፍልሰተኞች እንቅስቃሴ አስቸጋሪ እንደሆነ ነበር የነገሩን፡፡ በመኪና
የሚያልፉትን መቆጣጠር ቢቻል እንኳን በእግራቸው የሚያልፉትን መቆጣጠር አስቸጋሪ መሆኑን ገልጸውልናል፡፡ መደበኛ
ያልሆነውን ፍልሰት ለመከላከል ጥረት እያደረጉ መሆኑንም ነግረውናል፡፡ ነገር ግን የፍልሰቱ በየጊዜው መቀያየር ሥራችንን
አስቸጋሪ አድርጎብናልም ብለውናል፡፡
“ድሬዳዋ ይነሳሉ፣ አብዛኛዎቹ በእግራቸው ይጓዛሉ፣ ሌሎቹ ደግሞ በመኪና ይመጣሉ፣ ደላላዎቹ በሌሊት ያመጧቸውና በመንገድ
ላይ የሚገኝን አንድ የከተማ መብራት አሳይተው ጅቡቲ ደረሳችኋል ብለው ያወርዷቸዋል፤ ግን ከኢትዮጵያ አልወጡም፣ ነግቶ
ሲያዩት እንዳልደረሱ ያውቁታል” ነው ያሉን፡፡
በአካባቢው የሞባይል ኔትወርክ አስቸጋሪ መሆን የቁጥጥር ሥራውን ከባድ ማድረጉንም ሰምቻለሁ፡፡ አካባቢውን ለመቃኘት
ወደበረሃ የሚወርዱ የጸጥታ አካላት በየቀኑ ሬሳ ያገኛሉ፣ አፈር እያለበሱ ያልፋሉ፡፡ የሰው ልጅ እንደ ዋዛ እንደ ቅጠል ይረግፋል፣
እንደ ጥላ ያልፋል፤ ልቤን ሀዘን መላው፡፡ በሞታቸው ሳይለቀስላቸው በረሃ የበላቸው ወገኖቼ አሳዘኑኝ፡፡
የአይሻ ወረዳ የሥራ ኃላፊዎችን አመስግነን ጉዧችን ቀጠለ፡፡ ደወሌ መዳረሻችን ነው፡፡ በረሃው ይጋረፋል፤ ሰማይና ምድር
የተያያዙ ይመስላሉ፤ በግራም በቀኝም ሲታይ የምድር መጨረሻ የደረሰ ይመስላል፡፡ ወደላይ ሲያዩ የጠራ ሰማይ ወደ ታች ሲያዩም
የሚያቃጥል ደረቅ ምድር፤ ያን አይቶ የማያዝን ያለ አይመስልም፡፡ ምን አይነት የጨከነ ልብ ቢኖራቸው፣ ምን አይነትስ ችግር
ቢገጥማቸው ነው ይሄን በረሃ በእግራቸው የሚያቆራርጡት አልኩ፡፡ “አንተ በረሃ ሆይ የወገኖቻችንን ነብስ መልስ አልኩ” በልቤ፤
በረሃው አይከሰስም፣ አይወቅስም፣ የመጣውን እየበላ ዝም ይላል፡፡ ዳሩ ሄዱበት እንጂ አልሄደባቸውም፡፡ ነኩት እንጂ
አልነካቸውም፣ እውን ኢትዮጵያ ተሠርቶ የሚከበርባት፣ ተወልዶ የሚጌጥባት ሀገር ሆና ሳለ ለምን የበረሃ ሞት ተመረጠ፤
ያልታዬውን ለማየት ቢወደድ፣ ኑሮን የተሻለ ለማድረግ ቢታቀድ እንኳን በሕጋዊ መንገድ ከሀገር መውጣት ምን አለ? ይገርማል፡፡
ʺባሕረ እሳትን በዋና የምታሻግር ዋናተኛ፣ ከዚህች ዓለም የጥፋት ባሕር ታሻግረን ዘንድ ኃላፊ ጠፊ በሚሆን አንደበታችን
ሁልጊዜም እንለምናለን” አልኩ በለሆሳስ፤ የምሥራቹን ለማዬት የተጓዙትን የብርሃን ኮኮብና መላእክ መራቸው፡፡ ልባቸው
የሻተውንም አሳያቸው፡፡ እነዚህ ግን እንደዛ አይደሉም፡፡
ጉዟችን ቀጥሏል፤ ደወሌ ደረስን፡፡ የኢትዮጵያ የወደብ ከተማ ናት፡፡ ከደወሌ ጥቂት ኪሎሜትሮችን እንደተጓዙ ጅቡቲ ይደረሳል፡፡
ወደፊት ገሰገስን፡፡ የኢትዮጵያና የጅቡቲ የድንበር ምልክት ከመንገዱ በስተቀኝ ቆማለች፡፡ ከጅቡቲ ወደ ኢትዮጵያና ከኢትዮጵያ ወደ
ጅቡቲ የሚሄዱ ተሽከርካሪዎች ለፍተሻ ቆመዋል፡፡ ለመግባትና ለመውጣት ፈቃድ መጠየቅ ግዴታ ነው፡፡ የጠረፍ ጠባቂዎችን
ጠይቀን የኢትዮጵያን ድንበር ተሻገርን፤ በጠረፍ አካባቢ ያለውን እንቅስቃሴም ተመለከትን፡፡ የጅቡቲ መንግሥት ይዞ
የሚያመጣቸው ኢትዮጵያውያን በጊዜያዊነት የሚያርፉበት መጠለያ በኢትዮጵያ በኩል አለ፡፡ በመጠለያው የሚላስ የሚቀመስ
የለም፡፡ ዜጋ መሆናቸው ብቻ ተረጋግጦ ከመጠለያው እንዲወጡ ይደረጋሉ፡፡ የተራቡና የተጠሙ ጎሮሮዎች ውኃና ምግብ ይሻሉ፡፡
አያገኙም፡፡ ሴቶችና ህፃናትም የስቃዩ ቀማሾች ናቸው፡፡
አብዛኛዎቹ ተጓዦች በጅቡቲና በሌላው ሀገር መልካም ነገር እንዳለ ስለሚሰሙ ያን ለማዬት የሄዱ መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡
የተሻለ ሕይወትን ለመምራት የሚወጡትም ብዙዎች ናቸው፡፡ በጅቡቲ በሚኖራቸው ቆይታም ትርፋቸው መገረፍና መሰቃየት
እንደሆነም ነግረውናል፡፡ ረሃብና ጥም የጠናባቸው ሕፃናት ጫጫታ ልብ ይሰብራል፡፡ ʺ የሀገራችንን ንጹሕ ውኃ አጠጡን››
የሚሉት ብዙዎች ናቸው፡፡ እኔ ባየሁት ሁሉ አዘንኩ፡፡ ከሁሉም የሚገርመው በጅቡቲ ፖሊስ ተይዘው ወደ ሀገራቸው የተመለሱት
ኢትዮጵያውያን ተመልሰው ወደ ጅቡቲ መግባትን ይሻሉ፡፡ ጥቂቶች ወደ ቤተሰቦቻቸው መመለስ ይፈልጋሉ፡፡ አብዛኛዎቹ ግን ʺምን
ይዤ ልመለስ” በሚል አስቸጋሪ ሀሳብ ተወጥረው ተመልሰው መሄድ ምርጫቸው ነው፡፡
የበረሃው ሐሩር መቆሚያ መቀመጫ ነስቷል፡፡ በዚያ በረሃ ወደ ሀገራቸው የሚመለሱ ኢትዮጵያዊያን በእግራቸው ሲጓዙ ይታያሉ፡፡
የደወሌ ቆይታችን ተጠናቀቀ፡፡ ወደ ድሬዳዋም ተመለስን፡፡ ያየሁትን ሁሉ መርሳት አቃተኝ፤ ኢትዮጵያውያን ቢቻላቸው በሀገራቸው
ሠርተው ይለወጡ፤ ባይቻላቸው ግን በሕግ አግባብ ቢሄዱ መልካም ነው፡፡ እንደዚያ ሳይሆን ቢቀር ግን መከራው የከፋ ነው፡፡
በበረሃ መሞት፣ በአውሬ መበላት፣ ሩቅ አልሞ በቅርብ መቅረት አለና፤ አቤቱ ሀገራቸውን ባርከህ በሀገራቸው እንዲኖሩ
አድርጋቸው፣ መሄድ የሻቱንም በረሃውን አሻግራቸው እንጂ የበረሃ ሲሳይ ሆነው እንዲቀሩ አታድርጋቸው፡፡
በታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
Previous articleየ2013 ሀገራዊ ምርጫ ስኬታማ ሆኖ እንዲጠናቀቅ እየሠራ መሆኑን ኢዜማ ገለጸ፡፡
Next articleበጋምቤላ ክልል በ25 ሚሊየን ብር ወጪ የተገነባው የጸሐይ ሀይል ማመንጫ ፕሮጀክት ሥራ ጀመረ፡፡

Source link

Related posts

ጉራማይሌው ሕገ-መንግሥታችን – ከመርሐጽድቅ መኮንን አባይነህ | Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider

admin

የተቀነባበረው ኢትዮጵያን የማፈራረስ ሴራና የአንድነት ኃይሎች ድክመት

admin

የሕግ ማሻሻያዎች ባለፉት ሦስት ዓመታት ለተሰሩት ሥራዎች ምሰሶዎች ናቸው – ጠ/ሚ ዐቢይ

admin